የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 16

16
ዳዊትና ጺባ
1ዳዊት ከኮረብታው ጫፍ ባሻገር ገና ጥቂት እንደ ሄደ ጺባ ተብሎ የሚጠራው የመፊቦሼት አገልጋይ በድንገት አገኘው፤ እርሱም ሁለት መቶ ሙልሙል ዳቦ፥ አንድ መቶ የዘቢብ ጥፍጥፍ፥ አንድ መቶ እስር ፍራፍሬና በወይን ጠጅ የተሞላ አንድ አቁማዳ የተጫኑ ሁለት አህዮች ይነዳ ነበር፤ #2ሳሙ. 9፥9-10። 2ንጉሥ ዳዊትም “ይህ ሁሉ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።
ጺባም “ንጉሥ ሆይ! አህዮቹን ያመጣኋቸው ቤተሰብህ እንዲቀመጡባቸው፥ ዳቦውና ፍራፍሬውም ለተከታዮችህ ስንቅ እንዲሆኑና የወይን ጠጁም በምድረ በዳ በሚደክሙበት ጊዜ እንዲጠጡት ነው” ሲል መለሰ።
3ንጉሡም “የጌታህ የሳኦል የልጅ ልጅ መፊቦሼት የት ነው?” ሲል ጠየቀው። #2ሳሙ. 19፥26-27።
ጺባም “እስራኤላውያን የአያቱን የሳኦልን መንግሥት መልሰው እንደሚሰጡት ስለ ተማመነ እርሱ አሁን የሚገኘው በኢየሩሳሌም ነው” ሲል መለሰ።
4ንጉሡም ጺባን “የመፊቦሼት የነበረው ንብረት ሁሉ ከእንግዲህ የአንተ ነው” አለው።
ጺባም “ንጉሥ ሆይ! እነሆ እኔ አገልጋይህ ነኝ፤ ዘወትር አንተን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ለመሥራት እተጋለሁ!” ሲል መለሰ።
ዳዊትና ሺምዒ
5ንጉሥ ዳዊት ወደ ባሑሪም በደረሰ ጊዜ ከሳኦል ዘመዶች አንዱ የሆነው የጌራ ልጅ ሺምዒ ሊገናኘው ወጥቶ እየተራገመ ወደ እርሱ ቀረበ፤ 6ዳዊት በሠራዊቱና በክብር ዘበኞቹ መካከል እያለ ሺምዒ በዳዊትና በመኳንንቱ ላይ ድንጋይ መወርወር ጀመረ። 7ዳዊትንም በመራገም የተናገረው ቃል እንዲህ የሚል ነው፦ “አንተ ነፍሰ ገዳይ! አንተ ወንጀለኛ! ከዚህ ውጣ! 8አንተ የሳኦልን መንግሥት ወሰድህ ቤተሰቡንም ሁሉ ገደልክ፤ እነሆ አሁን ደግሞ እግዚአብሔር አንተን በመቅጣት ላይ ነው፤ እግዚአብሔር መንግሥትን ለልጅህ ለአቤሴሎም አሳልፎ ሰጥቶታል፤ አንተ ነፍሰ ገዳይ! እነሆ የአንተ መጥፊያ ደርሶአል።”
9በዚህ ጊዜ የጸሩያ ልጅ አቢሳ ንጉሡን “ንጉሥ ሆይ! ይህ የሞተ ውሻ ጌታዬን ንጉሡን እንዴት ይራገማል? እኔ ሄጄ ራሱን ልቊረጠው!” አለው።
10ንጉሡም አቢሳንና ወንድሙን ኢዮአብን “ይህ እናንተን አይመለከታችሁም፤ እግዚአብሔር አዞት ቢረግመኝ ‘ለምን እንዲህ ታደርጋለህ?’ ብሎ ለመጠየቅ መብት የሚኖረው ማን ነው?” አላቸው። 11ቀጥሎም ዳዊት ለአቢሳና ለመኳንንቱ ሁሉ እንዲህ አለ፤ “የራሴ ልጅ ሊገድለኝ ይፈልጋል፤ ታዲያ በዚህ ብንያማዊ ሰው ስለምን ትደነቃላችሁ? እኔን እንዲረግመኝ እግዚአብሔር ነግሮታል፤ ስለዚህ ተዉት፥ የአሰበውን ያድርግ፤ 12ምናልባት እግዚአብሔር መከራዬን አይቶ በእርሱ ርግማን ፈንታ በረከትን ይሰጠኝ ይሆናል።” 13ከዚህ በኋላ ዳዊትና ሠራዊቱ ባመሩበት መንገድ ተጓዙ፤ ሺምዒም በኮረብታው ጥግ እነርሱን ተከትሎ እየሄደ በመራገም ድንጋይና ዐፈር በእነርሱ ላይ ይወረውር ነበር። 14ንጉሡና ተከታዮቹ ሁሉ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በደረሱ ጊዜ በጣም ደክሞአቸው ስለ ነበር በዚያ ዕረፍት አደረጉ።
አቤሴሎም በኢየሩሳሌም
15አቤሴሎምና ከእርሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ወደ ኢየሩሳሌም ገቡ፤ አኪጦፌልም ከእነርሱ ጋር ነበር፤ 16የዳዊት ታማኝ ወዳጅ ሑሻይ አቤሴሎምን ባገኘው ጊዜ “ረጅም ዕድሜ ለንጉሡ! ረጅም ዕድሜ ለንጉሡ! ይሁን!” እያለ ጮኸ።
17አቤሴሎምም “ለወዳጅህ ለዳዊት የነበረህ ታማኝነት እንደዚህ ነበርን? እርሱንስ ተከትለህ ለምን አልሄድክም?” ሲል ጠየቀው።
18ሑሻይም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “እንዴት እኔ ይህንን አደርጋለሁ? እኔ ምንጊዜም በዚህ ሕዝብና በመላው እስራኤል እንዲሁም በእግዚአብሔር የተመረጠው ሰው ወገን ነኝ፤ አሁንም ከአንተ ጋር እኖራለሁ፤ 19ለመሆኑ የጌታዬን ልጅ ካላገለገልኩ ማንን ላገለግል ነው? ስለዚህ አባትህን እንዳገለገልኩ አሁንም ደግሞ አንተን አገለግላለሁ።”
20ከዚህ በኋላ አቤሴሎም ወደ አኪጦፌል መለስ ብሎ “እነሆ እኛ አሁን በዚህ ተገኝተናል፤ ታዲያ ምን እንድናደርግ ትመክረናለህ?” ሲል ጠየቀው።
21አኪጦፌልም አቤሴሎምን እንዲህ አለው፦ “ቤት እንዲጠብቁ ከተዋቸው ከአባትህ ቁባቶች ጋር ተገናኝ በዚህም እስራኤላውያን ሁሉ አባትህን እንዳዋረድከው ያውቃሉ፤ ከአንተም ጋር ያሉት ሰዎች ሁሉ ስሜታቸው ይበረታታል።” 22ስለዚህ በቤተ መንግሥቱ ጣራ ላይ ለአቤሴሎም ድንኳን ተከሉለት፤ ሰውም ሁሉ እየተመለከተው ወደ ድንኳኑ ገብቶ ከአባቱ ቊባቶች ጋር ተገናኘ። #2ሳሙ. 12፥11-12። 23በዚያን ጊዜ አኪጦፌል የሚሰጠው ማንኛውም ምክር ልክ እንደ እግዚአብሔር ቃል ተቀባይነት አግኝቶ ነበር፤ ቀድሞ ዳዊት አሁን ደግሞ አቤሴሎም የእርሱን ምክር ይከተሉ ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