የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መክብብ 9

9
1ስለ ነዚህ ሁሉ ነገሮች ለረጅም ጊዜ በብርቱ ካሰብኩ በኋላ የደጋግና የጥበበኞች ሰዎችን ሥራ በእግዚአብሔር እጅ እንደ ሆነ ተረዳሁ፤ ስለዚህ ወደፊት የሚገጥመውን ነገር ፍቅርም ሆነ ጥላቻ አስቀድሞ የሚያውቅ ሰው የለም። 2ምንም ዐይነት ልዩነት ሳይደረግ ለጻድቅና ለኃጢአተኛ ለደግና ለክፉ፥ ለንጹሓንና ንጹሓን ላልሆኑ መሥዋዕት ለሚያቀርቡትና ለማያቀርቡትም የሚገጥማቸው ዕድል አንድ ዐይነት ነው፤ ይኸውም ደጉ ሰው ከኃጢአተኛው የተሻለ ዕድል የለውም፤ መሐላን የሚፈራው መሐላን ከሚደፍረው ሰው ተለይቶ አይታይም። 3የሁሉም ዕድል ፈንታው አንድ ዐይነት ነው፤ ይህም በዓለም እንደሚደረገው እንደማንኛውም ነገር ሁሉ እጅግ የከፋ ነው፤ ሰዎችም በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ አእምሮአቸው በክፋትና በእብደት የተሞላ ሆኖ በመጨረሻ ይሞታሉ። 4ከሞተ አንበሳ ይልቅ በሕይወት ያለ ውሻ ይሻላል፤ በሕያዋን ምድር የሚኖር ሰው የተሻለ ተስፋ አለው፤ 5በሕይወት ያሉ ሰዎች አንድ ቀን እንደሚሞቱ ያውቃሉ፤ ሙታን ግን አንዳች ነገር አያውቁም፤ ፈጽሞ የተረሱ በመሆናቸውም ዋጋ የላቸውም። 6ፍቅራቸው፥ ጥላቻቸውና ቅናታቸው ሁሉ ከእነርሱ ጋር አብሮ ሞቶአል፤ በዚህ ዓለም በሚሆነው ነገር ሁሉ እንደገና እስከ ዘለዓለም ተካፋይነት አይኖራቸውም።
7እግዚአብሔር ቀድሞ የፈቀደልህ ይህ በመሆኑ ሂድ፤ ምግብህን ተመግበህ፥ የወይን ጠጅህንም ጠጥተህ በመርካትህ ደስ ይበልህ። 8ሁልጊዜ ነጭ ልብስ ለብሰህ ጠጒርህን ተቀባ። 9በዚህ ዓለም እግዚአብሔር በሰጠህ ከንቱ በሆነ ኑሮህ ከምትወዳት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ፤ ስለ መከራህና ስለ ድካምህ ሁሉ ዋጋ ሆኖ የተሰጠህ ዕድል ፈንታ ይኸው ብቻ ስለ ሆነ ከንቱ ዘመንህን፥ እያንዳንዱን ቀን ተደሰትበት። 10ባለህ ኀይል ሥራህን ሁሉ በትጋት ፈጽም፤ ወደ ሙታን ዓለም ከወረድህ በኋላ በዚያ ሥራና ሐሳብ፥ ዕውቀትና ጥበብ የለም።
11በዚህ ዓለም የተመለከትኩት ሌላም ነገር አለ፤ ይኸውም ፈጣን ሯጮች በአሸናፊነት አይወጡም፤ ጀግኖችም በጦርነት ድል አያደርጉም፤ ጠቢባን የዕለት እንጀራን፥ ብልኆች ሀብትን አያገኙም፤ ችሎታ ያላቸውም ሰዎች በማዕርግ አያድጉም፤ ነገር ግን ሁሉንም ጊዜና ዕድል ያጋጥማቸዋል፤ 12ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ሰው ይህ መጥፎ ዕድል መቼ እንደሚገጥመው አያውቅም፤ ወፍ በራ በወጥመድ ውስጥ እንደምትገባ፥ ዓሣም በመጥፎ አጋጣሚ በመረብ እንደሚያዝ እንዲሁም የሰው ልጅ ሁሉ ሳያስበው ድንገት በሚደርስበት በክፉ አጋጣሚ ይጠመዳል።
የጥበብ ልዕልና
13በዚህ ዓለም የተመለከትኩት ሌላም ነገር ደግሞ አለ፤ ይኸውም የጥበብ ታላቅ ምሳሌነት ነው። 14ጥቂት ሕዝብ የሚኖርባት አንዲት ትንሽ ከተማ ነበረች፤ አንድ ኀይለኛ ንጉሥ አደጋ ሊጥልባት ተነሣ፤ ትልቅ ምሽግ ሠርቶም ከበባት። 15በዚያች ከተማ የሚኖር ጥበበኛ የሆነ አንድ ድኻ ሰው ከተማይቱን በጥበቡ አዳናት፤ ይሁን እንጂ ያንን ድኻ ማንም አላስታወሰውም። 16ጥበብ ከኀይል እንደሚበልጥ ተናግሬአለሁ፤ ነገር ግን የድኻ ሰው ጥበብ የተናቀ ነው፤ ለንግግሩም ዋጋ የሚሰጠው የለም። 17በሞኞች ጉባኤ ከሚሰማው የአገረ ገዥ የጩኸት ድምፅ ይልቅ በዝግታ የሚነገር የጥበበኛ ቃል ይሻላል። 18ከጦር መሣሪያ ይልቅ ጥበብ ትሻላለች፤ ነገር ግን አንድ ኃጢአተኛ ብዙ መልካም ነገርን ያጠፋል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