ዘዳግም 30:3-10

ዘዳግም 30:3-10 NASV

አምላክህ እግዚአብሔር ምርኮህን ይመልስልሃል፤ ይራራልሃልም፤ አንተን ከበተነበት አሕዛብ መካከልም እንደ ገና ይሰበስብሃል። ከሰማይ በታች እጅግ ሩቅ ወደ ሆነ ምድር ብትጋዝ እንኳ፣ አምላክህ እግዚአብሔር ከዚያ ይሰበስብሃል፤ መልሶም ያመጣሃል። አምላክህን እግዚአብሔር የአባቶችህ ወደሆነችው ምድር ያመጣሃል፤ አንተም ትወርሳታለህ። ከአባቶችህ ይበልጥ ያበለጽግሃል፤ ያበዛሃልም። አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ እንድትወድደው፣ በሕይወትም እንድትኖር፣ አምላክህ እግዚአብሔር የአንተንና የዘርህን ልብ ይገርዛል። አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ርግማን ሁሉ በሚጠሉህና በሚያሳድዱህ ጠላቶችህ ላይ ያደርገዋል። አንተም ተመልሰህ ለእግዚአብሔር ትታዘዛለህ፤ ዛሬ እኔ የማዝዝህን ትእዛዝ ሁሉ ትጠብቃለህ። ከዚያም አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ ሥራ ሁሉና በወገብህ ፍሬ፣ በእንስሳትህ ግልገሎችና በምድርህ ሰብል እጅግ ያበለጽግሃል። በአባቶችህ ደስ እንደ ተሠኘ ሁሉ፣ እግዚአብሔር አንተንም በማበልጸግ ደስ ይለዋልና። ይህም የሚሆነው፣ አምላክህን እግዚአብሔርን ከታዘዝህና በዚህ የሕግ መጽሐፍ የተጻፉትን ትእዛዙንና ሥርዐቱን በመጠበቅ፣ በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ስትመለስ ነው።