የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 15

15
የአቤሴሎም ለማመፅ ማቀድ
1ከዚህ በኋላ አቤሴሎም አንድ ሠረገላና ፈረሶች ለራሱ አደራጀ፤ እንዲሁም ኀምሳ ጋሻ ጃግሬዎች እንዲኖሩት አደረገ፤ 2በማለዳ እየተነሣ በመሄድ ወደ ከተማይቱ ቅጽር በር በሚያስገባው መንገድ ዳር ይቆም ነበር፤ ንጉሡ ጉዳዩን እንዲያይለት የሚፈልግ ጠብ ክርክር ያለበት ሰው ሁሉ ወደዚያ ሲመጣ አቤሴሎም ጠርቶ ከወዴት እንደ መጣ ይጠይቀዋል፤ ሰውየው ከየትኛው ነገድ መሆኑን ከነገረው በኋላ፥ 3አቤሴሎም፥ “ተመልከት፤ ሕግ አንተን ይደግፍሃል፤ ነገር ግን በንጉሡ ተወክሎ ጉዳይህን በትክክል የሚያይልህ የለም” ይለዋል፤ 4ንግግሩንም በመቀጠል “እኔ ዳኛ ብሆን እንዴት በወደድሁ ነበር! ክርክር ወይም አቤቱታ ያለበት ሰው ወደ እኔ ሲመጣ እኔ ትክክለኛውን ፍርድ እሰጠው ነበር” ይለዋል። 5ሰውየው በፊቱ ለጥ ብሎ እጅ ለመንሣት በሚቀርብበት ጊዜ አቤሴሎም እጁን ዘርግቶ በማቀፍ ይስመዋል። 6አቤሴሎም ፍርድ ለማግኘት ወደ ንጉሡ ለሚመጡት ሁሉ እንደዚህ ያደርግ ስለ ነበር የእነርሱን ልብ ለመማረክ ቻለ።
7ከአራት ዓመት በኋላ አቤሴሎም ንጉሥ ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ንጉሥ ሆይ! ለእግዚአብሔር የተሳልኩትን ስእለት ለመፈጸም ወደ ኬብሮን እንድሄድ ፍቀድልኝ! 8እኔ አገልጋይህ በሶርያ በምትገኘው በገሹር በኖርኩበት ጊዜ ‘ወደ ኢየሩሳሌም ብትመልሰኝ መሥዋዕት አቀርብልሃለሁ’ ብዬ ለእግዚአብሔር ስእለት ተስዬ ነበር።”
9ንጉሡም “በሰላም ሂድ!” አለው፤ ስለዚህም አቤሴሎም ወደ ኬብሮን ሄደ፤ 10“ነገር ግን ወደ እስራኤል ነገዶች ሁሉ መልእክተኞችን ልኮ የእምቢልታ ድምፅ በምትሰሙበት ጊዜ ድምፃችሁን ከፍ በማድረግ ‘አቤሴሎም የኬብሮን ንጉሥ ሆኗል!’ ብላችሁ ጩኹ” ብለው እንዲነግሩአቸው አደረገ። 11በአቤሴሎም ጋባዥነት ከእርሱ ጋር ከኢየሩሳሌም የሄዱ ሁለት መቶ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም ተከትለውት የሄዱት ስለ ሤራው ምንም ነገር ሳያውቁ በቅንነት ነበር። 12አቤሴሎም መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ከንጉሥ ዳዊት አማካሪዎች አንዱ የሆነውን አኪጦፌል ተብሎ የሚጠራውን ሰው መልእክተኛ በመላክ ከጊሎ ከተማ አስጠራ፤ በንጉሡ ላይ የተጠነሰሰው ሤራ እየጠነከረ፥ የአቤሴሎምም ተከታዮች ቊጥር እየጨመረ ሄደ።
የዳዊት ከኢየሩሳሌም መሸሽ
13አንድ መልእክተኛ ዳዊትን “እስራኤላውያን ታማኝነታቸውን ለአቤሴሎም በመግለጥ ላይ ናቸው” አለው።
14ስለዚህም ዳዊት ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም ለሚገኙት መኳንንቱ ሁሉ “ከአቤሴሎም እጅ ማምለጥ ከፈለግን በፍጥነት ከዚህ ሸሽተን እንውጣ! እንግዲህ ፍጠኑ! አለበለዚያ በፍጥነት መጥቶ ድል ይመታናል፤ በከተማይቱ ያገኘውንም ሁሉ ይገድላል!” አላቸው።
15እነርሱም “እሺ ንጉሥ ሆይ! አንተ ያልከውን ሁሉ ለመፈጸም ዝግጁዎች ነን” ሲሉ መለሱለት። 16ስለዚህ ንጉሡ ቤተ መንግሥቱን ይጠብቁለት ዘንድ ካስቀራቸው ዐሥር ቊባቶች በቀር ቤተሰቡንና መኳንንቱን ሁሉ በማስከተል ሸሽቶ ሄደ።
17ንጉሡና ተከታዮቹ ሁሉ ከከተማይቱ ወጥተው በሚሄዱበት ጊዜ በከተማይቱ መጨረሻ ላይ በሚገኘው አንድ ቤት አጠገብ ቆሙ፤ 18ባለሟሎቹ ሁሉ በእርሱ በኩል አለፉ፤ የዳዊት ክብር ዘበኞች የነበሩት ከሪታውያንና ፈሊታውያን፥ እንዲሁም ከጋት የመጡ ስድስት መቶ ጌታውያን በንጉሡ ፊት አለፉ፤ 19ንጉሡም ኢታይ ተብሎ የሚጠራውን የጌት ሰው እንዲህ አለው፤ “ከእኛ ጋር ለምን ትሄዳለህ? ተመልሰህ ከአዲሱ ንጉሥ ጋር ቈይ፤ አንተ ከአገርህ ወጥተህ በመጻተኛነት እዚህ የምትኖር የውጪ አገር ሰው ነህ፤ 20በዚህ አገር የኖርከውም ለአጭር ጊዜ ነው፤ ታዲያ አንተ ከእኔ ጋር የምትንከራተተው ስለምንድን ነው? እኔ የት እንደምሄድ እንኳ አላውቅም፤ ስለዚህ የአገርህን ሰዎች ይዘህ ተመለስ፤ እግዚአብሔር ቸርነቱንና እውነተኛነቱን ይግለጥልህ።”
