የሐዋርያት ሥራ 10
10
ጴጥሮስና ቆርኔሌዎስ
1በቂሳርያ የሚኖር ቆርኔሌዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም በሮማውያን ጦር ሠራዊት ሥር “የኢጣልያ ብርጌድ” በሚባለው ውስጥ የመቶ አለቃ ነበር። 2እርሱ ከቤተ ሰቡ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ሰው ነበረ፤ ለድኾችም ብዙ ምጽዋት ይሰጥ ነበር፤ ወደ እግዚአብሔርም ዘወትር ይጸልይ ነበር። 3አንድ ቀን በዘጠኝ ሰዓት ገደማ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባና “ቆርኔሌዎስ!” ብሎ ሲጠራው በራእይ በግልጥ ታየው።
4ትኲር ብሎ ወደ መልአኩ ተመለከተና በመደንገጥ “ጌታ ሆይ! ምንድን ነው?” አለ።
መልአኩም እንዲህ አለው፦ “ጸሎትህና ለድኾች የምታደርገው ምጽዋት መልካም መታሰቢያ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር ዐርጓል፤ 5አሁንም ሰዎችን ወደ ኢዮጴ ላክና ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስጠራ፤ 6እርሱ አሁን በባሕር አጠገብ በሚገኘው በቊርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት ተቀምጦአል።” 7ይህን የነገረው መልአክ ተለይቶት በሄደ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ከአገልጋዮቹ ሁለቱንና የእርሱ ክፍል ከሆኑት ወታደሮች እግዚአብሔርን የሚፈራውን አንዱን ጠራና፥ 8ሁሉንም ነገር ከነገራቸው በኋላ ወደ ኢዮጴ ላካቸው።
9በማግስቱ እነርሱ ሄደው ወደ ከተማው ሲቀርቡ ስድስት ሰዓት ገደማ ጴጥሮስ ወደነበረበት ቤት ሰገነት ሊጸልይ ወጣ። 10በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ራበውና አንዳች ነገር መብላት ፈለገ፤ ምሳ በመዘጋጀት ላይ እንዳለም በተመስጦ ራእይ አየ። 11ያየውም ራእይ ሰማይ ተከፍቶ በአራት ማእዘን የተያዘ ትልቅ የመጋረጃ ጨርቅ የሚመስል ነገር ወደ ምድር ሲወርድ ነው። 12በዚያም ላይ ልዩ ልዩ እንስሳት በልባቸው የሚሳቡ ፍጥረቶችና በሰማይ የሚበርሩ ወፎች ነበሩበት። 13በዚያን ጊዜ “ጴጥሮስ ሆይ! ተነሥና እያረድክ ብላ!” የሚል ድምፅ ሰማ።
14ጴጥሮስ ግን “ጌታ ሆይ! አይሆንም! እኔ ንጹሕ ያልሆነ ወይም ርኩስ ነገር በልቼ አላውቅም” አለ።
15ደግሞም “እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ ርኩስ ነው ማለት አይገባህም” የሚል ድምፅ እንደገና ሰማ። 16ይህም ሦስት ጊዜ ከሆነ በኋላ ያ ጨርቅ የሚመስል ነገር ወዲያውኑ ወደ ሰማይ ተወሰደ።
17ጴጥሮስ የራእዩ ፍች “ምን ይሆን?” እያለ በሐሳቡ ሲጨነቅ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች በጥያቄ የስምዖንን ቤት አግኝተው በበር ቆመው ነበር፤ 18ተጣርተውም “ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን በእንግድነት የሚገኘው እዚህ ነውን?” ብለው ጠየቁ።
19ጴጥሮስ የራእዩን ነገር በማሰላሰል ላይ ሳለ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ አለው፦ “እነሆ! ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ 20ተነሥና ውረድ፤ የላክኋቸው እኔ ስለ ሆንኩ ሳታመነታ ከእነርሱ ጋር ሂድ።” 21ጴጥሮስም ወርዶ ወደ ሰዎቹ ሄደና “እነሆ፥ የምትፈልጉት ሰው እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበት ምክንያት ምንድን ነው?” አላቸው። 22እነርሱም “እኛ የመጣነው ከመቶ አለቃው ከቆርኔሌዎስ ዘንድ ነው፤ እርሱ የአይሁድ ሕዝብ ሁሉ የሚያከብረው እግዚአብሔርን የሚያመልክ ደግ ሰው ነው፤ አንተን ወደ ቤቱ አስጠርቶ የምትለውን እንዲሰማ ቅዱስ መልአክ ገልጦ ነግሮታል” አሉት። 23ጴጥሮስም ወደ ቤት አስገባቸውና አስተናገዳቸው፤ ለምኖም አሳደራቸው።
በማግስቱም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር ሄደ፤ በኢዮጴ ከነበሩት ወንድሞች አንዳንዶቹም አብረውት ሄዱ። 24በሁለተኛውም ቀን ወደ ቂሳርያ ደረሱ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ጠርቶ እነጴጥሮስን ይጠባበቅ ነበር። 25ጴጥሮስ ወደ ቤት ሲገባ ቆርኔሌዎስ ወደ እርሱ ቀረበና በእግሩ ሥር ወድቆ ሰገደለት። 26ጴጥሮስ ግን “ተነሥ! እኔም እንደ አንተ ሰው ነኝ!” ብሎ አስነሣው።
