በቂሳርያም ቆርኔሌዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራም የመቶ አለቃ ነበር። እርሱም ጻድቅና ከነቤተ ሰቡ እግዚአብሔርን የሚፈራ ነበር፤ ለሕዝቡም ብዙ ምጽዋት ይሰጥ ነበር፤ ዘወትርም ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር። የእግዚአብሔር መልአክም በራእይ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት በግልጥ ታየው፤ ወደ እርሱም ገብቶ፥ “ቆርኔሌዎስ ሆይ፥” አለው። ወደእርሱም ተመልክቶ ፈራና፥ “አቤቱ፥ ምንድን ነው?” አለ፤ መልአኩም እንዲህ አለው፥ “ጸሎትህም ምጽዋትህም መልካም መታሰቢያ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር ዐርጎአል። አሁንም ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን ይጠሩልህ ዘንድ ወደ ኢዮጴ ከተማ ሰዎችን ላክ። እርሱም ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት እንግድነት ተቀምጦአል። ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል።” ያነጋገረውም መልአክ ከሄደ በኋላ ከሎሌዎቹ ሁለት፥ ከማይለዩት ጭፍሮቹም አንድ ደግ ወታደር ጠራ። ነገሩንም ሁሉ ነግሮ ወደ ኢዮጴ ከተማ ላካቸው። በማግሥቱም ሄደው ወደ ከተማዪቱ በር ደረሱ፤ ጴጥሮስም በቀትር ጊዜ ሊጸልይ ወደ ሰገነት ወጥቶ ነበር። በተራበ ጊዜም ምሳ ሊበላ ወደደ፤ እነርሱም እያዘጋጁ ሳሉ ተመስጦ መጣበት። ሰማይም ተከፍቶ በአራቱ ማዕዘን የተያዘ እንደ ታላቅ መጋረጃ ያለ ዕቃ ወደ ምድር ሲወርድ አየ። በውስጡም አራት እግር ያለው እንስሳ ሁሉ፥ አራዊትም፥ የሚንቀሳቀስም፥ የሰማይም ወፎች ነበሩበት። “ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሥና አርደህ ብላ” የሚል ቃል ወደ እርሱ መጣ። ጴጥሮስ ግን፥ “አቤቱ፥ ከቶ አይሆንም፤ ርኩስ፥ የሚያጸይፍም ከቶ በልች አላውቅም” አለው። ዳግመኛም፥ “እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ አታርክስ” የሚል ቃል ወደ እርሱ መጣ። ይህንም ሦስት ጊዜ አለው፤ ወዲያውኑም ዕቃዉ ወደ ሰማይ ተመለሰ። ጴጥሮስም ስለ አየው ራእይ ምን እንደ ሆነ ሲያወጣና ሲያወርድ ከቆርኔሌዎስ ተልከው የመጡ ሰዎች የስምዖንን ቤት እየጠየቁ በደጅ ቁመው ነበር። ተጣርተውም፦ ጴጥሮስ የተባለ ስምዖን በእንግድነት በዚያ ይኖር እንደ ሆነ ጠየቁ። ጴጥሮስም ስለ ታየው ራእይ ሲያወጣ ሲያወርድ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ አለው፥ “እነሆ፥ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል። ተነሥና ውረድ፤ ምንም ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ፤ እኔ ልኬአቸዋለሁና።”
የሐዋርያት ሥራ 10 ያንብቡ
ያዳምጡ የሐዋርያት ሥራ 10
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 10:1-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos