ከዚያም በኋላ ሙሴና አሮን ወደ ግብጽ ንጉሥ ሄደው “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ‘በበረሓ ለእኔ በዓል ለማድረግ እንዲሄዱ ሕዝቤን ልቀቅ’ ይልሃል” አሉት። ንጉሡም “ለመሆኑ እግዚአብሔር ማን ነው? የእርሱንስ ትእዛዝ ሰምቼ እስራኤልን የምለቀው ለምንድን ነው? እኔ እግዚአብሔርን አላውቅም፤ እስራኤልንም አለቅም” አለ። ሙሴና አሮንም “የዕብራውያን አምላክ ለእኛ ተገልጦልናል፤ የሦስት ቀን መንገድ ወደ በረሓ ተጒዘን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እናቀርብ ዘንድ ፍቀድልን፤ እኛ ይህን ባናደርግ በበሽታ ወይም በጦርነት እንድናልቅ ያደርጋል” ሲሉ መለሱለት። ንጉሡም እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ሙሴና አሮን ለምን ሕዝቡን ሥራ ታስፈታላችሁ? በሉ ወደ ሥራችሁ ተመለሱ!” ከዚያም ንጉሡ እንዲህ አለ፤ “እነሆ፥ አሁን እናንተ ከአገሬው ሕዝብ በዝታችኋል፤ እናንተ ሙሴና አሮን ደግሞ ሥራ ታስፈቱአቸዋላችሁ።” በዚያኑ ቀን ንጉሡ ፈርዖን ጨካኞች የሆኑትን ግብጻውያን አሠሪዎችንና የእስራኤላውያን ሠራተኞች አለቆችን እንዲህ ብሎ አዘዘ፥ “ለጡብ ሥራ የሚሆን ገለባ ለሕዝቡ እንደ ወትሮው አትስጡ፤ እነርሱ ራሳቸው ገለባውን ፈልገው ያምጡ፤ ነገር ግን ቀድሞ ይሠሩት የነበረውን ያኽል አንድ ጡብ እንኳ ሳይጐድል እንዲያስረክቡ አድርጉ፤ ‘ለአምላካችን መሥዋዕት እናቀርብ ዘንድ ልቀቀን!’ እያሉ የሚነዘንዙኝ ብዙ የሚሠሩት ነገር ስለሌለ ነው፤ ሐሰተኛ ወሬ የሚሰሙበት ጊዜ እንዳይኖራቸው፥ እነዚህ ሰዎች ከምንጊዜውም ይልቅ በሥራ እንዲጠመዱና በብርቱ እንዲሠሩ አድርጉአቸው።” ጨካኞች የሆኑት ግብጻውያን አሠሪዎችና የእስራኤላውያን ሠራተኞች አለቆች ሄደው ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ አሉ፤ “ንጉሡ ከእንግዲህ ወዲህ ገለባ እንዳይሰጣችሁ አዞአል፤ ራሳችሁ ሄዳችሁ ከየትም ስፍራ ፈልጋችሁ ማምጣት ይኖርባችኋል፤ ነገር ግን የምትሠሩት ጡብ ቊጥር ማነስ የለበትም።” ስለዚህ ሕዝቡ ገለባ ፈልገው ለማግኘት በመላይቱ የግብጽ ምድር ተሰማሩ። ጨካኞች የሆኑትም አሠሪዎች ቀድሞ ገለባ እየሰጡአቸው ይሠሩት የነበረውን ያኽል ጡብ ቈጥረው እንዲያስረክቡ ያስገድዱአቸው ጀመር። እነዚህም ጨካኞች የሆኑት ግብጻውያን አሠሪዎች፥ የእስራኤላውያን ሠራተኞችን አለቆች “ቀድሞ ትሠሩት የነበረውን ያኽል ጡብ ሠርታችሁ የማታስረክቡት ስለምንድነው?” እያሉ ይገርፉአቸው ነበር። የእስራኤላውያን ሠራተኞች አለቆችም ወደ ንጉሡ ቀርበው “ንጉሥ ሆይ፥ በእኛ በአገልጋዮችህ ላይ እንዴት ይህን ሁሉ ነገር አደረግህብን? ምንም ገለባ ሳይሰጠን ጡብ እንድንሠራ ታዘናል፤ ከዚህም ጋር እነሆ፥ እየተገረፍን ነው፤ ስሕተቱ ግን የገዛ ሕዝብህ ነው እንጂ የእኛ አይደለም” ሲሉ አቤቱታቸውን አቀረቡ። ንጉሡም መልሶ “እናንተ ሥራ የማትወዱ ሰነፎች ናችሁ፤ በፍጹም ሰነፎች ናችሁ፤ ‘ሄደን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እንድናቀርብ ልቀቀን’ እያላችሁ የምትጠይቁበትም ምክንያት ይኸው ነው፤ በሉ አሁንም ወደ ሥራችሁ ተመለሱ! ከቶ ገለባ አይሰጣችሁም፤ ነገር ግን ቀድሞ የምትሠሩትን ያኽል ጡብ እየሠራችሁ ማስረከብ ይኖርባችኋል!” አላቸው። የእስራኤላውያን ሠራተኞች አለቆች ቀድሞ የሚሠሩትን ያኽል ጡብ በየቀኑ መሥራት እንዳለባቸው በተረዱ ጊዜ በመከራ ላይ መውደቃቸውን ተገነዘቡ። ከንጉሡም ፊት እንደ ወጡ፥ እነርሱን በመጠባበቅ ላይ የነበሩትን ሙሴንና አሮንን አገኙአቸው፤ ሙሴንና አሮንንም “በንጉሡ በፈርዖንና በመኳንንቱ ዘንድ እጅግ እንድንጠላ በማድረጋችሁና በሰይፍ ይገድሉንም ዘንድ ምክንያት በመሆናችሁ፥ እግዚአብሔር ይይላችሁ፤ እርሱም ይፍረድባችሁ፤” አሉአቸው። ሙሴም እንደገና ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ እንዲህ አለ፤ “አምላክ ሆይ! በዚህ ሕዝብ ላይ ይህን ያኽል መከራ የምታደርስበት ስለምንድነው? እንዲህ ከሆነ እኔንስ ወደዚህ ስለምን ላክኸኝ? እኔ በአንተ ስም ለመናገር ወደ ንጉሡ መቅረብ ከጀመርኩበት ጊዜ አንሥቶ እርሱ በዚህ ሕዝብ ላይ የባሰ መከራ አምጥቶበታል፤ አንተም ይህን ሕዝብ ለመታደግ ከቶ አልፈቀድክም።”
ኦሪት ዘጸአት 5 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘጸአት 5:1-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች