ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 4
4
ኤልሳዕ ድኻይቱን መበለት መርዳቱ
1የነቢያት ጉባኤ አባል የነበረ ባልዋ የሞተባት አንዲት ሴት ወደ ኤልሳዕ መጥታ “ጌታዬ ሆይ! ባሌ ሞቶብኛል! እርሱም አንተ እንደምታውቀው እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ነበር፤ ነገር ግን እነሆ ለባሌ ገንዘብ አበድሮት የነበረ አንድ ሰው በባሌ ዕዳ ፈንታ ሁለት ወንዶች ልጆቼን ወስዶ ባሪያ አድርጎ ሊገዛቸው ፈልጎአል” አለችው።
2ኤልሳዕም “ታዲያ ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ? በቤትሽም ምን እንዳለሽ ንገሪኝ” ሲል ጠየቃት።
እርስዋም “በትንሽ ማሰሮ ከሚገኝ የወይራ ዘይት በቀር ሌላ ምንም የለኝም” ስትል መለሰች።
3ኤልሳዕም እንዲህ አላት፦ “ወደ ጐረቤቶችሽ ሄደሽ ማግኘት የምትችዪውን ያኽል ባዶ ማድጋ ለምኚ፤ 4ከዚህም በኋላ አንቺና ልጆችሽ ወደ ቤት ገብታችሁ መዝጊያውን ዝጉ፤ የማሰሮውንም ዘይት ወደ ማድጋዎቹ ማንቈርቈር ጀምሩ፤ እያንዳንዱ ማድጋ በሚሞላበት ጊዜ ለብቻው በማግለል አኑሩት።”
5ስለዚህም ሴትዮዋ ወደ ቤትዋ ሄዳ ከልጆችዋ ጋር በሩን ዘጋች፤ ዘይት የነበረበትን ትንሽ ማሰሮ አንሥታ ልጆችዋ እያቀረቡላት በማንቈርቈር በየማድጋዎቹ ሞላች። 6ማድጋዎቹንም ሁሉ ከሞሉ በኋላ “ሌላ ትርፍ የለም ወይ?” ስትል ጠየቀች፤ ከልጆችዋም አንዱ “ሌላ ማድጋ የለም” ሲል መለሰላት። ከዚያም በኋላ ዘይቱ መውረዱን አቆመ፤ 7እርስዋም ተመልሳ ወደ ነቢዩ ኤልሳዕ ሄደች፤ እርሱም “እንግዲህ ዘይቱን ሸጠሽ ዕዳሽን በሙሉ ክፈይ፤ ለአንቺና ለልጆችሽ መተዳደሪያ የሚሆንም ብዙ ገንዘብ ይተርፍሻል” አላት።
ኤልሳዕና የሱነም ከተማ ነዋሪ የሆነችው ባለጸጋ ሴት
8አንድ ቀን ኤልሳዕ አንዲት ሀብታም ሴት ወደምትኖርበት ወደ ሱነም ሄደ፤ እርስዋም ምግብ እንዲበላ ጋበዘችው፤ ከዚያን ዕለት ጀምሮ ወደ ሱነም በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ በቤትዋ ይመገብ ነበር፤ 9እርስዋም ባልዋን እንዲህ አለችው፤ “ብዙ ጊዜ ወደ ቤታችን የሚመጣው ይህ ሰው የተቀደሰ የእግዚአብሔር ሰው ስለ መሆኑ እርግጠኛ ነኝ፤ 10ስለዚህም በሰገነቱ ላይ አንድ ትንሽ ክፍል ሠርተን በዚያች ውስጥ አንድ አልጋ፥ አንድ ጠረጴዛ፥ አንድ ወንበርና አንድ የፋኖስ መብራት እናኑርለት፤ እርሱም እኛን ለመጐብኘት በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ ማረፊያ ትሆነዋለች።”
