የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 10:1-20

ሐዋርያት ሥራ 10:1-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በቂሳርያ፣ “የኢጣሊያ ክፍለ ጦር” በሚባለው ሰራዊት ውስጥ የመቶ አለቃ የሆነ ቆርኔሌዎስ የተባለ አንድ ሰው ነበረ። እርሱም ከመላው ቤተ ሰቡ ጋር በመንፈሳዊ ነገር የተጋና እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ለሰዎች እጅግ ምጽዋት የሚሰጥ፣ አዘውትሮ ወደ እግዚአብሔር የሚጸልይ ነበር። አንድ ቀን፣ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ የእግዚአብሔር መልአክ በራእይ ወደ እርሱ መጥቶ፣ “ቆርኔሌዎስ ሆይ!” ሲለው በግልጽ አየ። ቆርኔሌዎስም በድንጋጤ ትኵር ብሎ እያየው፣ “ጌታ ሆይ፤ ምንድን ነው?” አለው። መልአኩም እንዲህ አለው፤ “ጸሎትህና ምጽዋትህ ለመታሰቢያነት ወደ እግዚአብሔር ፊት ዐርጎልሃል። አሁንም ሰዎች ወደ ኢዮጴ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስመጣው፤ እርሱም በባሕሩ አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት ዐርፏል።” ቆርኔሌዎስም፣ ያነጋገረው መልአክ ተለይቶት ከሄደ በኋላ፣ ከአገልጋዮቹ ሁለቱን፣ እንዲሁም በመንፈሳዊ ነገር የተጋና ለእርሱ ታማኝ የሆነውን አንዱን ወታደር አስጠራ፤ የሆነውንም ነገር ሁሉ ከነገራቸው በኋላ ወደ ኢዮጴ ላካቸው። የተላኩትም ሰዎች በማግስቱም ወደ ከተማዪቱ እንደ ተቃረቡ፣ ጴጥሮስ እኩለ ቀን ገደማ ሲሆን፣ ለመጸለይ ወደ ሰገነት ወጣ። በዚያን ጊዜም ስለ ተራበ የሚበላ ነገር ፈለገ፤ ምግብ እየተዘጋጀ ሳለም አሸለበውና በተመስጦ ውስጥ ሆነ፤ ሰማይም ተከፍቶ አንድ ትልቅ ጨርቅ የሚመስል ነገር በአራቱ ማእዘን ተይዞ ወደ ምድር ሲወርድ አየ። በጨርቁም ላይ አራት እግር ያላቸው የተለያዩ እንስሳት፣ በምድር የሚሳቡ ፍጥረታትና በአየር የሚበርሩ አዕዋፍ ነበሩበት። በዚህ ጊዜ፣ “ጴጥሮስ ሆይ፤ ተነሣ፤ እነዚህን ዐርደህ ብላ” የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ጴጥሮስ ግን “ጌታ ሆይ፤ ይህማ አይሆንም፤ እኔ ያልተቀደሰ ወይም ርኩስ ነገር ፈጽሞ በልቼ አላውቅምና” አለ። ያም ድምፅ እንደ ገና ለሁለተኛ ጊዜ ወደ እርሱ መጥቶ፣ “እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ እንደ ርኩስ አትቍጠረው” አለው። ይህም ሦስት ጊዜ ተደጋገመ፤ ጨርቁም ወዲያውኑ ወደ ሰማይ ተወሰደ። ጴጥሮስም ስላየው ራእይ ትርጕም እጅግ ተጨንቆ በማሰላሰል ላይ ሳለ፣ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች የስምዖንን ቤት ፈልገው ካገኙ በኋላ መጥተው በሩ ላይ ቆሙ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን እዚያ ይኖር እንደ ሆነ ጠየቁ። ጴጥሮስ የራእዩን ነገር በማሰላሰል ላይ ሳለ፣ መንፈስ እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ስለዚህ ተነሥተህ ውረድ፤ የላክኋቸውም እኔ ስለሆንሁ፣ ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ።”

ሐዋርያት ሥራ 10:1-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በቂ​ሳ​ር​ያም ቆር​ኔ​ሌ​ዎስ የሚ​ባል አንድ ሰው ነበረ፤ ኢጣ​ሊቄ ለሚ​ሉት ጭፍ​ራም የመቶ አለቃ ነበር። እር​ሱም ጻድ​ቅና ከነ​ቤተ ሰቡ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን የሚ​ፈራ ነበር፤ ለሕ​ዝ​ቡም ብዙ ምጽ​ዋት ይሰጥ ነበር፤ ዘወ​ት​ርም ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይጸ​ልይ ነበር። