ዘፀአት 3:1-14
ዘፀአት 3:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አንድ ቀን ሙሴ የምድያም ካህን የሆነውን የዐማቱን የዮቶር በጎችና ፍየሎች እየጠበቀ ሳለ፣ መንጋውን እየነዳ ወደ ምድረ በዳው ዳርቻ አምርቶ የእግዚአብሔር ተራራ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ኮሬብ ቀረበ። እዚያም የእግዚአብሔር መልአክ በቍጥቋጦው ውስጥ በሚንቀለቀል የእሳት ነበልባል መካከል ተገለጠለት። ሙሴም ቍጥቋጦው በእሳት ቢያያዝም እንኳ፣ አለመቃጠሉን አየ። ሙሴም፣ “ቍጥቋጦው ለምን እንደማይቃጠል ቀረብ ብዬ ይህን አስገራሚ ነገር ልመልከት” አለ። ሙሴ ሁኔታውን ለመመልከት መቅረቡን እግዚአብሔር ባየ ጊዜ፣ ከቍጥቋጦው ውስጥ እግዚአብሔር “ሙሴ፣ ሙሴ” ብሎ ጠራው። ሙሴም “አቤት እነሆኝ” አለው። እግዚአብሔርም፣ “ወደዚህ እንዳትቀርብ፤ ይህች የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች ስለ ሆነች ጫማህን ከእግርህ አውልቅ” አለው። ቀጥሎም፣ “እኔ የአባቶችህ የአብርሃም፣ የይሥሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ” አለው። በዚህ ጊዜ ሙሴ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ማየት ስለ ፈራ ፊቱን ሸፈነ። ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፣ “በግብጽ አገር የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ከአሠሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሣ የሚያሰሙትንም ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ሥቃያቸውንም ተረድቻለሁ። ስለዚህም ከግብጻውያን እጅ ልታደጋቸውና ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ሰፊና ለም ወደሆነችው ወደ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ አሞራውያን፣ ፌርዛውያን፣ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር ላወጣቸው ወርጃለሁ። አሁንም የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ደርሷል፤ ግብጻውያን የሚያደርሱባቸውን ግፍ አይቻለሁ። በል እንግዲህ ና፤ ሕዝቤን፣ የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር እንድታወጣቸው ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ”። ሙሴ እግዚአብሔርን፣ “ወደ ፈርዖን የምሄድና የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ የማወጣ እኔ ማን ነኝ?” አለው። እግዚአብሔርም፣ “እኔ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ፤ እኔ የላክሁህ ለመሆኑ ምልክቱ ይህ ነው፤ ሕዝቡን ከግብጽ ካወጣሃቸው በኋላ በዚህ ተራራ ላይ እግዚአብሔርን ታመልካላችሁ” አለው። ሙሴም እግዚአብሔርን፣ “ወደ እስራኤል ልጆች ሄጄ፣ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ልኮኛል’ ስላቸው ‘ስሙ ማን ነው?’ ብለው ቢጠይቁኝ ምን እላቸዋለሁ?” አለው። እግዚአብሔርም ሙሴን፣ “እኔ፣ ያለሁና የምኖር ነኝ፤ ስለዚህም ለእስራኤል ልጆች፣ ‘ያለና የሚኖር ልኮኛል’ ብለህ ንገራቸው” አለው።
