ኦሪት ዘጸአት 3:1-14

ኦሪት ዘጸአት 3:1-14 አማ05

እነሆ፥ ሙሴ የምድያም ካህን የሆነውን የዐማቹን የየትሮንን በጎች ይጠብቅ ነበር፤ መንጋውንም እየነዳ ከበረሓው ማዶ ወዳለው የእግዚአብሔር ተራራ እየተባለ ወደሚጠራው ወደ ሲና መጣ። እዚያም የእግዚአብሔር መልአክ በቊጥቋጦ ውስጥ በተቀጣጠለ የእሳት ነበልባል መካከል ሆኖ ተገለጠለት፤ ሙሴም ቊጥቋጦው በእሳት ተያይዞ ሳለ ምንም አለመቃጠሉን ተመለከተና፥ “ይህ እንዴት አስገራሚ ሁኔታ ነው? ቊጥቋጦውስ እንዴት አይቃጠልም? ቀርቤ መመልከት አለብኝ” አለ። ሙሴም ሁኔታውን ለማየት በቀረበ ጊዜ እግዚአብሔር ተመለከተው፤ በቊጥቋጦውም መካከል ሆኖ “ሙሴ! ሙሴ!” ብሎ ጠራው። ሙሴም “እነሆ፥ አለሁ” አለ። እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “ወደዚህ አትቅረብ፤ የቆምክባት ምድር የተቀደሰች ስለ ሆነች ጫማህን አውልቅ፤ እኔ የቀድሞ አባቶችህ የአብርሃም፥ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ነኝ፤” በዚህ ጊዜ ሙሴ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ማየት ስለ ፈራ ፊቱን ሸፈነ። ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “በግብጽ ያለውን የሕዝቤን ጭንቀት አይቻለሁ፤ በአስጨናቂዎቻቸው ምክንያት የሚጮኹትን ጩኸት ሰምቼአለሁ፤ ጭንቀታቸውንም ዐውቃለሁ። እነርሱንም ከግብጻውያን እጅ ለማዳን ወርጃለሁ፤ ከግብጽም አውጥቼ አሁን ከነዓናውያን፥ ሒታውያን፥ አሞራውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን፥ የሚኖሩባትን፥ በማርና በወተት የበለጸገችውን ሰፊና ለም የሆነችውን ምድር እሰጣቸዋለሁ። እነሆ፥ የሕዝቤ የእስራኤል ጩኸት ወደ እኔ ደርሶአል፤ ግብጻውያን በእነርሱ ላይ የሚያደርሱባቸውን የግፍ ጭቈና ተመልክቻለሁ፤ ስለዚህ አሁን ሕዝቤን ከግብጽ ምድር ታወጣ ዘንድ ወደ ግብጽ ንጉሥ እልክሃለሁ።” ሙሴ ግን እግዚአብሔርን “ወደ ፈርዖን ሄጄ የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ለማውጣት እኔ ማን ነኝ?” አለ። እግዚአብሔርም መልሶ “አይዞህ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እኔ እንደ ላክኹህም ምልክት የሚሆንህ ይህ ነው፤ ሕዝቤን ከግብጽ በምታወጣበት ጊዜ በዚህ ተራራ ላይ እኔን ታመልኩኛላችሁ” አለው። ሙሴም “እኔ ወደ እስራኤል ሕዝብ ሄጄ ‘የቀድሞ አባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ልኮኛል’ በምላቸው ጊዜ እነርሱ ‘ስሙ ማን ነው?’ ብለው ቢጠይቁኝ ምን እመልስላቸዋለሁ?” አለ። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እኔ ‘ያለሁና የምኖር ነኝ፤’ ስለዚህም ‘እኔ ነኝ’ ወደ እናንተ ልኮኛል” በላቸው፤

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}