እነሆ፥ ሙሴ የምድያም ካህን የሆነውን የዐማቹን የየትሮንን በጎች ይጠብቅ ነበር፤ መንጋውንም እየነዳ ከበረሓው ማዶ ወዳለው የእግዚአብሔር ተራራ እየተባለ ወደሚጠራው ወደ ሲና መጣ። እዚያም የእግዚአብሔር መልአክ በቊጥቋጦ ውስጥ በተቀጣጠለ የእሳት ነበልባል መካከል ሆኖ ተገለጠለት፤ ሙሴም ቊጥቋጦው በእሳት ተያይዞ ሳለ ምንም አለመቃጠሉን ተመለከተና፥ “ይህ እንዴት አስገራሚ ሁኔታ ነው? ቊጥቋጦውስ እንዴት አይቃጠልም? ቀርቤ መመልከት አለብኝ” አለ። ሙሴም ሁኔታውን ለማየት በቀረበ ጊዜ እግዚአብሔር ተመለከተው፤ በቊጥቋጦውም መካከል ሆኖ “ሙሴ! ሙሴ!” ብሎ ጠራው። ሙሴም “እነሆ፥ አለሁ” አለ። እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “ወደዚህ አትቅረብ፤ የቆምክባት ምድር የተቀደሰች ስለ ሆነች ጫማህን አውልቅ፤ እኔ የቀድሞ አባቶችህ የአብርሃም፥ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ነኝ፤” በዚህ ጊዜ ሙሴ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ማየት ስለ ፈራ ፊቱን ሸፈነ። ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “በግብጽ ያለውን የሕዝቤን ጭንቀት አይቻለሁ፤ በአስጨናቂዎቻቸው ምክንያት የሚጮኹትን ጩኸት ሰምቼአለሁ፤ ጭንቀታቸውንም ዐውቃለሁ። እነርሱንም ከግብጻውያን እጅ ለማዳን ወርጃለሁ፤ ከግብጽም አውጥቼ አሁን ከነዓናውያን፥ ሒታውያን፥ አሞራውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን፥ የሚኖሩባትን፥ በማርና በወተት የበለጸገችውን ሰፊና ለም የሆነችውን ምድር እሰጣቸዋለሁ። እነሆ፥ የሕዝቤ የእስራኤል ጩኸት ወደ እኔ ደርሶአል፤ ግብጻውያን በእነርሱ ላይ የሚያደርሱባቸውን የግፍ ጭቈና ተመልክቻለሁ፤ ስለዚህ አሁን ሕዝቤን ከግብጽ ምድር ታወጣ ዘንድ ወደ ግብጽ ንጉሥ እልክሃለሁ።” ሙሴ ግን እግዚአብሔርን “ወደ ፈርዖን ሄጄ የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ለማውጣት እኔ ማን ነኝ?” አለ። እግዚአብሔርም መልሶ “አይዞህ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እኔ እንደ ላክኹህም ምልክት የሚሆንህ ይህ ነው፤ ሕዝቤን ከግብጽ በምታወጣበት ጊዜ በዚህ ተራራ ላይ እኔን ታመልኩኛላችሁ” አለው። ሙሴም “እኔ ወደ እስራኤል ሕዝብ ሄጄ ‘የቀድሞ አባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ልኮኛል’ በምላቸው ጊዜ እነርሱ ‘ስሙ ማን ነው?’ ብለው ቢጠይቁኝ ምን እመልስላቸዋለሁ?” አለ። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እኔ ‘ያለሁና የምኖር ነኝ፤’ ስለዚህም ‘እኔ ነኝ’ ወደ እናንተ ልኮኛል” በላቸው፤ እግዚአብሔርም እንደገና ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ በላቸው፦ የአባቶቻችሁ የአብርሃም፥ የይስሐቅ፥ የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር ወደ እናንተ ልኮኛል፤ ይህ የዘለዓለም ስሜ ነው፤ በዚህም ስም ከትውልድ እስከ ትውልድ እታወቃለሁ። እንግዲህ ሂድና የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች ሁሉ በአንድነት ሰብስብ፤ የቀድሞ አባቶቻቸው የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ እኔ እግዚአብሔር የተገለጥኩልህ መሆኔንም ንገራቸው፤ ወደ እነርሱ ወርጄ ግብጻውያን በእነርሱ ላይ ያደረሱባቸውን ግፍና ጭቈና መመልከቴን ንገራቸው። በግፍ ጭቈና ከሚሠቃዩባት ከግብጽ ምድር አውጥቼ እነሆ ዛሬ፥ ከነዓናውያን፥ ሒታውያን፥ አሞራውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን የሚኖሩባትን፥ በማርና በወተት የበለጸገች ሰፊና ለም የሆነች ምድር ልሰጣቸው ቃል ገብቻለሁ። “ሕዝቤም አንተ የምትነግራቸውን ሁሉ ይሰማሉ፤ ከዚያም በኋላ ከእስራኤል ሕዝብ አለቆች ጋር ሆነህ ወደ ግብጽ ንጉሥ ሂድና ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር ተገልጦልናል፤ ስለዚህም ለአምላካችን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እናቀርብ ዘንድ የሦስት ቀን መንገድ ተጒዘን ወደ በረሓ እንድንሄድ ፍቀድልን’ ብላችሁ ንገሩት። እርግጥ ነው በታላቅ ክንድ ካልተገደደ በቀር የግብጽ ንጉሥ እንደማይለቃችሁ ዐውቃለሁ። ስለዚህም እጅግ አስፈሪ የሆኑ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ የኀይል ክንዴን ዘርግቼ ግብጻውያንን እቀጣለሁ፤ ከዚያም በኋላ እንድትወጡ ይፈቅድላችኋል።
ኦሪት ዘጸአት 3 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘጸአት 3:1-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos