የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሐዋርያት ሥራ 10:1-20

የሐዋርያት ሥራ 10:1-20 አማ05

በቂሳርያ የሚኖር ቆርኔሌዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም በሮማውያን ጦር ሠራዊት ሥር “የኢጣልያ ብርጌድ” በሚባለው ውስጥ የመቶ አለቃ ነበር። እርሱ ከቤተ ሰቡ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ሰው ነበረ፤ ለድኾችም ብዙ ምጽዋት ይሰጥ ነበር፤ ወደ እግዚአብሔርም ዘወትር ይጸልይ ነበር። አንድ ቀን በዘጠኝ ሰዓት ገደማ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባና “ቆርኔሌዎስ!” ብሎ ሲጠራው በራእይ በግልጥ ታየው። ትኲር ብሎ ወደ መልአኩ ተመለከተና በመደንገጥ “ጌታ ሆይ! ምንድን ነው?” አለ። መልአኩም እንዲህ አለው፦ “ጸሎትህና ለድኾች የምታደርገው ምጽዋት መልካም መታሰቢያ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር ዐርጓል፤ አሁንም ሰዎችን ወደ ኢዮጴ ላክና ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስጠራ፤ እርሱ አሁን በባሕር አጠገብ በሚገኘው በቊርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት ተቀምጦአል።” ይህን የነገረው መልአክ ተለይቶት በሄደ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ከአገልጋዮቹ ሁለቱንና የእርሱ ክፍል ከሆኑት ወታደሮች እግዚአብሔርን የሚፈራውን አንዱን ጠራና፥ ሁሉንም ነገር ከነገራቸው በኋላ ወደ ኢዮጴ ላካቸው። በማግስቱ እነርሱ ሄደው ወደ ከተማው ሲቀርቡ ስድስት ሰዓት ገደማ ጴጥሮስ ወደነበረበት ቤት ሰገነት ሊጸልይ ወጣ። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ራበውና አንዳች ነገር መብላት ፈለገ፤ ምሳ በመዘጋጀት ላይ እንዳለም በተመስጦ ራእይ አየ። ያየውም ራእይ ሰማይ ተከፍቶ በአራት ማእዘን የተያዘ ትልቅ የመጋረጃ ጨርቅ የሚመስል ነገር ወደ ምድር ሲወርድ ነው። በዚያም ላይ ልዩ ልዩ እንስሳት በልባቸው የሚሳቡ ፍጥረቶችና በሰማይ የሚበርሩ ወፎች ነበሩበት። በዚያን ጊዜ “ጴጥሮስ ሆይ! ተነሥና እያረድክ ብላ!” የሚል ድምፅ ሰማ። ጴጥሮስ ግን “ጌታ ሆይ! አይሆንም! እኔ ንጹሕ ያልሆነ ወይም ርኩስ ነገር በልቼ አላውቅም” አለ። ደግሞም “እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ ርኩስ ነው ማለት አይገባህም” የሚል ድምፅ እንደገና ሰማ። ይህም ሦስት ጊዜ ከሆነ በኋላ ያ ጨርቅ የሚመስል ነገር ወዲያውኑ ወደ ሰማይ ተወሰደ። ጴጥሮስ የራእዩ ፍች “ምን ይሆን?” እያለ በሐሳቡ ሲጨነቅ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች በጥያቄ የስምዖንን ቤት አግኝተው በበር ቆመው ነበር፤ ተጣርተውም “ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን በእንግድነት የሚገኘው እዚህ ነውን?” ብለው ጠየቁ። ጴጥሮስ የራእዩን ነገር በማሰላሰል ላይ ሳለ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ አለው፦ “እነሆ! ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ተነሥና ውረድ፤ የላክኋቸው እኔ ስለ ሆንኩ ሳታመነታ ከእነርሱ ጋር ሂድ።”