11አንድ ቀን ኤልሳዕ ወደ ሱነም ተመልሶ ሄደ፤ ዕረፍት ለማድረግም ወደ ተሠራለት ክፍል ገብቶ ዐረፈ፤ 12ግያዝ ተብሎ የሚጠራውንም አገልጋዩን፥ “ሄደህ ሱነማዊትን ጥራ” አለው፤ እርስዋም መጥታ በፊቱ ቆመች። 13ግያዝ “ለእኛ ስላደረገችው መልካም ነገር ሁሉ ምን አደርግላት ዘንድ እንደምትፈልግ ጠይቃት፤ ምናልባት ወደ ንጉሡ ወይም ወደ ጦር አዛዡ ዘንድ ሄጄ የምነግርላት ጉዳይ ሊኖር ይችላል” አለው።
እርስዋም “በዘመዶች መካከል በምኖርበት በዚህ ስፍራ ምንም የሚቸግረኝ ነገር የለም” ስትል መለሰችለት።
14ኤልሳዕም ግያዝም “ታዲያ ምን ላደርግላት እችላለሁ?” ሲል ጠየቀው።
ግያዝም “እነሆ፥ ልጅ የላትም፤ ባልዋም ሽማግሌ ነው” ሲል መለሰ።
15ኤልሳዕም “እንድትመጣ ንገራት” ብሎ አዘዘው። እርስዋም መጥታ በበሩ አጠገብ ቆመች፤ 16ኤልሳዕም “በመጪው ዓመት ልክ ይህን ጊዜ ወንድ ልጅ ትታቀፊያለሽ” አላት። #ዘፍ. 18፥14።
እርስዋም፦ “አይደለም! ጌታዬ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! እባክህ የማይፈጸም የተስፋ ቃል አትንገረኝ!” አለችው።
17ነገር ግን ሴቲቱ ፀነሰች፤ ልክ ኤልሳዕ የተናገረው ጊዜ ሲደርስ በተከታዩ ዓመት ወንድ ልጅ ወለደች።
18ሕፃኑም አደገ፤ በመከር ወራት አንድ ቀን ጧት ያ ልጅ ከአጫጆች ጋር በእርሻ ውስጥ ወደነበረው ወደ አባቱ ሄደ፤ 19በድንገትም “ራሴን! ራሴን!” ብሎ ወደ አባቱ ጮኸ። አባትየውም አንዱን አገልጋይ ጠርቶ፥ “ልጁን ወደ እናቱ ውሰድ” ሲል አዘዘው። 20አገልጋዩም ያን ልጅ ተሸክሞ በመውሰድ ለእናቱ ሰጣት፤ እርስዋም እንደ ታቀፈችው ቈይቶ እኩለ ቀን ላይ ሞተ፤ 21እርሱንም አውጥታ ለኤልሳዕ በተሠራው ክፍል በማስገባት በአልጋው ላይ አስተኛችው፤ በሩንም ዘግታበት ተመልሳ ሄደች። 22ባልዋንም ጠርታ “አንድ አገልጋይና አንድ አህያ ላክልኝ፤ ወደ እግዚአብሔር ሰው ዘንድ መሄድ ይገባኛል፤ በተቻለም መጠን ፈጥኜ እመለሳለሁ” አለችው።
23ባልዋ ግን “ዛሬ ስለምን ትሄጂአለሽ? ሰንበት ወይም የጨረቃ በዓል የሚከበርበት ጊዜ አይደለም” አላት።
እርስዋም “ግድ የለም፤ እንዳልኩህ አድርግ” አለችው፤ 24እርስዋም አህያው እንዲጫንላት ካደረገች በኋላ አገልጋዩን “በሚቻል መጠን አህያው እንዲፈጥን አድርግ፤ እኔም ካልነገርኩህ በቀር ቀስ ብሎ እንዲሄድ ፋታ አትስጠው” ስትል አዘዘችው። 25እርስዋም ከዚያ ተነሥታ ኤልሳዕ ወደነበረበት ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ወጣች።
ኤልሳዕም ገና በሩቅ ሳለች ወደ እርሱ ስትመጣ አይቶ አገልጋዩን ግያዝን “ተመልከት! ያቺ ሴት ከሱነም ወደዚህ በመምጣት ላይ ናት! 26ፈጠን ብለህ ሂድና የእርስዋን፥ የባልዋንና የልጅዋን ደኅንነት ጠይቃት” አለው።
እርስዋም ግያዝን “ሁላችንም ደኅና ነን” ስትል ነገረችው። 27ወደ ኤልሳዕ በቀረበች ጊዜ ግን ወደ መሬት ለጥ ብላ እጅ በመንሣት እግሮቹን ያዘች፤ በዚህ ጊዜ ግያዝ ገፍቶ ሊያስወግዳት ቃጣ፤ ኤልሳዕ ግን “ተዋት፤ ምን ያኽል ጭንቀት እንዳለባት አታይምን? እግዚአብሔርም ስለ እርስዋ ችግር የገለጠልኝ ነገር የለም” አለው።
