ሙሴም የአማቱን የምድያምን ካህን የዮቶርን በጎች ይጠብቅ ነበር፤ በጎቹንም ወደ ምድረ በዳ ዳርቻ ነዳ፤ ወደ እግዚአብሔርም ተራራ ወደ ኮሬብ መጣ። የእግዚአብሔርም መልአክ ለሙሴ በእሳት ነበልባል በቍጥቋጦ መካከል ታየው፤ እነሆም፥ ቍጥቋጦው በእሳት ሲነድድ፥ ቍጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ። ሙሴም፥ “ልሂድና ቍጥቋጦው ስለምን አልተቃጠለም? ይህን ታላቅ ራእይ ልይ” አለ። እግዚአብሔር እርሱ ይመለከት ዘንድ እንደ መጣ በአየ ጊዜ እግዚአብሔር ከቍጥቋጦው ውስጥ እርሱን ጠርቶ፥ “ሙሴ! ሙሴ!” አለው እርሱም፥ “ይህ ምንድን ነው?” አለ። “ወደዚህ አትቅረብ፤ አንተ የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና፥ ጫማህን ከእግርህ አውጣ” አለው። ደግሞም፥ “እኔ የአባቶችህ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ ነኝ” አለው። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ያይ ዘንድ ፈርቶአልና ፊቱን መለሰ። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “በግብፅ ያለውን የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ፦ ከአሠሪዎቻቸውም የተነሣ ጩኸታቸውን ሰማሁ፤ ሥቃያቸውንም ዐውቄአለሁ፤ ከግብፃውያንም እጅ አድናቸው ዘንድ፥ ከዚያችም ሀገር ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ሀገር፥ ወደ ሰፊዪቱና ወደ መልካሚቱ ሀገር፥ ወደ ከነዓናውያንም፥ ወደ ኬጤዎናውያንም፥ ወደ አሞሬዎናውያንም፥ ወደ ፌርዜዎናውያንም፥ ወደ ጌርጌሴዎናውያንም፥ ወደ ኤዌዎናውያንም፥ ወደ ኢያቡሴዎናውያንም ስፍራ አወጣቸው ዘንድ ወረድሁ። አሁንም እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ደረሰ፤ ግብፃውያንም የሚያደርጉባቸውን ግፍ ደግሞ አየሁ። አሁንም ና፤ ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ። ሕዝቤን የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ምድር ታወጣቸዋለህ።” ሙሴም እግዚአብሔርን፥ “ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ፈርዖን እሄድ ዘንድ፥ የእስራኤልንም ልጆች ከግብፅ ምድር አወጣ ዘንድ እኔ ማን ነኝ?” አለው። እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው፤ እንዲህ ሲል፥ “በእውነት እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እኔም እንደ ላክሁህ ይህ ለአንተ ምልክት ይሆንሃል፤ ሕዝቡን ከግብፅ በአወጣህ ጊዜ በዚህ ተራራ ላይ እግዚአብሔርን ታመልካላችሁ” አለው። ሙሴም እግዚአብሔርን፥ “እነሆ፥ እኔ ወደ እስራኤል ልጆች እሄዳለሁ፤ የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ እላቸዋለሁ፤ ‘ስሙስ ማን ነው?’ ብለው በጠየቁኝ ጊዜ ምን እላቸዋለሁ?” አለው። እግዚአብሔርም ለሙሴ ነገረው፤ እንዲህ ሲል፥ “ያለና የሚኖር እኔ ነኝ፤ እንዲህ ለእስራኤል ‘ያለና የሚኖር’ ወደ እናንተ ላከኝ ትላቸዋለህ” አለው።
ኦሪት ዘፀአት 3 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፀአት 3:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos