ወደ ቆላስይስ ሰዎች 4
4
1ጌቶች ሆይ! እናንተም በሰማይ ጌታ እንዳላችሁ ዐውቃችሁ አገልጋዮቻችሁን በቅንነትና በእኩልነት አስተዳድሩአቸው። #ኤፌ. 6፥9።
ተጨማሪ ምክር
2እግዚአብሔርን ተግታችሁ በማመስገን ባለማቋረጥ ጸልዩ፤ 3ከዚህም ጋር እግዚአብሔር ለቃሉ በር እንዲከፍትልንና እኔ በእርሱ ምክንያት ታስሬ የምገኝበትን የክርስቶስን ምሥጢር ማብሠር እንድንችል ለእኛም ጸልዩ። 4እኔም እንደሚገባኝ ቃሉን በግልጥ እንድናገር ጸልዩልኝ።
5በማንኛውም አጋጣሚ ጊዜ እየተጠቀማችሁ በማያምኑት ሰዎች ዘንድ በጥበብ ኑሩ። #ኤፌ. 5፥16። 6ለእያንዳንዱ ሰው ተገቢውን መልስ መስጠት እንድታውቁ ዘወትር ንግግራችሁ ለዛና ጣዕም ያለው ይሁን።
የመጨረሻ ሰላምታ
7ቲኪቆስ ስለ እኔ ጉዳይ ሁሉንም ነገር ይነግራችኋል፤ እርሱ ተወዳጅ ወንድም፥ ታማኝ አገልጋይና በጌታ ሥራም የአገልግሎት ጓደኛዬ ነው። #ሐ.ሥ. 20፥4፤ 2ጢሞ. 4፥12። 8እርሱን ወደ እናንተ የላክሁበት ምክንያት ስለ እኛ ሁኔታ እንዲነግራችሁና ልባችሁንም እንዲያጽናና ነው። #ኤፌ. 6፥21-22። 9ከእርሱም ጋር የእናንተ ወገን የሆነው የታመነውና የተወደደው ወንድም ኦኔሲሞስ ወደ እናንተ ይመጣል፤ እነርሱ በዚህ ስፍራ ስላለው ነገር ሁሉ ያስታውቋችኋል።
10ከእኔ ጋር የታሰረው አርስጥሮኮስም ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ አንድ ጊዜ፥ “ወደ እናንተ በሚመጣበት ጊዜ እንድትቀበሉት” ብዬ አሳስቤአችሁ የነበረው የበርናባስ የአጐቱ ልጅ ማርቆስም ሰላምታ ያቀርብላችኋል። #ሐ.ሥ. 19፥29፤ 27፥2፤ ፊልሞና 24፤ ሐ.ሥ. 12፥12፤25፤ 13፥13፤ 15፥37-39። 11ኢዮስጦስ ተብሎም የሚጠራው ኢያሱ ሰላምታ ያቀርብላችኋል። ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ከእኔ ጋር አብረው ከሚሠሩት ሰዎች መካከል የአይሁድ ወገኖች የሆኑት እነዚህ ብቻ ናቸው፤ እኔንም አጽናንተውኛል።
12የእናንተ ወገን የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ኤጳፍራም ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ በመንፈሳዊ ሕይወት በማደግ ጸንታችሁ እንድትቆሙና የእግዚአብሔርንም ፈቃድ በሙሉ እንድትፈጽሙ እርሱ ስለ እናንተ በጸሎቱ ዘወትር ይጸልያል። #ቆላ. 1፥7፤ ፊልሞና 23። 13ስለ እናንተ በሎዶቅያና በሂራፖሊስ ከተሞች ስላሉትም ሰዎች በጣም እንደሚደክም እኔ ራሴ እመሰክርለታለሁ። 14የተወደደው ሐኪም ሉቃስና ዴማስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። #2ጢሞ. 4፥10-11፤ ፊልሞና 24። 15በሎዶቅያ ላሉት ወንድሞች ለንምፉና በቤትዋም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ። #4፥15 ለንምፉና በቤትዋም ላለች፦ አንዳንድ ቅጂዎች “ለኒምፉስና በቤቱም ላለች” ይላሉ። 16ይህችን መልእክት እናንተ ካነበባችኋት በኋላ በሎዶቅያ ሰዎች ዘንድ ባለችው ቤተ ክርስቲያን እንድትነበብ አድርጉ፤ እናንተም ከሎዶቅያ የሚላክላችሁን መልእክት አንብቡ። 17ለአርኪጳስም “በጌታ አገልግሎት የተሰጠህን ሥራ በጥንቃቄ እንድትፈጽም” ብላችሁ ንገሩልኝ። #ፊልሞና 2።
18ይህን ሰላምታ በገዛ እጄ የጻፍኩት እኔ ጳውሎስ ነኝ፤ በሰንሰለት ታስሬ እንዳለሁ አስታውሱ።
የእግዚአብሔር ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።
Currently Selected:
ወደ ቆላስይስ ሰዎች 4: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997