ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 5
5
የንዕማን ከቈዳ በሽታ መዳን
1እግዚአብሔር በንዕማን አማካይነት ለሶርያ ሠራዊት ድልን ስለ አጐናጸፈ፥ የሶርያ ጦር አዛዥ የነበረው ንዕማን በሶርያ ንጉሥ ዘንድ እጅግ የተከበረና የተወደደ ባለሟል ነበር፤ ታዲያ ንዕማን ጀግና ወታደር ሆኖ ሳለ፥ በቈዳ በሽታ ይሠቃይ ነበር። 2ሶርያውያን በእስራኤላውያን ላይ ወረራ በፈጸሙበት በአንድ ወቅት፥ አንዲት ትንሽ እስራኤላዊት ልጃገረድ ማርከው ወስደው ነበር፤ እርስዋም ለንዕማን ሚስት፥ ገረድ ሆና ትኖር ነበር። 3አንድ ቀን እመቤትዋን፥ “ጌታዬ ንዕማን በሰማርያ ወደሚገኘው ነቢይ ቢሄድ መልካም ይመስለኛል! ነቢዩ ከዚህ የቆዳ በሽታው ሊያነጻው ይችላል!” አለቻት። 4ንዕማንም ይህን በሰማ ጊዜ ወደ ንጉሡ ቀርቦ ልጃገረዲቱ ያለችውን ሁሉ ነገረው፤ 5ንጉሡም “ይህን ደብዳቤ ይዘህ ወደ እስራኤል ንጉሥ ሂድ” ብሎ ፈቀደለት።
ስለዚህም ንዕማን ሠላሳ ሺህ ጥሬ ብር፥ ስድስት ሺህ መሐለቅ ወርቅና ምርጥ የሆነ ዐሥር መለወጫ ልብስ አስጭኖ፥ ጒዞውን ቀጠለ፤ 6ይዞት የሄደውም መልእክት “ይህ ደብዳቤ የእኔ ሠራዊት አዛዥ ስለ ሆነው ስለ ንዕማን ጉዳይ የሚገልጥ ነው፤ ከቈዳ በሽታ በማንጻት እንድትፈውሰው እፈልጋለሁ” የሚል ነበር።
7የእስራኤልም ንጉሥ ደብዳቤውን ባነበበ ጊዜ በቊጣ ልብሱን ቀደደ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ “የሶርያ ንጉሥ ይህን ሰው እንደምፈውስለት አድርጎ እንዴት ይገምታል? እኔ ሰውን ከቈዳ በሽታ እፈውስ ዘንድ የማዳንና የመግደል ሥልጣን ያለኝ እግዚአብሔር መሰልኩትን? በእርግጥ ይህ አባባል ከእኔ ጋር ጠብ መፈለጉን በግልጥ ያሳያል!” አለ።
8ነቢዩ ኤልሳዕም የሆነውን ነገር ሁሉ በሰማ ጊዜ ወደ ንጉሡ መልእክት ልኮ “ስለምን ልብስህን ቀደድክ? ሰውየውን ወደ እኔ ላከው፤ እኔም በእስራኤል ነቢይ መኖሩን አሳየዋለሁ!” አለው።
9ስለዚህም ንዕማን ፈረሶች በሚስቡት ሠረገላ ተቀምጦ በመሄድ ወደ ኤልሳዕ ቤት በሚያስገባው በር ላይ ሲደርስ ቆመ። 10ኤልሳዕም አንዱን አገልጋይ “ ‘ሄደህ በዮርዳኖስ ወንዝ ሰባት ጊዜ በመነከር ታጠብ፤ ከበሽታህም ፈጽሞ ትነጻለህ’ ብለህ ለዚህ ሰው ንገረው” ሲል አዘዘው፤ 11ንዕማን ግን ተቈጥቶ ወደ አገሩ ለመመለስ ተነሣ፤ እንዲህም እያለ ያጒረመርም ነበር፤ “እኔ እኮ ነቢዩ መጥቶ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ የቆዳው በሽታ ባረፈበት ገላዬ ላይ እጆቹን በመወዝወዝ ይፈውሰኛል ብዬ አስቤ ነበር! 12የውሃ የውሃማ በእስራኤል ከሚገኙት ወንዞች ይልቅ በአገሬ በደማስቆ የሚገኙት አባናና ፋርፋር አይሻሉምን? እንዲህ ከሆነማ በእነርሱ ታጥቤ በነጻሑ ነበር!”
