ኦሪት ዘጸአት 3:1-20

ኦሪት ዘጸአት 3:1-20 አማ54

ሙሴም የአማቱን የምድያምን ካህን የዮቶርን በጎች ይጠብቅ ነበር፤ ወደ ምድረ በዳ ዳርቻም በጎቹን ነዳ፤ ወደ እግዚአብሔርም ተራራ ወደ ኮሬብ መጣ። የእግዚአብሔርም መልአክ በእሳት ነበልባል በእሾህ ቁጥቍጦው መካከል ታየው፤ እነሆም ቍጥቍጦው በእሳት ሲነድድ ቁጥቍጦውም ሳይቃጠል አየ። ሙሴም፦ “ልሂድና ቁጥቍጦው ስለ ምን እንደማይቃጠል ይህን ታላቅ ራእይ ልይ” አለ። እግዚአብሔር እርሱ ይመለከት ዘንድ እንደ መጣ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር ከቁጥቍጦ ውስጥ እርሱን ጠርቶ፦ “ሙሴ! ሙሴ ሆይ!” አለ። እርሱም፦ “እነሆኝ” አለ። “ወደዚህ አትቅረብ፤ አንተ የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ፤” አለው። ደግሞም፦ “እኔ የአባትህ አምላክ፥ የአብረሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ ነኝ፤” አለው። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ያይ ዘንድ ፈርቶአልና ፊቱን ሸፈነ። እግዚአብሔርም አለ፦ “በግብፅ ያለውን የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ፤ ከአስገባሪዎቻቸውም የተነሣ ጩኸታቸውን ሰማሁ፤ ሥቃያቸውንም አውቄአለሁ። ከግብፃውያንም እጅ አድናቸው ዘንድ፥ ከዚያችም አገር ወተትና ማር ወደምታፈስሰው አገር ወደ ሰፊይቱና ወደ መልካሚቱ አገር ወደ ከነዓናውያንም ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ኢያቡሳውያንም ስፍራ አወጣቸው ዘንድ ወረድሁ። አሁንም እነሆ የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ወጣ፤ ግብፃውያንም የሚያደርጉባቸውን ግፍ ደግሞ አየሁ። አሁንም ና! ሕዝቤን የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ታወጣ ዘንድ ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ።” ሙሴም እግዚአብሔርን፦ “ወደ ፈርዖን የምሄድ የእስራኤልንም ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማን ነኝ?” አለው። እርሱም፦ “በእውነት እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እኔም እንደ ላክሁህ ምልክትህ ይህ ነው፤ ሕዝቡን ከግብፅ ባወጣህ ጊዜ በዚህ ተራራ ላይ ለእግዚአብሔር ትገዛላችሁ፤” አለ። ሙሴም እግዚአብሔርን፦ “እነሆ፥ እኔ ወደ እስራኤል ልጆች በመጣሁ ጊዜ፦ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ’ ባልሁም ጊዜ፦ ‘ስሙስ ማን ነው?’ ባሉኝ ጊዜ፥ ምን እላቸዋለሁ?” አለው። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ “‘ያለና የሚኖር’ እኔ ነኝ” አለው፤ “እንዲህ ለእስራኤል ልጆች፦ ‘ያለና የሚኖር’ ወደናንተ ላከኝ ትላለህ፤” አለው። እግዚአብሔርም ደግሞ ሙሴን አለው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ትላለህ፦ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ፥ የያቆብም አምላክ እግዚአብሔር ወደናንተ ላከኝ፤’ ይህ ለዘላለሙ ስሜ ነው፥ እስከ ልጅ ልጅ ድረስም መታሰቢያዬ ይህ ነው። ሂድ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች ሰብስብ፦ ‘እግዚአብሔር የአባቶቻችሁ አምላክ የአብርሃም የይስሐቅም የያዕቆብም አምላክ፦ መጎብኘትን ጎበኘኋችሁ፤ በግብፅም የሚደረግባችሁን አየሁ፤ ከግብፅም መከራ ወደ ከነዓናውያን ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ያቡሳውያንም አገር ወተትና ማር ወደምታፈስስ አገር አወጣችኋለሁ፤ አልሁ ብሎ ተገለጠልኝ፤’ በላቸው። እነርሱም ቃልህን ይሰማሉ፤ አንተና የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ግብፅ ንጉሥ ትገባላችሁ፤ “የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር ተገለጠልን፤ አሁንም ለአምላካችን ለእግዚአብሔር እንሠዋ ዘንድ የሦስት ቀን መንገድ በምድረ በዳ እንሂድ’ ትሉታላችሁ። ነገር ግን በጽኑ እጅ ካልሆነ በቀር ትሄዱ ዘንድ የግብፅ ንጉሥ እንደማይፈቅድላችሁ እኔ አውቃለሁ። እኔም እጄን እዘረጋለሁ፤ በማደርግባቸውም ተአምራቴ ሁሉ ግብፅን እመታለሁ፤ ከዚያም በኋላ ይለቅቃችኋል።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}