ዘፀአት 3:1-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሙሴም የአማቱን የምድያምን ካህን የዮቶርን በጎች ይጠብቅ ነበር፤ በጎቹንም ወደ ምድረ በዳ ዳርቻ ነዳ፤ ወደ እግዚአብሔርም ተራራ ወደ ኮሬብ መጣ። የእግዚአብሔርም መልአክ ለሙሴ በእሳት ነበልባል በቍጥቋጦ መካከል ታየው፤ እነሆም፥ ቍጥቋጦው በእሳት ሲነድድ፥ ቍጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ። ሙሴም፥ “ልሂድና ቍጥቋጦው ስለምን አልተቃጠለም? ይህን ታላቅ ራእይ ልይ” አለ። እግዚአብሔር እርሱ ይመለከት ዘንድ እንደ መጣ በአየ ጊዜ እግዚአብሔር ከቍጥቋጦው ውስጥ እርሱን ጠርቶ፥ “ሙሴ! ሙሴ!” አለው እርሱም፥ “ይህ ምንድን ነው?” አለ። “ወደዚህ አትቅረብ፤ አንተ የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና፥ ጫማህን ከእግርህ አውጣ” አለው። ደግሞም፥ “እኔ የአባቶችህ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ ነኝ” አለው። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ያይ ዘንድ ፈርቶአልና ፊቱን መለሰ። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “በግብፅ ያለውን የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ፦ ከአሠሪዎቻቸውም የተነሣ ጩኸታቸውን ሰማሁ፤ ሥቃያቸውንም ዐውቄአለሁ፤ ከግብፃውያንም እጅ አድናቸው ዘንድ፥ ከዚያችም ሀገር ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ሀገር፥ ወደ ሰፊዪቱና ወደ መልካሚቱ ሀገር፥ ወደ ከነዓናውያንም፥ ወደ ኬጤዎናውያንም፥ ወደ አሞሬዎናውያንም፥ ወደ ፌርዜዎናውያንም፥ ወደ ጌርጌሴዎናውያንም፥ ወደ ኤዌዎናውያንም፥ ወደ ኢያቡሴዎናውያንም ስፍራ አወጣቸው ዘንድ ወረድሁ። አሁንም እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ደረሰ፤ ግብፃውያንም የሚያደርጉባቸውን ግፍ ደግሞ አየሁ። አሁንም ና፤ ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ። ሕዝቤን የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ምድር ታወጣቸዋለህ።” ሙሴም እግዚአብሔርን፥ “ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ፈርዖን እሄድ ዘንድ፥ የእስራኤልንም ልጆች ከግብፅ ምድር አወጣ ዘንድ እኔ ማን ነኝ?” አለው። እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው፤ እንዲህ ሲል፥ “በእውነት እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እኔም እንደ ላክሁህ ይህ ለአንተ ምልክት ይሆንሃል፤ ሕዝቡን ከግብፅ በአወጣህ ጊዜ በዚህ ተራራ ላይ እግዚአብሔርን ታመልካላችሁ” አለው። ሙሴም እግዚአብሔርን፥ “እነሆ፥ እኔ ወደ እስራኤል ልጆች እሄዳለሁ፤ የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ እላቸዋለሁ፤ ‘ስሙስ ማን ነው?’ ብለው በጠየቁኝ ጊዜ ምን እላቸዋለሁ?” አለው። እግዚአብሔርም ለሙሴ ነገረው፤ እንዲህ ሲል፥ “ያለና የሚኖር እኔ ነኝ፤ እንዲህ ለእስራኤል ‘ያለና የሚኖር’ ወደ እናንተ ላከኝ ትላቸዋለህ” አለው።
ዘፀአት 3:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አንድ ቀን ሙሴ የምድያም ካህን የሆነውን የዐማቱን የዮቶር በጎችና ፍየሎች እየጠበቀ ሳለ፣ መንጋውን እየነዳ ወደ ምድረ በዳው ዳርቻ አምርቶ የእግዚአብሔር ተራራ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ኮሬብ ቀረበ። እዚያም የእግዚአብሔር መልአክ በቍጥቋጦው ውስጥ በሚንቀለቀል የእሳት ነበልባል መካከል ተገለጠለት። ሙሴም ቍጥቋጦው በእሳት ቢያያዝም እንኳ፣ አለመቃጠሉን አየ። ሙሴም፣ “ቍጥቋጦው ለምን እንደማይቃጠል ቀረብ ብዬ ይህን አስገራሚ ነገር ልመልከት” አለ። ሙሴ ሁኔታውን ለመመልከት መቅረቡን እግዚአብሔር ባየ ጊዜ፣ ከቍጥቋጦው ውስጥ እግዚአብሔር “ሙሴ፣ ሙሴ” ብሎ ጠራው። ሙሴም “አቤት እነሆኝ” አለው። እግዚአብሔርም፣ “ወደዚህ እንዳትቀርብ፤ ይህች የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች ስለ ሆነች ጫማህን ከእግርህ አውልቅ” አለው። ቀጥሎም፣ “እኔ የአባቶችህ የአብርሃም፣ የይሥሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ” አለው። በዚህ ጊዜ ሙሴ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ማየት ስለ ፈራ ፊቱን ሸፈነ። ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፣ “በግብጽ አገር የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ከአሠሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሣ የሚያሰሙትንም ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ሥቃያቸውንም ተረድቻለሁ። ስለዚህም ከግብጻውያን እጅ ልታደጋቸውና ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ሰፊና ለም ወደሆነችው ወደ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ አሞራውያን፣ ፌርዛውያን፣ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር ላወጣቸው ወርጃለሁ። አሁንም የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ደርሷል፤ ግብጻውያን የሚያደርሱባቸውን ግፍ አይቻለሁ። በል እንግዲህ ና፤ ሕዝቤን፣ የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር እንድታወጣቸው ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ”። ሙሴ እግዚአብሔርን፣ “ወደ ፈርዖን የምሄድና የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ የማወጣ እኔ ማን ነኝ?” አለው። እግዚአብሔርም፣ “እኔ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ፤ እኔ የላክሁህ ለመሆኑ ምልክቱ ይህ ነው፤ ሕዝቡን ከግብጽ ካወጣሃቸው በኋላ በዚህ ተራራ ላይ እግዚአብሔርን ታመልካላችሁ” አለው። ሙሴም እግዚአብሔርን፣ “ወደ እስራኤል ልጆች ሄጄ፣ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ልኮኛል’ ስላቸው ‘ስሙ ማን ነው?’ ብለው ቢጠይቁኝ ምን እላቸዋለሁ?” አለው። እግዚአብሔርም ሙሴን፣ “እኔ፣ ያለሁና የምኖር ነኝ፤ ስለዚህም ለእስራኤል ልጆች፣ ‘ያለና የሚኖር ልኮኛል’ ብለህ ንገራቸው” አለው።
ዘፀአት 3:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሙሴም የአማቱን የምድያምን ካህን የዮቶርን በጎች ይጠብቅ ነበር፤ ወደ ምድረ በዳ ዳርቻም በጎቹን ነዳ፤ ወደ እግዚአብሔርም ተራራ ወደ ኮሬብ መጣ። የእግዚአብሔርም መልአክ በእሳት ነበልባል በእሾህ ቁጥቍጦው መካከል ታየው፤ እነሆም ቍጥቍጦው በእሳት ሲነድድ ቁጥቍጦውም ሳይቃጠል አየ። ሙሴም፦ “ልሂድና ቁጥቍጦው ስለ ምን እንደማይቃጠል ይህን ታላቅ ራእይ ልይ” አለ። እግዚአብሔር እርሱ ይመለከት ዘንድ እንደ መጣ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር ከቁጥቍጦ ውስጥ እርሱን ጠርቶ፦ “ሙሴ! ሙሴ ሆይ!” አለ። እርሱም፦ “እነሆኝ” አለ። “ወደዚህ አትቅረብ፤ አንተ የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ፤” አለው። ደግሞም፦ “እኔ የአባትህ አምላክ፥ የአብረሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ ነኝ፤” አለው። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ያይ ዘንድ ፈርቶአልና ፊቱን ሸፈነ። እግዚአብሔርም አለ፦ “በግብፅ ያለውን የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ፤ ከአስገባሪዎቻቸውም የተነሣ ጩኸታቸውን ሰማሁ፤ ሥቃያቸውንም አውቄአለሁ። ከግብፃውያንም እጅ አድናቸው ዘንድ፥ ከዚያችም አገር ወተትና ማር ወደምታፈስሰው አገር ወደ ሰፊይቱና ወደ መልካሚቱ አገር ወደ ከነዓናውያንም ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ኢያቡሳውያንም ስፍራ አወጣቸው ዘንድ ወረድሁ። አሁንም እነሆ የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ወጣ፤ ግብፃውያንም የሚያደርጉባቸውን ግፍ ደግሞ አየሁ። አሁንም ና! ሕዝቤን የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ታወጣ ዘንድ ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ።” ሙሴም እግዚአብሔርን፦ “ወደ ፈርዖን የምሄድ የእስራኤልንም ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማን ነኝ?” አለው። እርሱም፦ “በእውነት እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እኔም እንደ ላክሁህ ምልክትህ ይህ ነው፤ ሕዝቡን ከግብፅ ባወጣህ ጊዜ በዚህ ተራራ ላይ ለእግዚአብሔር ትገዛላችሁ፤” አለ። ሙሴም እግዚአብሔርን፦ “እነሆ፥ እኔ ወደ እስራኤል ልጆች በመጣሁ ጊዜ፦ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ’ ባልሁም ጊዜ፦ ‘ስሙስ ማን ነው?’ ባሉኝ ጊዜ፥ ምን እላቸዋለሁ?” አለው። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ “‘ያለና የሚኖር’ እኔ ነኝ” አለው፤ “እንዲህ ለእስራኤል ልጆች፦ ‘ያለና የሚኖር’ ወደናንተ ላከኝ ትላለህ፤” አለው።
ዘፀአት 3:1-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እነሆ፥ ሙሴ የምድያም ካህን የሆነውን የዐማቹን የየትሮንን በጎች ይጠብቅ ነበር፤ መንጋውንም እየነዳ ከበረሓው ማዶ ወዳለው የእግዚአብሔር ተራራ እየተባለ ወደሚጠራው ወደ ሲና መጣ። እዚያም የእግዚአብሔር መልአክ በቊጥቋጦ ውስጥ በተቀጣጠለ የእሳት ነበልባል መካከል ሆኖ ተገለጠለት፤ ሙሴም ቊጥቋጦው በእሳት ተያይዞ ሳለ ምንም አለመቃጠሉን ተመለከተና፥ “ይህ እንዴት አስገራሚ ሁኔታ ነው? ቊጥቋጦውስ እንዴት አይቃጠልም? ቀርቤ መመልከት አለብኝ” አለ። ሙሴም ሁኔታውን ለማየት በቀረበ ጊዜ እግዚአብሔር ተመለከተው፤ በቊጥቋጦውም መካከል ሆኖ “ሙሴ! ሙሴ!” ብሎ ጠራው። ሙሴም “እነሆ፥ አለሁ” አለ። እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “ወደዚህ አትቅረብ፤ የቆምክባት ምድር የተቀደሰች ስለ ሆነች ጫማህን አውልቅ፤ እኔ የቀድሞ አባቶችህ የአብርሃም፥ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ነኝ፤” በዚህ ጊዜ ሙሴ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ማየት ስለ ፈራ ፊቱን ሸፈነ። ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “በግብጽ ያለውን የሕዝቤን ጭንቀት አይቻለሁ፤ በአስጨናቂዎቻቸው ምክንያት የሚጮኹትን ጩኸት ሰምቼአለሁ፤ ጭንቀታቸውንም ዐውቃለሁ። እነርሱንም ከግብጻውያን እጅ ለማዳን ወርጃለሁ፤ ከግብጽም አውጥቼ አሁን ከነዓናውያን፥ ሒታውያን፥ አሞራውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን፥ የሚኖሩባትን፥ በማርና በወተት የበለጸገችውን ሰፊና ለም የሆነችውን ምድር እሰጣቸዋለሁ። እነሆ፥ የሕዝቤ የእስራኤል ጩኸት ወደ እኔ ደርሶአል፤ ግብጻውያን በእነርሱ ላይ የሚያደርሱባቸውን የግፍ ጭቈና ተመልክቻለሁ፤ ስለዚህ አሁን ሕዝቤን ከግብጽ ምድር ታወጣ ዘንድ ወደ ግብጽ ንጉሥ እልክሃለሁ።” ሙሴ ግን እግዚአብሔርን “ወደ ፈርዖን ሄጄ የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ለማውጣት እኔ ማን ነኝ?” አለ። እግዚአብሔርም መልሶ “አይዞህ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እኔ እንደ ላክኹህም ምልክት የሚሆንህ ይህ ነው፤ ሕዝቤን ከግብጽ በምታወጣበት ጊዜ በዚህ ተራራ ላይ እኔን ታመልኩኛላችሁ” አለው። ሙሴም “እኔ ወደ እስራኤል ሕዝብ ሄጄ ‘የቀድሞ አባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ልኮኛል’ በምላቸው ጊዜ እነርሱ ‘ስሙ ማን ነው?’ ብለው ቢጠይቁኝ ምን እመልስላቸዋለሁ?” አለ። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እኔ ‘ያለሁና የምኖር ነኝ፤’ ስለዚህም ‘እኔ ነኝ’ ወደ እናንተ ልኮኛል” በላቸው፤
ዘፀአት 3:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሙሴም የምድያን ካህን የሆነውን የአማቹን የይትሮን በጎች ያሰማራ ነበር፤ በጎቹን ከምድረ በዳው ማዶ ነዳቸው፥ ወደ እግዚአብሔርም ተራራ ወደ ኮሬብ መጣ። የጌታም መልአክ በእሳት ነበልባል በቁጥቋጦው መካከል ታየው፤ ቁጥቋጦው በእሳት ሲነድድ ቁጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ። ሙሴም፦ “ልሂድና ይህን ታላቅ ራእይ ልይ ቁጥቋጦው ለምን አልተቃጠለም?” አለ። ጌታም እርሱን ሊያይ እንደመጣ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር ከቁጥቋጦው መካከል፦ “ሙሴ፥ ሙሴ” ብሎ ጠራው። እርሱም፦ “እነሆኝ” አለ። እርሱም “ወደዚህ አትቅረብ፤ ጫማህን ከእግርህ አውልቅ የቆምህበት ስፍራ የተቀደሰ መሬት ነውና” አለው። እርሱም፦ “እኔ የአባትህ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅ አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ ነኝ” አለው። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ማየት ፈርቶ ፊቱን ሸፈነ። ጌታም አለ፦ “በግብጽ ያለውን የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ፥ በአስገባሪዎቻቸውም ምክንያት የሚጮሁትን ጩኸት ሰማሁ፤ ሥቃያቸውንም አውቄአለሁ። ከግብፃውያን እጅ አድናቸው ዘንድ፥ ከዚያችም አገር ወደ መልካምና ሰፊ አገር፥ ወተትና ማር ወደምታፈስሰው አገር ወደ ከነዓናውያን፥ ሒቲያውያን፥ ኤሞራውያን፥ ፌርዛውያን፥ ሒዊያውያን፥ የቡሳውያንም ስፍራ አወጣቸው ዘንድ ወረድሁ። አሁን ደግሞ የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ መጣ፤ ግብፃውያን የሚያደርጉባቸውን ግፍ ደግሞ አየሁ። ስለዚህ ሂድ፥ ሕዝቤን የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ እንድታወጣ ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ።” ሙሴም እግዚአብሔርን፦ “ወደ ፈርዖን የምሄድና የእስራኤልንም ልጆች ከግብጽ የማወጣ እኔ ማን ነኝ?” አለው። እርሱም፦ “እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እኔም እንደ ላክሁህ ምልክትህ ይህ ይሆናል፤ ሕዝቡን ከግብጽ ባወጣህ ጊዜ በዚህ ተራራ ላይ እግዚአብሔርን ታገለግላላችሁ” አለ። ሙሴም እግዚአብሔርን፦ “እኔ ወደ እስራኤል ልጆች ሄጄ፦ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ’ ባልሁ ጊዜ፦ ‘ስሙ ማን ነው?’ ቢሉኝ፥ ምን እላቸዋለሁ?” አለው። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ “የምኖር እኔ ነኝ” አለው፤ ስለዚህ ለእስራኤል ልጆች፦ “‘የምኖር’ ወደ እናንተ ላከኝ በላቸው” አለው።