ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3
3
በክርስቶስ አዲስ ሕይወት
1እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከሞት ከተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ በሰማይ ያሉትን ነገሮች ፈልጉ። #መዝ. 110፥1። 2ዘወትር በላይ በሰማይ ስላሉት ነገሮች አስቡ እንጂ በምድር ላይ ስላሉት ነገሮች አታስቡ። 3እናንተ በሞት የመለየትን ያኽል ከዚህ ዓለም ተለይታችኋል፤ ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ውስጥ ተሰውሮአል። 4ሕይወታችሁ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ እናንተም ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ።
አሮጌውና አዲሱ ሕይወት
5ስለዚህ በእናንተ የሚገኙትን የምድራዊ ሕይወት ምኞቶች ሁሉ ግደሉ፤ እነርሱም “ዝሙት፥ ርኲሰት፥ ፍትወት፥ ክፉ ምኞት፥ ጣዖት ማምለክ የሆነ መጐምጀት” ናቸው። 6በእነዚህ ነገሮች ምክንያት በማይታዘዙ ሰዎች ላይ የእግዚአብሔር ቊጣ ይመጣል። 7እናንተም ራሳችሁ ከዚህ በፊት በማይታዘዙ ሰዎች መካከል ሳላችሁ እነዚህን ነገሮች በማድረግ ትኖሩ ነበር።
8አሁን ግን ቊጣን፥ ንዴትን፥ ተንኰልን፥ ስም ማጥፋትን ከእናንተ አስወግዱ፤ የሚያሳፍር ንግግርም ከአፋችሁ አይውጣ። 9አሮጌውን ባሕርይ ከነሥራው አውልቃችሁ ስለ ጣላችሁት እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ። #ኤፌ. 4፥22። 10በፈጣሪው አምሳል በዕውቀት እየታደሰ የሚሄደውን አዲሱን ባሕርይ ልበሱ። #ዘፍ. 1፥26፤ ኤፌ. 4፥24። 11በዚህ ሁኔታ በግሪካዊና በአይሁዳዊ፥ በተገረዘና ባልተገረዘ፥ በሠለጠነ አረመኔና ባልሠለጠነ አረመኔ፥ ነጻነት በሌለውና ነጻነት ባለው ሰው መካከል ልዩነት የለም፤ ክርስቶስ ሁሉም ነው፤ በሁሉም ነው።
12እንግዲህ የእግዚአብሔር ምርጦችና ቅዱሳን፥ የተወደዳችሁም እንደ መሆናችሁ መጠን ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትሕትናን፥ ገርነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ። #ኤፌ. 4፥2። 13እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ይቅር በሉ። #ኤፌ. 4፥32። 14ከዚህም ሁሉ በላይ ሁሉን ነገር ሰብስቦ በማሰር ፍጹም አንድነትን የሚያስገኘውን ፍቅርን ልበሱ። 15የአንድ አካል ክፍሎች ሆናችሁ በእርግጥ የተጠራችሁት ለዚህ ሰላም ስለ ሆነ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይንገሥ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። 16የክርስቶስ ቃል በሙላት በልባችሁ ይኑር፤ በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በውዳሴ፥ በመንፈሳዊ ዜማም እግዚአብሔርን ከልብ እያመሰገናችሁ ዘምሩ። 17በኢየሱስ በኩል እግዚአብሔር አብን እያመሰገናችሁ በቃልም ሆነ በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት፤ በእርሱም እግዚአብሔር አብን አመስግኑ። #ኤፌ. 5፥19-20።
የክርስቲያን ቤተሰብ የኑሮ ሥርዓት
18ሚስቶች ሆይ! በጌታ ዘንድ ተገቢ ስለ ሆነ ለባሎቻችሁ ታዘዙ። #ኤፌ. 5፥22፤ 1ጴጥ. 3፥1።
19ባሎች ሆይ! ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ ጨካኞችም አትሁኑባቸው። #ኤፌ. 5፥25፤ 1ጴጥ. 3፥7።
20ልጆች ሆይ! ይህ ጌታን ደስ የሚያሰኝ ስለ ሆነ በሁሉ ነገር ለወላጆቻችሁ ታዘዙ። #ኤፌ. 6፥1።
21ወላጆች ሆይ! ተስፋ እንዳይቈርጡ ልጆቻችሁን በቊጣ አታበሳጩአቸው። #ኤፌ. 6፥4።
22በባርነት ሥርዓት ያላችሁ! ለምድራዊ ጌቶቻችሁ በሁሉም ነገር ታዘዙ፤ የምትታዘዙትም እነርሱ ስለሚያዩአችሁና ሰውን ደስ ስለምታሰኙ ለታይታ ሳይሆን ጌታን በመፍራትና በልብ ቅንነት ይሁን። #ኤፌ. 6፥5-8። 23የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለጌታ ኢየሱስ እንደምታደርጉት ዐይነት ከልባችሁ አድርጉት። 24ለዚህም ጌታ ሰማያዊ ርስትን ዋጋ አድርጎ እንደሚሰጣችሁ ታውቃላችሁ፤ የምታገለግሉትም ጌታ ክርስቶስን ነው፤ 25በእግዚአብሔር ዘንድ አድልዎ ስለሌለ ክፉ የሚሠራም ስለ ክፉ ሥራው ቅጣቱን ይቀበላል። #ዘዳ. 10፥17፤ ኤፌ. 6፥9።
Currently Selected:
ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997