የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 6:24-33

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 6:24-33 አማ05

ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሶርያ ንጉሥ ቤንሀዳድ መላ ሠራዊቱን በእስራኤል ላይ በማዝመት፥ የሰማርያን ከተማ ከበበ፤ ከበባውም የምግብን እጥረትና ብርቱ ራብ ከማስከተሉ የተነሣ፥ የአንድ አህያ ራስ ዋጋ እስከ ሰማኒያ ጥሬ ብር፥ ሁለት መቶ ግራም የሚያኽል የርግብ ኩስ ዋጋ ደግሞ አምስት ጥሬ ብር ማውጣት ጀመረ። አንድ ቀን የእስራኤል ንጉሥ በከተማይቱ የቅጽር ግንብ ላይ በሚመላለስበት ጊዜ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ “ንጉሥ ሆይ፥ እባክህ እርዳኝ!” ስትል ጮኸች። ንጉሡም “እግዚአብሔር ሊረዳሽ ካልፈቀደ እኔ ምን ዐይነት ርዳታ ልሰጥሽ እችላለሁ? ከአውድማው ወይስ ከወይን መጭመቂያው? ምን ያለኝ ይመስልሻል? ለመሆኑ ችግርሽ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቃት። እርስዋም እንዲህ ስትል መለሰችለት፤ “ባለፈው ቀን ይህች ሴት ‘ዛሬ የአንቺን ልጅ እንብላ፤ በማግስቱ ደግሞ የእኔን ልጅ እንበላለን’ ስትል ሐሳብ አቀረበች። ስለዚህም የእኔን ልጅ ቀቅለን በላን፤ በማግስቱም ‘ልጅሽን አምጪና እንብላ’ ብዬ ጠየቅኋት፤ እርስዋ ግን ደበቀችው።” ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፤ በግንቡ ላይ በመሆኑ በአቅራቢያው የነበረው ሕዝብ ንጉሡ ከልብሱ በውስጥ በኩል ማቅ ለብሶ እንደ ነበር አዩ። ንጉሡም ድምፁን ከፍ በማድረግ “የዛሬይቱ ጀንበር ከመጥለቅዋ በፊት የሳፋጥ ልጅ የኤልሳዕ ራስ ሳይቈረጥ ቢያድር እግዚአብሔር እኔን በሞት ይቅጣኝ!” ሲል ተናገረ። ወዲያውኑም ኤልሳዕን ይዞ የሚመጣ መልእክተኛ ላከ። በዚህም ጊዜ ኤልሳዕ ሊጐበኙት ከመጡ ጥቂት ሽማግሌዎች ጋር በቤት ውስጥ ነበር፤ የንጉሡ መልእክተኛ ከመድረሱም በፊት ኤልሳዕ ሽማግሌዎቹን “ያ ነፍሰ ገዳይ እኔን ለማስገደል አንድ ሰው ልኮአል! እነሆ፥ እርሱ እዚህ በሚደርስበት ጊዜ በሩን ዝጉ፤ ወደ ውስጥም እንዲገባ አትፍቀዱለት፤ ንጉሡም እርሱን ተከትሎ መጥቶ በኋላው ይገኛል” አላቸው። ገና ይህን ተናግሮ ሳይጨርስ ንጉሡ ድንገት ከተፍ ብሎ “ይህን መከራ በእኛ ላይ ያመጣብን እግዚአብሔር ነው፤ ታዲያ እርሱ አንድ ነገር ያደርግ ዘንድ ከዚህ በላይ ምን ልጠብቅ?” አለ።