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መል​አ​ክም በራ​እይ ከቀኑ በዘ​ጠኝ ሰዓት በግ​ልጥ ታየው፤ ወደ እር​ሱም ገብቶ፥ “ቆር​ኔ​ሌ​ዎስ ሆይ፥” አለው። ወደ​እ​ር​ሱም ተመ​ል​ክቶ ፈራና፥ “አቤቱ፥ ምን​ድን ነው?” አለ፤ መል​አ​ኩም እን​ዲህ አለው፥ “ጸሎ​ት​ህም ምጽ​ዋ​ት​ህም መል​ካም መታ​ሰ​ቢያ ሆኖ ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዐር​ጎ​አል። አሁ​ንም ጴጥ​ሮስ የሚ​ባ​ለ​ውን ስም​ዖ​ንን ይጠ​ሩ​ልህ ዘንድ ወደ ኢዮጴ ከተማ ሰዎ​ችን ላክ። እር​ሱም ቤቱ በባ​ሕር አጠ​ገብ ባለው በቍ​ር​በት ፋቂው በስ​ም​ዖን ቤት እን​ግ​ድ​ነት ተቀ​ም​ጦ​አል። ልታ​ደ​ር​ገው የሚ​ገ​ባ​ህን እርሱ ይነ​ግ​ር​ሃል።” ያነ​ጋ​ገ​ረ​ውም መል​አክ ከሄደ በኋላ ከሎ​ሌ​ዎቹ ሁለት፥ ከማ​ይ​ለ​ዩት ጭፍ​ሮ​ቹም አንድ ደግ ወታ​ደር ጠራ። ነገ​ሩ​ንም ሁሉ ነግሮ ወደ ኢዮጴ ከተማ ላካ​ቸው። በማ​ግ​ሥ​ቱም ሄደው ወደ ከተ​ማ​ዪቱ በር ደረሱ፤ ጴጥ​ሮ​ስም በቀ​ትር ጊዜ ሊጸ​ልይ ወደ ሰገ​ነት ወጥቶ ነበር። በተ​ራበ ጊዜም ምሳ ሊበላ ወደደ፤ እነ​ር​ሱም እያ​ዘ​ጋጁ ሳሉ ተመ​ስጦ መጣ​በት። ሰማ​ይም ተከ​ፍቶ በአ​ራቱ ማዕ​ዘን የተ​ያዘ እንደ ታላቅ መጋ​ረጃ ያለ ዕቃ ወደ ምድር ሲወ​ርድ አየ። በው​ስ​ጡም አራት እግር ያለው እን​ስሳ ሁሉ፥ አራ​ዊ​ትም፥ የሚ​ን​ቀ​ሳ​ቀ​ስም፥ የሰ​ማ​ይም ወፎች ነበ​ሩ​በት። “ጴጥ​ሮስ ሆይ፥ ተነ​ሥና አር​ደህ ብላ” የሚል ቃል ወደ እርሱ መጣ። ጴጥ​ሮስ ግን፥ “አቤቱ፥ ከቶ አይ​ሆ​ንም፤ ርኩስ፥ የሚ​ያ​ጸ​ይ​ፍም ከቶ በልች አላ​ው​ቅም” አለው። ዳግ​መ​ኛም፥ “እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ንጹሕ ያደ​ረ​ገ​ውን አንተ አታ​ር​ክስ” የሚል ቃል ወደ እርሱ መጣ። ይህ​ንም ሦስት ጊዜ አለው፤ ወዲ​ያ​ው​ኑም ዕቃዉ ወደ ሰማይ ተመ​ለሰ። ጴጥ​ሮ​ስም ስለ አየው ራእይ ምን እንደ ሆነ ሲያ​ወ​ጣና ሲያ​ወ​ርድ ከቆ​ር​ኔ​ሌ​ዎስ ተል​ከው የመጡ ሰዎች የስ​ም​ዖ​ንን ቤት እየ​ጠ​የቁ በደጅ ቁመው ነበር። ተጣ​ር​ተ​ውም፦ ጴጥ​ሮስ የተ​ባለ ስም​ዖን በእ​ን​ግ​ድ​ነት በዚያ ይኖር እንደ ሆነ ጠየቁ። ጴጥ​ሮ​ስም ስለ ታየው ራእይ ሲያ​ወጣ ሲያ​ወ​ርድ መን​ፈስ ቅዱስ እን​ዲህ አለው፥ “እነሆ፥ ሦስት ሰዎች ይፈ​ል​ጉ​ሃል። ተነ​ሥና ውረድ፤ ምንም ሳት​ጠ​ራ​ጠር ከእ​ነ​ርሱ ጋር ሂድ፤ እኔ ልኬ​አ​ቸ​ዋ​ለ​ሁና።”

ሐዋርያት ሥራ 10:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነ ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበረ። እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ። ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት ያህል፦ “ቆርኔሌዎስ ሆይ” የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው። እርሱም ትኵር ብሎ ሲመለከተው ደንግጦ፦ “ጌታ ሆይ፥ ምንድር ነው?” አለ። መልአኩም አለው፦ “ጸሎትህና ምጽዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን አረገ። አሁንም ወደ ኢዮጴ ሰዎችን ልከህ ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን አስመጣ። እርሱ ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ዘንድ እንግድነት ተቀምጦአል፤ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል።” የተናገረውም መልአክ በሄደ ጊዜ፥ ከሎሎዎቹ ሁለቱን፥ ከማይለዩትም ጭፍሮቹ እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንዱን ወታደር ጠርቶ፥ ነገሩን ሁሉ ተረከላቸው ወደ ኢዮጴም ላካቸው። እነርሱም በነገው ሲሄዱ ወደ ከተማም ሲቀርቡ፥ ጴጥሮስ በስድስት ሰዓት ያህል ይጸልይ ዘንድ ወደ ጣራው ወጣ። ተርቦም ሊበላ ወደደ፤ ሲያዘጋጁለት ሳሉም ተመስጦ መጣበት፤ ሰማይም ተከፍቶ በአራት ማዕዘን የተያዘ ታላቅ ሸማ የሚመስል ዕቃ ወደ ምድር ሲወርድ አየ፤ በዚያውም አራት እግር ያላቸው ሁሉ አራዊትም በምድርም የሚንቀሳቀሱት የሰማይ ወፎችም ነበሩበት። ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሣና አርደህ ብላ የሚልም ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ጴጥሮስ ግን፦ “ጌታ ሆይ፥ አይሆንም፤ አንዳች ርኵስ የሚያስጸይፍም ከቶ በልቼ አላውቅምና” አለ። ደግሞም ሁለተኛ፦ “እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው” የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ፥ ወዲያውም ዕቃው ወደ ሰማይ ተወሰደ። ጴጥሮስም ስላየው ራእይ፦ “ምን ይሆን?” ብሎ በልቡ ሲያመነታ፥ እነሆ፥ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች ስለ ስምዖን ቤት ጠይቀው ወደ ደጁ ቀረቡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው፦ ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን በዚህ እንግድነት ተቀምጦአልን?” ብለው ይጠይቁ ነበር። ጴጥሮስም ስለ ራእዩ ሲያወጣ ሲያወርድ ሳለ፥ መንፈስ፦ “እነሆ፥ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ተነሥተህ ውረድ፥ እኔም ልኬአቸዋለሁና ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ” አለው።

ሐዋርያት ሥራ 10:1-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በቂሳርያ የሚኖር ቆርኔሌዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም በሮማውያን ጦር ሠራዊት ሥር “የኢጣልያ ብርጌድ” በሚባለው ውስጥ የመቶ አለቃ ነበር። እርሱ ከቤተ ሰቡ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ሰው ነበረ፤ ለድኾችም ብዙ ምጽዋት ይሰጥ ነበር፤ ወደ እግዚአብሔርም ዘወትር ይጸልይ ነበር። አንድ ቀን በዘጠኝ ሰዓት ገደማ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባና “ቆርኔሌዎስ!” ብሎ ሲጠራው በራእይ በግልጥ ታየው። ትኲር ብሎ ወደ መልአኩ ተመለከተና በመደንገጥ “ጌታ ሆይ! ምንድን ነው?” አለ። መልአኩም እንዲህ አለው፦ “ጸሎትህና ለድኾች የምታደርገው ምጽዋት መልካም መታሰቢያ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር ዐርጓል፤ አሁንም ሰዎችን ወደ ኢዮጴ ላክና ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስጠራ፤ እርሱ አሁን በባሕር አጠገብ በሚገኘው በቊርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት ተቀምጦአል።” ይህን የነገረው መልአክ ተለይቶት በሄደ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ከአገልጋዮቹ ሁለቱንና የእርሱ ክፍል ከሆኑት ወታደሮች እግዚአብሔርን የሚፈራውን አንዱን ጠራና፥ ሁሉንም ነገር ከነገራቸው በኋላ ወደ ኢዮጴ ላካቸው። በማግስቱ እነርሱ ሄደው ወደ ከተማው ሲቀርቡ ስድስት ሰዓት ገደማ ጴጥሮስ ወደነበረበት ቤት ሰገነት ሊጸልይ ወጣ። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ራበውና አንዳች ነገር መብላት ፈለገ፤ ምሳ በመዘጋጀት ላይ እንዳለም በተመስጦ ራእይ አየ። ያየውም ራእይ ሰማይ ተከፍቶ በአራት ማእዘን የተያዘ ትልቅ የመጋረጃ ጨርቅ የሚመስል ነገር ወደ ምድር ሲወርድ ነው። በዚያም ላይ ልዩ ልዩ እንስሳት በልባቸው የሚሳቡ ፍጥረቶችና በሰማይ የሚበርሩ ወፎች ነበሩበት። በዚያን ጊዜ “ጴጥሮስ ሆይ! ተነሥና እያረድክ ብላ!” የሚል ድምፅ ሰማ። ጴጥሮስ ግን “ጌታ ሆይ! አይሆንም! እኔ ንጹሕ ያልሆነ ወይም ርኩስ ነገር በልቼ አላውቅም” አለ። ደግሞም “እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ ርኩስ ነው ማለት አይገባህም” የሚል ድምፅ እንደገና ሰማ። ይህም ሦስት ጊዜ ከሆነ በኋላ ያ ጨርቅ የሚመስል ነገር ወዲያውኑ ወደ ሰማይ ተወሰደ። ጴጥሮስ የራእዩ ፍች “ምን ይሆን?” እያለ በሐሳቡ ሲጨነቅ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች በጥያቄ የስምዖንን ቤት አግኝተው በበር ቆመው ነበር፤ ተጣርተውም “ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን በእንግድነት የሚገኘው እዚህ ነውን?” ብለው ጠየቁ። ጴጥሮስ የራእዩን ነገር በማሰላሰል ላይ ሳለ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ አለው፦ “እነሆ! ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ተነሥና ውረድ፤ የላክኋቸው እኔ ስለ ሆንኩ ሳታመነታ ከእነርሱ ጋር ሂድ።”

ሐዋርያት ሥራ 10:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነ ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበረ። እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ። ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት ያህል “ቆርኔሌዎስ ሆይ!” የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው። እርሱም ትኩር ብሎ ሲመለከተው ደንግጦ “ጌታ ሆይ! ምንድነው?” አለ። መልአኩም አለው “ጸሎትህና ምጽዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን አረገ። አሁንም ወደ ኢዮጴ ሰዎችን ልከህ ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን አስመጣ። እርሱ ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቁርበት ፋቂው በስምዖን ዘንድ በእንግድነት ተቀምጦአል፤ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል።” የተናገረውም መልአክ በሄደ ጊዜ፥ ከሎሌዎቹ ሁለቱን፥ ከማይለዩትም ጭፍሮቹ እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንዱን ወታደር ጠርቶ፥ ነገሩን ሁሉ ተረከላቸው፤ ወደ ኢዮጴም ላካቸው። እነርሱም በነገው ሲሄዱ ወደ ከተማም ሲቀርቡ፥ ጴጥሮስ በስድስት ሰዓት ያህል ይጸልይ ዘንድ ወደ ሰገነት ወጣ። ተርቦም ሊበላ ወደደ፤ ሲያዘጋጁለት ሳሉም ተመስጦ መጣበት፤ ሰማይም ተከፍቶ በአራት ማዕዘን የተያዘ ታላቅ ሸማ የሚመስል ዕቃ ወደ ምድር ሲወርድ አየ፤ በዚያውም አራት እግር ያላቸው ሁሉ አራዊትም በምድርም የሚንቀሳቀሱት የሰማይ ወፎችም ነበሩበት። “ጴጥሮስ ሆይ! ተነሣና አርደህ ብላ፤” የሚልም ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ጴጥሮስ ግን “ጌታ ሆይ! አይሆንም፤ አንዳች ርኩስ የሚያስጸይፍም ከቶ በልቼ አላውቅምና፤” አለ። ደግሞም ሁለተኛ “እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው፤” የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ፥ ወዲያውም ዕቃው ወደ ሰማይ ተወሰደ። ጴጥሮስም ስላየው ራእይ “ምን ይሆን?” ብሎ በልቡ ሲያመነታ፥ እነሆ፥ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች ስለ ስምዖን ቤት ጠይቀው ወደ ደጁ ቀረቡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው “ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን በዚህ በእንግድነት ተቀምጦአልን?” ብለው ይጠይቁ ነበር። ጴጥሮስም ስለ ራእዩ ሲያወጣ ሲያወርድ ሳለ፥ መንፈስ “እነሆ፥ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ተነሥተህ ውረድ፤ እኔም ልኬአቸዋለሁና ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ፤” አለው።