27እያነጋገረውም ወደ ውስጥ ሲገባ ብዙ ሰዎች ተሰብስበው አገኘ። 28እንዲህም አላቸው፦ “አይሁዳዊ ለሆነ ሰው ከሌላ ሕዝብ ጋር ለመተባበርና ወደ ቤቱም ለመግባት በሃይማኖታችን ሕግ እንደማይፈቀድ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን ማንንም ንጹሕ ያልሆነ ወይም ርኩስ እንዳልል እግዚአብሔር ገልጦልኛል። 29ስለዚህ በተላከብኝ ጊዜ ያለ አንዳች ተቃውሞ መጣሁ፤ እንግዲህ ለምን እንደ ጠራችሁኝ ማወቅ እፈልጋለሁ።”
30ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለ፦ “ከአራት ቀን በፊት ልክ በዚህ ጊዜ በዘጠኝ ሰዓት በቤቴ እጸልይ ነበር፤ እነሆ፥ በድንገት አንድ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሰ ሰው በፊቴ ቆመ፤ 31እንዲህም አለኝ፦ ‘ቆርኔሌዎስ ሆይ! እግዚአብሔር ጸሎትህን ሰምቶአል፤ ለድኾች የምታደርገውም ምጽዋት ታስቦልሃል፤ 32እንግዲህ ወደ ኢዮጴ መልእክተኛ ላክና ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስጠራ፤ እርሱ በባሕር አጠገብ በሚገኘው በቊርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት ተቀምጦአል፤’ 33ስለዚህ ወዲያውኑ መልእክተኞች ወደ አንተ ላክሁ፤ አንተም በመምጣትህ መልካም አድርገሃል፤ እንግዲህ እግዚአብሔር እንድትናገር ያዘዘህን ሁሉ ለመስማት እኛ ሁላችን በእግዚአብሔር ፊት እዚህ ተሰብስበናል።”
የጴጥሮስ ንግግር
34ጴጥሮስ እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ፦ “በእውነት እግዚአብሔር ሰውን ከሰው እንደማያበላልጥ አስተዋልኩ፤ #ዘዳ. 10፥17። 35የማንኛውም አገር ሰው ቢሆን እግዚአብሔርን የሚፈራና ትክክለኛውን ነገር የሚያደርግ ከሆነ እግዚአብሔር ይቀበለዋል። 36እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ቃሉን መላኩ የታወቀ ነው፤ በሁሉ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ሰላምን እየሰበከ የመጣውም ለእነርሱ ነው። 37ዮሐንስ ስለ ጥምቀት ከሰበከበት ጊዜ ጀምሮ ከገሊላ አንሥቶ በይሁዳ ምድር ሁሉ የሆነውን ነገር ታውቃላችሁ።
38“ደግሞም እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ እንደ ቀባውና ኀይልም እንደ ሰጠው ታውቃላችሁ፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ እርሱን መልካም ነገርን እያደረገና በዲያብሎስ የተያዙትን ሁሉ እየፈወሰ ተዘዋወረ።
39“በይሁዳ ገጠርና በኢየሩሳሌም ከተማ እርሱ ስላደረገው ነገር ሁሉ እኛ ምስክሮች ነን፤ እርሱን ግን በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት። 40ነገር ግን እግዚአብሔር በሦስተኛው ቀን ከሞት አስነሣውና እንዲገለጥ አደረገው። 41የተገለጠውም አስቀድሞ በእግዚአብሔር ለተመረጡት ምስክሮች ነው እንጂ ለሕዝቡ ሁሉ አይደለም፤ እርሱ ከሞት ከተነሣ በኋላ እኛ ከእርሱ ጋር አብረን የበላንና የጠጣን ምስክሮቹ ነን፤ 42ይህን ነገር ለሕዝቡ እንድናበሥር እርሱ በሕያዋንና በሙታን ላይ እንዲፈርድ በእግዚአብሔር የተሠየመ መሆኑን እንድንመሰክር አዞናል። 43በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአት ይቅርታ እንደሚያገኝ ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።”
አሕዛብ አምነው መንፈስ ቅዱስን መቀበላቸው
44ጴጥሮስ ይህን በሚናገርበት ጊዜ ቃሉን በሰሙት ሰዎች ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ። 45ከጴጥሮስ ጋር የመጡት ከተገረዙት አይሁድ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ለአሕዛብ መንፈስ ቅዱስን እንደ ሰጣቸው ባዩ ጊዜ ተደነቁ። 46ለአሕዛብ መንፈስ ቅዱስ እንደ ተሰጠ ያወቁትም አሕዛብ በሌሎች ቋንቋዎች ሲናገሩና እግዚአብሔርን በምስጋና ሲያከብሩ በመስማታቸው ነው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ 47“እነዚህ ሰዎች እንደ እኛ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለዋል፤ ታዲያ፥ እነርሱ በውሃ እንዳይጠመቁ ማን ይከለክላቸዋል?” ሲል ተናገረ። 48ስለዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲጠመቁ አዘዘ፤ ከዚህ በኋላ ጴጥሮስ ከእነርሱ ጋር ለጥቂት ቀኖች እንዲቈይ ለመኑት።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 10: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997