21ኢታይ ግን ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ጌታዬ በሚኖርበት ቦታ ሁሉ፥ በሞትም ሆነ በሕይወት እኔ አገልጋይህ በዚያ እንደምገኝ በእግዚአብሔር ስም እንዲሁም በጌታዬ በንጉሡ ሕይወት እምላለሁ።”
22ዳዊትም “መልካም ነው! እንግዲህ ጒዞህን ቀጥል!” አለው፤ ስለዚህም ኢታይ ከወታደሮቹ ሁሉና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ጒዞውን ቀጠለ፤ 23የዳዊት ተከታዮች ወጥተው በሄዱ ጊዜ ሕዝቡ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ ንጉሡ ከተከታዮቹ ጋር የቄድሮንን ወንዝ ተሻገረ፤ በአንድነትም ሆነው ወደ በረሓው አመሩ።
24ካህኑ ሳዶቅም እዚያው ነበር፤ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ሌዋውያን ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ የቃል ኪዳኑን ታቦት፥ ሕዝቡ ሁሉ ከተማውን ለቆ እስኪወጣ ድረስ በአብያታር አጠገብ አስቀመጡት። 25ከዚህ በኋላ ንጉሡ ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ከተማይቱ መልሰህ ውሰድ፤ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ያገኘሁ እንደ ሆነ አንድ ቀን ታቦቱንና ማደሪያውን እንዳይ ይፈቅድልኝ ይሆናል፤ 26በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ባላገኝ ግን በእኔ ላይ የወደደውን ያድርግ።” 27ንግግሩንም በመቀጠል ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “ተመልከት፤ ልጅህን አሒማዓጽንና የአብያታርንም ልጅ ዮናታንን ይዘህ ወደ ከተማይቱ በሰላም ሂድ፤ 28እኔም ከአንተ ወሬ እስከማገኝ ድረስ በበረሓው ውስጥ በሚገኘው በወንዙ መሸጋገሪያ ላይ እጠባበቃለሁ።” 29ስለዚህም ሳዶቅና አብያታር የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም መልሰው ወሰዱ፤ በዚያም ቈዩ።
30ዳዊትም ሐዘኑን በመግለጥ ጫማ ሳያደርግ ራሱን ተከናንቦ የደብረ ዘይትን አቀበት እያለቀሰ ወጣ፤ የተከተሉትም ሁሉ ደግሞ ራሳቸውን ተከናንበው ያለቅሱ ነበር። 31ዳዊት፥ አኪጦፌል ከአቤሴሎም ጋር በዐመፅ መተባበሩን በሰማ ጊዜ “እግዚአብሔር ሆይ! የአኪጦፌልን ምክር ወደ ከንቱነት እንድትለውጥበት እለምንሃለሁ!” ሲል ጸለየ።
32ዳዊት የማምለኪያ ስፍራ ወዳለበት ወደ ኮረብታው ጫፍ በደረሰ ጊዜ ታማኝ ጓደኛው የሆነው አርካዊው ሑሻይ ልብሱን ቀዶና በራሱ ላይ ትቢያ ነስንሶ ሊገናኘው መጣ። 33ዳዊትም እንዲህ አለው፦ “አንተ እኔን ተከትለህ ብትሄድ ወደ ኋላ ትጐትተናለህ፤ 34አንተ እኔን ልትረዳኝ የምትችለው ግን ወደ ከተማይቱ ተመልሰህ አቤሴሎምን፥ አባትህን እንዳገለገልኩ አንተንም በታማኝነት አገለግላለሁ ብለህ ብትነግረው እንዲሁም አኪጦፌል የሚሰጠውን ምክር ሁሉ ብትቃወምልኝ ነው፤ 35ካህናቱ ሳዶቅና አብያታርም በዚያው ይገኛሉ፤ በቤተ መንግሥት የምትሰማውን ነገር ሁሉ ለእነርሱ ትነግራቸዋለህ፤ 36ከእነርሱም ጋር ልጆቻቸው አሒማዓጽና ዮናታን ይገኛሉ፤ የምታገኘውንም ወሬ ሁሉ በእነርሱ በኩል ልትልክብኝ ትችላለህ።”
37ስለዚህም የዳዊት ወዳጅ ሑሻይ ወደ ከተማይቱ ተመለሰ፤ አቤሴሎምም ወዲያውኑ እዚያ ደረሰ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