ኦሪት ዘዳግም 30:3-10

ኦሪት ዘዳግም 30:3-10 አማ05

አምላክህ እግዚአብሔር ምሕረት ያደርግልሃል፤ በአሕዛብ መካከል አንተን ከበታተነበት ስፍራ ሁሉ መልሶ በማምጣት እንደገና ያበለጽግሃል። እስከ ምድር ዳርቻ ተበታትነህ የምትኖር ብትሆን እንኳ አምላክህ እግዚአብሔር በአንድነት በመሰብሰብ መልሶ ያመጣሃል፤ በዚህም ዐይነት የቀድሞ አባቶችህ የነበሩበትን ምድር እንደገና ትወርሳለህ፤ እርሱም ከቀድሞ አባቶችህ ይበልጥ ባለጸጋና ቊጥርህ የበዛ እንድትሆን ያደርጋል። አምላክህ እግዚአብሔር ለአንተና ለልጆችህ ታዛዥ ልብ ይሰጣል፤ ስለዚህም እርሱን በፍጹም ልብህ ትወደዋለህ፤ በዚያችም ምድር በሕይወት ትኖራለህ። እነዚህንም መርገሞች ሁሉ አንተን በሚጠሉህና በሚጨቊኑህ ጠላቶችህ ላይ ይመልስባቸዋል፤ አንተም እንደገና ለእርሱ ታዛዥ ትሆናለህ፤ ዛሬ እኔ የምሰጥህንም የእርሱን ትእዛዞች ትጠብቃለህ፤ በምትሠራው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ያበለጽግሃል፤ ልጆችህን፤ እንስሶችህንና የምድርህን ሰብልና ፍሬ ያበዛልሃል፤ እግዚአብሔር የቀድሞ አባቶችህን በማበልጸግ ደስ ይለው እንደ ነበር አንተንም በማበልጸግ ደስ ይለዋል። ይህንንም የሚያደርገው በዚህ የሕግ መጽሐፍ ውስጥ የተጻፉትን ትእዛዞችና ሕጎች በመጠበቅ በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር የተመለስክ እንደ ሆነ ነው።