ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “በግብጽ ያለውን የሕዝቤን ጭንቀት አይቻለሁ፤ በአስጨናቂዎቻቸው ምክንያት የሚጮኹትን ጩኸት ሰምቼአለሁ፤ ጭንቀታቸውንም ዐውቃለሁ። እነርሱንም ከግብጻውያን እጅ ለማዳን ወርጃለሁ፤ ከግብጽም አውጥቼ አሁን ከነዓናውያን፥ ሒታውያን፥ አሞራውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን፥ የሚኖሩባትን፥ በማርና በወተት የበለጸገችውን ሰፊና ለም የሆነችውን ምድር እሰጣቸዋለሁ። እነሆ፥ የሕዝቤ የእስራኤል ጩኸት ወደ እኔ ደርሶአል፤ ግብጻውያን በእነርሱ ላይ የሚያደርሱባቸውን የግፍ ጭቈና ተመልክቻለሁ፤ ስለዚህ አሁን ሕዝቤን ከግብጽ ምድር ታወጣ ዘንድ ወደ ግብጽ ንጉሥ እልክሃለሁ።” ሙሴ ግን እግዚአብሔርን “ወደ ፈርዖን ሄጄ የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ለማውጣት እኔ ማን ነኝ?” አለ። እግዚአብሔርም መልሶ “አይዞህ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እኔ እንደ ላክኹህም ምልክት የሚሆንህ ይህ ነው፤ ሕዝቤን ከግብጽ በምታወጣበት ጊዜ በዚህ ተራራ ላይ እኔን ታመልኩኛላችሁ” አለው። ሙሴም “እኔ ወደ እስራኤል ሕዝብ ሄጄ ‘የቀድሞ አባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ልኮኛል’ በምላቸው ጊዜ እነርሱ ‘ስሙ ማን ነው?’ ብለው ቢጠይቁኝ ምን እመልስላቸዋለሁ?” አለ። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እኔ ‘ያለሁና የምኖር ነኝ፤’ ስለዚህም ‘እኔ ነኝ’ ወደ እናንተ ልኮኛል” በላቸው፤ እግዚአብሔርም እንደገና ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ በላቸው፦ የአባቶቻችሁ የአብርሃም፥ የይስሐቅ፥ የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር ወደ እናንተ ልኮኛል፤ ይህ የዘለዓለም ስሜ ነው፤ በዚህም ስም ከትውልድ እስከ ትውልድ እታወቃለሁ። እንግዲህ ሂድና የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች ሁሉ በአንድነት ሰብስብ፤ የቀድሞ አባቶቻቸው የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ እኔ እግዚአብሔር የተገለጥኩልህ መሆኔንም ንገራቸው፤ ወደ እነርሱ ወርጄ ግብጻውያን በእነርሱ ላይ ያደረሱባቸውን ግፍና ጭቈና መመልከቴን ንገራቸው። በግፍ ጭቈና ከሚሠቃዩባት ከግብጽ ምድር አውጥቼ እነሆ ዛሬ፥ ከነዓናውያን፥ ሒታውያን፥ አሞራውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን የሚኖሩባትን፥ በማርና በወተት የበለጸገች ሰፊና ለም የሆነች ምድር ልሰጣቸው ቃል ገብቻለሁ።
ኦሪት ዘጸአት 3 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘጸአት 3:7-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos