ዘዳግም 30:3-10
ዘዳግም 30:3-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ኀጢአትህን ይቅር ይልሃል ይራራልህማል፤ እግዚአብሔርም አንተን ከበተነበት ከአሕዛብ ሁሉ መካከል መልሶ ይሰበስብሃል። መበተንህም እስከ ሰማይ ዳርቻ ቢሆን አምላክህ እግዚአብሔር ከዚያ ይሰበስብሃል፤ ከዚያም ያመጣሃል። አባቶችህም ወደ ወረሱአት ምድር አምላክህ እግዚአብሔር ይወስድሃል፤ ትወርሳትማለህ፤ መልካምም ነገር ያደርግልሃል፤ ከአባቶችህም ይልቅ ያበዛሃል። በሕይወትም እንድትኖር፥ አምላክህን እግዚአብሔርንም በፍጹም ልብህ፥ በፍጹምም ነፍስህ እንድትወድድ እግዚአብሔር ልብህን፥ የዘርህንም ልብ ያጠራዋል። አምላክህም እግዚአብሔር ይህችን መርገም ሁሉ በጠላቶችህና በሚጠሉህ በሚያሳድዱህም ላይ ያመጣታል። አንተም ተመልሰህ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ትሰማለህ፤ ዛሬም እኔ የማዝዝህን ትእዛዙን ሁሉ ታደርጋለህ። እግዚአብሔርም በአባቶችህ ደስ እንዳለው በመልካሙ ነገር ሁሉ እንደ ገና በአንተ ደስ ይለዋልና አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ ሥራ ሁሉ፥ በሆድህም ፍሬ፥ በእርሻህም ፍሬ፥ በከብትህም ብዛት እጅግ ይባርክሃል። በዚህ የሕግ መጽሐፍ የተጻፉትን ትእዛዙን፥ ሥርዐቱንና ፍርዱን ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ፥ በፍጹም ልብህ፥ በፍጹምም ነፍስህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ብትመለስ ይባርክሃል።
ዘዳግም 30:3-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አምላክህ እግዚአብሔር ምርኮህን ይመልስልሃል፤ ይራራልሃልም፤ አንተን ከበተነበት አሕዛብ መካከልም እንደ ገና ይሰበስብሃል። ከሰማይ በታች እጅግ ሩቅ ወደ ሆነ ምድር ብትጋዝ እንኳ፣ አምላክህ እግዚአብሔር ከዚያ ይሰበስብሃል፤ መልሶም ያመጣሃል። አምላክህን እግዚአብሔር የአባቶችህ ወደሆነችው ምድር ያመጣሃል፤ አንተም ትወርሳታለህ። ከአባቶችህ ይበልጥ ያበለጽግሃል፤ ያበዛሃልም። አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ እንድትወድደው፣ በሕይወትም እንድትኖር፣ አምላክህ እግዚአብሔር የአንተንና የዘርህን ልብ ይገርዛል። አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ርግማን ሁሉ በሚጠሉህና በሚያሳድዱህ ጠላቶችህ ላይ ያደርገዋል። አንተም ተመልሰህ ለእግዚአብሔር ትታዘዛለህ፤ ዛሬ እኔ የማዝዝህን ትእዛዝ ሁሉ ትጠብቃለህ። ከዚያም አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ ሥራ ሁሉና በወገብህ ፍሬ፣ በእንስሳትህ ግልገሎችና በምድርህ ሰብል እጅግ ያበለጽግሃል። በአባቶችህ ደስ እንደ ተሠኘ ሁሉ፣ እግዚአብሔር አንተንም በማበልጸግ ደስ ይለዋልና። ይህም የሚሆነው፣ አምላክህን እግዚአብሔርን ከታዘዝህና በዚህ የሕግ መጽሐፍ የተጻፉትን ትእዛዙንና ሥርዐቱን በመጠበቅ፣ በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ስትመለስ ነው።
ዘዳግም 30:3-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አምላክህ እግዚአብሔር ምርኮህን ይመልሳል ይራራልህማል፤ አምላክህም እግዚአብሔር አንተን ከበተነበት ከአሕዛብ ሁሉ መካከል መልሶ ይሰበስብሃል። ሰዎችህም እስከ ሰማይ ዳርቻ ድረስ ፈልሰው እንደ ሆነ አምላክህ እግዚአብሔር ከዚያ ይሰበስብሃል፥ ከዚያም ያመጣሃል። አባቶችህም ወደ ወረሱአት ምድር አምላክህ እግዚአብሔር ያጋባሃል፥ ትወርሳትማለህ፤ መልካምም ያደርግልሃል፥ ከአባቶችህም ይልቅ ያበዛሃል። በሕይወትም እንድትኖር፥ አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ እንድትወድድ አምላክህ እግዚአብሔር ልብህን የዘርህንም ልብ ይገርዛል። አምላክህም እግዚአብሔር ይህችን መርገም ሁሉ በጠላቶችህና በሚጠሉህ በሚያሳድዱህም ላይ ያመጣታል። አንተም ተመልሰህ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ትሰማለህ፥ ዛሬም እኔ የማዝዝህን ትእዛዙን ሁሉ ታደርጋለህ የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ፥ በዚህም ሕግ መጽሐፍ የተጻፉትን ትእዛዙንና ሥርዓቱን ብትጠብቅ፥ በፍጹምም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ብትመለስ፥ እግዚአብሔር በአባቶችህ ደስ እንዳለው በመልካሙ ነገር ሁሉ እንደ ገና በአንተ ደስ ይለዋልና አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ ሥራ ሁሉ በሆድህም ፍሬ በከብትህም ፍሬ በእርሻህም ፍሬ እጅግ ይባርክሃል።
ዘዳግም 30:3-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አምላክህ እግዚአብሔር ምሕረት ያደርግልሃል፤ በአሕዛብ መካከል አንተን ከበታተነበት ስፍራ ሁሉ መልሶ በማምጣት እንደገና ያበለጽግሃል። እስከ ምድር ዳርቻ ተበታትነህ የምትኖር ብትሆን እንኳ አምላክህ እግዚአብሔር በአንድነት በመሰብሰብ መልሶ ያመጣሃል፤ በዚህም ዐይነት የቀድሞ አባቶችህ የነበሩበትን ምድር እንደገና ትወርሳለህ፤ እርሱም ከቀድሞ አባቶችህ ይበልጥ ባለጸጋና ቊጥርህ የበዛ እንድትሆን ያደርጋል። አምላክህ እግዚአብሔር ለአንተና ለልጆችህ ታዛዥ ልብ ይሰጣል፤ ስለዚህም እርሱን በፍጹም ልብህ ትወደዋለህ፤ በዚያችም ምድር በሕይወት ትኖራለህ። እነዚህንም መርገሞች ሁሉ አንተን በሚጠሉህና በሚጨቊኑህ ጠላቶችህ ላይ ይመልስባቸዋል፤ አንተም እንደገና ለእርሱ ታዛዥ ትሆናለህ፤ ዛሬ እኔ የምሰጥህንም የእርሱን ትእዛዞች ትጠብቃለህ፤ በምትሠራው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ያበለጽግሃል፤ ልጆችህን፤ እንስሶችህንና የምድርህን ሰብልና ፍሬ ያበዛልሃል፤ እግዚአብሔር የቀድሞ አባቶችህን በማበልጸግ ደስ ይለው እንደ ነበር አንተንም በማበልጸግ ደስ ይለዋል። ይህንንም የሚያደርገው በዚህ የሕግ መጽሐፍ ውስጥ የተጻፉትን ትእዛዞችና ሕጎች በመጠበቅ በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር የተመለስክ እንደ ሆነ ነው።
ዘዳግም 30:3-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታ አምላክህ ምርኮህን ይመልስልሃል፤ ይራራልሃልም፤ አንተን ከበተነበት አሕዛብ መካከል ጌታ እግዚአብሔር እንደገና ይሰበስብሃል። የፈለስክበት ስፍራ ከሰማይ በታች እጅግ ሩቅ ወደ ሆነ ምድር ቢሆን እንኳ፥ ጌታ እግዚአብሔር ከዚያ ይሰበስብሃል፤ ከዚያም መልሶ ያመጣሃል። የአባቶችህ ወደ ሆነችው ምድር ያመጣሃል፤ አንተም ትወርሳታለህ። ከአባቶችህ ይበልጥ ያበለጽግሃል፤ ያበዛሃልም። ጌታ እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ እንድትወደው፥ በሕይወትም እንድትኖር፥ አምላክህ ጌታ የአንተንና የዘርህን ልብ ይገርዛል። ጌታ አምላክህም ይህን ርግማን ሁሉ በጠላቶችህና በሚጠሉህ በሚያሳድዱህም ላይ ያደርገዋል። አንተም ተመልሰህ ለጌታ ቃል ትታዘዛለህ፤ ዛሬ እኔ የማዝህንም ትእዛዝ ሁሉ ታደርጋለህ። ጌታ በአባቶችህ ደስ እንዳለው በመልካሙ ነገር ሁሉ እንደገና በአንተ ደስ ይለዋልና፥ ጌታ እግዚአብሔር በእጅህ ሥራ ሁሉ፥ በሆድህም ፍሬ፥ እንዲሁም በከብትህም ፍሬ፥ በእርሻህም ፍሬ እጅግ ያበለጽግሃል። የጌታ እግዚአብሔርን ቃል ከሰማህ፥ በዚህ የሕግ መጽሐፍ የተጻፉትን ትእዛዙንና ሥርዓቱን ለመጠበቅ፥ በፍጹምም ልብህና በፍጹም ነፍስህ ወደ ጌታ ወደ አምላክህ ተመለስ።