13የንዕማንም አሽከሮች ወደ እርሱ ቀረብ ብለው፥ “ጌታችን ሆይ፥ ነቢዩ ሌላ ከባድ ነገር እንድታደርግ ቢያዝህ ኖሮ ትፈጽመው ነበር፤ ታዲያ ነቢዩ ባዘዘህ መሠረት ታጥበህ ከበሽታህ መንጻት ምን ይከብድሃል?” አሉት። 14ስለዚህም ንዕማን የእግዚአብሔር ሰው ባዘዘው መሠረት ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወርዶ ሰባት ጊዜ በመነከር ታጠበ፤ ከበሽታውም ፈጽሞ ነጻ፤ ሥጋውም እንደ ትንሽ ልጅ ገላ በመታደስ ፍጹም ጤናማ ሆነ፤ #ሉቃ. 4፥27። 15ከዚህም በኋላ ከተከታዮቹ ጋር ወደ እግዚአብሔር ሰው ተመልሶ መጥቶ፦ “ከእስራኤል አምላክ በቀር ሌላ አምላክ አለመኖሩን እነሆ፥ አሁን ተረዳሁ፤ ስለዚህም ጌታዬ ሆይ፥ እባክህ ይህን ስጦታ ተቀበለኝ” አለው።
16ኤልሳዕም “በማገለግለው በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፤ ምንም ነገር አልቀበልም” ሲል መለሰለት።
ንዕማንም ስጦታውን እንዲቀበልለት አጥብቆ ቢለምነውም ኤልሳዕ ሊቀበለው አልፈቀደም፤ 17ስለዚህም ንዕማን እንዲህ አለ፦ “ስጦታዬን የማትቀበለኝ ከሆነ ከአሁን ጀምሮ ለእግዚአብሔር ብቻ እንጂ ለሌሎች ባዕዳን አማልክት የሚቃጠልም ሆነ ወይም ሌላ ዐይነት መሥዋዕት ስለማላቀርብ የሁለት በቅሎ ጭነት ዐፈር ይዤ እንድሄድ ፍቀድልኝ፤ 18ስለዚህም የሀገሬን ንጉሥ በማጀብ ሪሞን የተባለ የሶርያ አምላክ ወደሚመለክበት መቅደስ ብገባና ብሰግድም እንኳ እግዚአብሔር ይቅር እንደሚለኝ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በእርግጥም ይቅር ይለኛል።”
19ኤልሳዕም “በሰላም ሂድ!” አለው፤ ንዕማንም ተሰናብቶ ሄደ።
እርሱም ጥቂት ራቅ ብሎ እንደ ሄደ፥ 20የኤልሳዕ አገልጋይ የሆነው ግያዝ፥ “ጌታዬ ንዕማንን ምንም ነገር ሳያስከፍል አሰናብቶታል፤ ያ ሶርያዊ ሰው ያቀረበለትን ስጦታ መቀበል ይገባው ነበር፤ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፥ በፍጥነት በመሮጥ ተከትየው ሄጄ ከእርሱ አንድ ነገር ማግኘት አለብኝ” ሲል በልቡ አሰበ። 21ስለዚህም ግያዝ ንዕማንን ከኋላው ተከተለው፤ ንዕማንም መለስ ብሎ አንድ ሰው እየሮጠ ሲከተለው ባየ ጊዜ፥ ከሠረገላው ወርዶ “ምነው፥ በደኅና መጣህን?” ሲል ጠየቀው።
22ግያዝም “መምጣትስ በደኅና ነው የመጣሁት፤ ነገር ግን ጌታዬ በኰረብታማው በኤፍሬም አገር የሚኖሩ ሁለት የነቢያት ጒባኤ አባላት ድንገት በእንግድነት ስለ መጡበት፥ ሦስት ሺህ ብርና ሁለት መቀየሪያ ልብስ እንድትሰጣቸው እነግርህ ዘንድ ወደ አንተ ልኮኛል” ሲል መለሰለት።
23ንዕማንም “እንግዲያውስ እባክህ ስድስት ሺህ ብር ልስጥ” ሲል መለሰለት፤ በዚህም አሳቡ በመጽናት ብሩን በሁለት ከረጢት ሞልቶ ከሁለት መለወጫ ልብሶች ጋር በሁለት አገልጋዮች አስይዞ ከግያዝ ቀድመው በፊት በፊቱ እንዲሄዱ አደረገ። 24ኤልሳዕ ወደሚኖርባትም ኰረብታ በደረሱ ጊዜ፥ ግያዝ ሁለቱን ከረጢት ተቀብሎ ወደ ቤት አስገባ፤ ከዚያም በኋላ የንዕማንን አገልጋዮች አሰናብቶአቸው ሄዱ። 25ወደ ቤት ተመልሶ ገባ፤ ኤልሳዕም “እስከ አሁን የት ነበርክ?” ሲል ጠየቀው።
ግያዝም “ጌታዬ፥ ኧረ እኔ የትም አልሄድኩም” ሲል መለሰ።
26ኤልሳዕም “ሰውየው ሊያነጋግርህ ከሠረገላው ላይ ሲወርድ እኔ በመንፈስ ከአንተ ጋር አልነበርኩምን? እነሆ አሁን ገንዘብና ልብስ፥ የወይራና የወይን ተክል ቦታ፥ በግና የቀንድ ከብት ወይም አገልጋዮችን ለመቀበል ጊዜው አይደለም! 27ከዚህም የተነሣ እነሆ፥ የንዕማን የቆዳ በሽታ ወደ አንተ ይተላለፋል፤ አንተና ዘሮችህ ለዘለዓለም ከዚያ በሽታ አትነጹም!” አለው።
ግያዝም ወጥቶ ሲሄድ፥ ያ የቆዳ በሽታ ስለ ተጋባበት ገላው እንደ በረዶ ነጭ ሆነ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 5: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997