ከዚህም በኋላ ሙሴና አሮን ሄደው ፈርዖንን እንዲህ አሉት፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘በምድረ በዳ በዓል ያደርግልኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።”’ ፈርዖንም፦ “ቃሉን እሰማ ዘንድ እስራኤልንስ እለቅቅ ዘንድ እግዚአብሔር ማን ነው? እግዚአብሔርን አላውቅም፤ እስራኤልንም ደግሞ አልለቅቅም፤” አለ። እነርሱም፦ “የዕብራውያን አምላክ ተገናኘን፤ ቸነፈር ወይም ሰይፍ እንዳይጥልብን የሦስት ቀን መንገድ በምድረ በዳ እንድንሄድ፥ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር እንድንሠዋ እንለምንሃለን፤” አሉት። የግብፅ ንጉሥም፦ “አንተ ሙሴ! አንተም አሮን! ሕዝቡን ለምን ሥራቸውን ታስተዋላችሁ? ወደ ተግባራችሁ ሂዱ!” አላቸው። ፈርዖንም፦ “እነሆ የምድሩ ሕዝብ አሁን በዝቶአል፤ እናንተም ሥራቸውን ታስፈቱአቸዋላችሁ” አለ። ፈርዖንም በዚያን ቀን የሕዝቡን አስገባሪዎች ሹማምቶቹንም እንዲህ ሲል አዘዘ፤ እንደ ወትሮው ለጡብ ሥራ ደግሞ ገለባ ለሕዝቡ አትስጡ፤ ነገር ግን እነርሱ ሄደው ገለባ ይሰብስቡ። ቀድሞ ያደርጉት የነበረውን የጡብ ቁጥር በእነርሱ ላይ አድርጉት፤ ምንም ከእርሱ አታጉድሉ፤ ሥራ ሰልችተዋልና ስለዚህ፥ ‘ለአምላካችን እንድንሰዋ እንሂድ’ እያሉ ይጮኻሉ። እርሱንም ያደርጉ ዘንድ በሰዎች ላይ ሥራው ይክበድባቸው፤ ከንቱ ቃልም አያስቡ።” የሕዝቡም አስገባሪዎች ሹማምቶቹም ወጡ፤ ሕዝቡንም፥ “ፈርዖን እንዲህ ይላል፦ ‘ገለባ አልሰጣችሁም። እናንተ ሂዱ፤ ከምታገኙበትም ስፍራ ገለባ ሰብስቡ፤ ከሥራችሁ ግን ምንም አይጎድልም፤”’ አሉአቸው። ሕዝቡም ስለ ገለባ እብቅ ሊሰበስቡ በግብፅ ምድር ሁሉ ተበተኑ። አስገባሪዎቹም፥ “ገለባ ትቀበሉበት እንደ ነበረ ጊዜ የቀን ሥራችሁን ጨርሱ፤” እያሉ አስቸኮሉአቸው። የፈርዖንም አስገባሪዎች፦ “ቀድሞ ታደርጉ እንደ ነበራችሁ ትናንትናና ዛሬ የተቆጠረውን ጡብ ስለ ምን አትጨርሱም?” እያሉ በእስራኤል ልጆች ላይ የተሾሙትን አለቆቹን ገረፉ። የእስራኤል ልጆች አለቆችም ወደ ፈርዖን መጡ፤ “ለምን በባሪያዎችህ እንዲህ ታደርጋለህ? ገለባ አይሰጡንም፤ የጡቡንም ሥራ እንድንሠራ ያዝዙናል፤ እነሆም ባሪያዎችህን ይገርፉናል፤ ግድፈቱ ግን በአንተ ሕዝብ ላይ ነው” ብለው ጮሁ። እርሱ ግን፦ “ሰልችታችኋል፤ ሰልችታችኋል፤ ስለዚህም፦ ‘እንሂድ ለእግዚአብሔርም እንሠዋ’ ትላላችሁ። አሁንም ሂዱ፤ ሥሩ፤ ገለባ አይሰጡአችሁም፤ የጡቡን ቁጥር ግን ታመጣላችሁ፤” አላቸው። የእስራኤልም ልጆች አለቆች፦ “ዕለት ዕለት ከምትሰሩት ከጡቡ ቁጥር ምንም አታጕድሉ!” ባሉአቸው ጊዜ ነገሩ እንደ ከፋባቸው አዩ። ከፈርዖንም ዘንድ ሲወጡ ሙሴንና አሮንን በፊታቸው ቆመው ተገናኙአቸው። እነርሱም፦ “በፈርዖንና በባሪያዎቹ ፊት ሽታችንን አግምታችሁታልና፥ ይገድሉንም ዘንድ ሰይፍን በእጃቸው ሰጥታችኋቸዋልና እግዚአብሔር ይመልከታችሁ፤ ይፍረድባችሁም፤” አሉአቸው። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመለሰና፦ “ጌታ ሆይ! ስለ ምን ይህን ሕዝብ አስከፋህ? ስለ ምንስ ላክኸኝ? በስምህ እናገር ዘንድ ወደ ፈርዖን ከገባሁ ወዲህ ይህን ሕዝብ አስከፍቶታልና፤ አንተም ሕዝብህን ከቶ አላዳንኸውም፤” አለ።
ኦሪት ዘጸአት 5 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘጸአት 5:1-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች