መጽሐፈ መክብብ 8
8
1ጥበበኛን የሚመስለው ማነው? የነገሮችን ፍቺ የሚያውቅ ማነው? ጥበብ የሰውን ፊት ታበራለች፤ ኰስታራነትንም ትለውጣለች።
ለንጉሥ ስለ መታዘዝ
2ለንጉሡ እታዘዛለሁ ብለህ በመሐላ ለእግዚአብሔር ቃል ስለ ገባህ ለንጉሥ ታማኝ ሁን። 3ንጉሥ የፈለገውን ማድረግ ስለሚችል ክፉ ዓላማን በመደገፍ አትጽና፤ ከንጉሡም ፊት ለመራቅ አትቸኲል። 4ንጉሥ ሁሉን ነገር ለማድረግ ሥልጣን አለው፤ “ለምን ይህን ሠራህ?” ብሎ የሚጠይቀውስ ማን አለ? 5ትእዛዙን ብትፈጽም ጒዳት አይደርስብህም፤ ይህ ሁሉ የሚፈጸምበትን ጊዜና ሁኔታ ለይቶ የሚያውቅ ጥበበኛ ብቻ ነው። 6ሕይወት አስቸጋሪ ቢሆንም ለሁሉም ነገር ጊዜና ቦታ አለው። 7ወደፊት የሚሆነውን ነገር ለይቶ የሚያውቅ ሰው የለም፤ “ይህ ይሆናል” ብሎ የሚነግረውስ ማነው? 8የሕይወትን እስትንፋስ ለማስቀረትና የሞትን ቀን ለመለወጥ የሚችል ማንም የለም፤ ማንም ሰው ከጦር ሜዳ መሰናበት እንደማይችል ክፋትም ክፉ ሠሪዎችን አይለቃቸውም።
የክፉና የደግ ሰው ሁኔታ
9በዚህ ዓለም የሚካሄደውን ሁናቴ በጥሞና ስመለከት ይህን ሁሉ አስተዋልኩ፤ አንድ ሰው ሌላውን ሰው ለመጒዳት ሥልጣን የሚኖረው ለምንድን ነው? 10ክፉዎች በክብር ሲቀበሩ አየሁ፤ የእግዚአብሔር ሰዎች ግን ከቅድስቲቱ ከተማ ወጥተው በመሄድ ተረሱ፤ ይህ ሁሉ ከንቱ ነው።
11ሰዎች ሆን ብለው ወንጀል የሚሠሩት ለምንድን ነው? የዚህ ምክንያት ሌላ ሳይሆን ወንጀል በሚሠሩ ሰዎች ላይ ፈጣን የቅጣት ፍርድ ባለመሰጠቱ ነው። 12ይኸውም ኃጢአተኞች መቶ ጊዜ ወንጀል ቢሠሩም ለረጅም ዘመን ይኖራሉ፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔርን ለሚፈሩና ለሚያከብሩ ሁሉ ነገር እንደሚሰምርላቸው ዐውቃለሁ። 13ክፉ ሰዎች ግን ምንም ነገር አይሰምርላቸውም፤ እግዚአብሔርንም ስለማይፈሩ ሕይወታቸው እንደ ጥላ ያልፋል፤ 14በምድር ላይ የሚደረግ ከንቱ ነገር አለ፤ አንዳንድ ጊዜ ደጋግ ሰዎች ለክፉ ሰዎች የሚገባውን ቅጣት ይቀበላሉ፤ ክፉ ሰዎች ደግሞ ለደጋግ ሰዎች የሚገባውን ዋጋ ያገኛሉ፤ ይህም ሁሉ ከንቱ ነው አልኩ።
15ስለዚህ ሰው በዚህ ዓለም ሲኖር የተሰጠው ዕድል ፈንታ መብላት፥ መጠጣትና ራሱን ማስደሰት መሆኑን አረጋገጥኩ፤ እግዚአብሔር በዚህ ዓለም በሰጠው ዘመን፥ ሰው ሁሉ ሠርቶ ያገኘውን ሀብት በዚህ ዐይነት ይደሰትበታል።
16ጥበበኛ ለመሆንና በዚህ ዓለም የሚደረገውንም ነገር ሁሉ መርምሬ ለማወቅ በሞከርኩ መጠን ሰው ሌት ከቀን ዕረፍት አጥቶ እንደሚኖር ተረዳሁ። 17ሰው በምርምር ብዛትም እግዚአብሔር የሚያደርገውን ነገር ሁሉ ማወቅ እንደማይችል አረጋገጥኩ፤ ሰው ብዙ ነገር መርምሮ ለማወቅ የቱንም ያኽል ቢደክም አንዳች ነገር ማግኘት አይችልም፤ በእርግጥ ጥበበኞች ሰዎች “ይህንን እናውቃለን” ለማለት ይደፍሩ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ የሚያውቁት ነገር የለም።
Currently Selected:
መጽሐፈ መክብብ 8: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997