28ሴቲቱም “ጌታዬ፥ ልጅ እንድትሰጠኝ ጠይቄህ ነበርን? ‘የማይፈጸምስ የተስፋ ቃል አትስጠኝ’ ብዬ ነግሬህ አልነበረምን?” አለችው።
29ኤልሳዕም ወደ ግያዝ መለስ ብሎ “በፍጥነት ተነሥና የእኔን ምርኲዝ ይዘህ ሂድ! ለአንድም ሰው ሰላምታ ለመስጠት እንኳ በመንገድ አትቁም፤ ማንም ሰው ሰላምታ ቢሰጥህ አጸፋውን ለመመለስ ጊዜ አታጥፋ፤ በቀጥታ ወደ ቤት ሄደህ የእኔን ምርኲዝ በልጁ ፊት ላይ አኑር!” አለው።
30የልጁ እናት ግን ኤልሳዕን “በምተማመንበት በሕያው እግዚአብሔር ስምና በነፍስህ እምላለሁ፤ ከቶ አንተን ትቼ አልሄድም!” አለችው፤ ስለዚህ እርስዋን ተከትሎ ለመሄድ ተነሣ፤ 31ግያዝም ወደ ፊት ቀድሞአቸው ሄደና የኤልሳዕን ምርኲዝ በልጁ ፊት ላይ አኖረ፤ ነገር ግን ድምፅም ሆነ ሌላ የሕይወት ምልክት አልነበረም፤ ስለዚህም ተመልሶ ሄዶ ኤልሳዕን “ልጁ አልተነሣም” አለው።
32ኤልሳዕም በደረሰ ጊዜ ብቻውን ወደ ክፍሉ ገብቶ፥ ልጁ ሞቶ በአልጋው ላይ መጋደሙን አየ፤ 33ከልጁ ጋር ብቻውን ሆኖ፥ ክፍሉንም ዘግቶ፥ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። 34ከዚህም በኋላ አፉን ከአፉ፥ ዐይኖቹን ከዐይኖቹ፥ እጆቹን ከእጆቹ ጋር ገጥሞ በልጁ ሬሳ ላይ ተጋደመ፤ ኤልሳዕም ተዘርግቶ እንደ ተጋደመበት የልጁ ሰውነት መሞቅ ጀመረ። 35ኤልሳዕም ተነሥቶ በክፍሉ ውስጥ ወዲያና ወዲህ ይመላለስ ጀመር፤ እንደገናም ተመለሰና በመዘርጋት በልጁ ላይ ተጋደመ፤ ልጁም ሰባት ጊዜ ካስነጠሰው በኋላ ዐይኖቹን ከፈተ። #1ነገ. 17፥21። 36ኤልሳዕም ግያዝን “ሱነማይቱን ጥራ” አለው፤ እርስዋም በመጣች ጊዜ ኤልሳዕ “ልጅሽ ይኸውልሽ!” አላት። 37እርስዋም ወደ መሬት ለጥ ብላ በኤልሳዕ ጫማ ላይ በመውደቅ እጅ ነሣች፤ ከዚያም በኋላ ልጅዋን ይዛ ሄደች።
ሌሎች ሁለት ተአምራት
38በመላ አገሪቱ ራብ በነበረበት በአንድ ወቅት ኤልሳዕ ወደ ጌልጌላ ተመልሶ መጣ፤ በዚያም የነቢያትን ጉባኤ በማስተማር ላይ ሳለ አገልጋዩን “ትልቅ ድስት ጥደህ ወጥ ሥራላቸው” አለው። 39ከነቢያቱም አንዱ ጎመን የሚመስል ቅጠላ ቅጠል ለመልቀም ወደ ሜዳ ሔደ፤ እርሱም በዱር ውስጥ የበቀለ የቅል ሐረግ አገኘ፤ መሸከም የሚችለውን ያኽል በርከት ያለ ቅል ቈርጦ አመጣ፤ የዚያንም ምንነት ሳያውቅ ከትፎ ወጡ ውስጥ ጨመረው፤ 40ነቢያትም እንዲመገቡት የወጣላቸውን ወጥ ቀምሰው “በዚህ ወጥ ውስጥ የሚገድል መርዝ አለ!” ብለው ወደ ኤልሳዕ ጮኹ፤ ሊመገቡትም አልቻሉም፤ 41ኤልሳዕም ዱቄት እንዲሰጡት ጠይቆ በድስቱ ውስጥ ጨመረውና “ወጡን እያወጣህ ጨምርላቸው” ሲል አዘዘ፤ በዚህም ጊዜ በወጡ ውስጥ ምንም ዐይነት መራራነት አልነበረም።
42ሌላም ጊዜ በዓልሻሊሻ ተብሎ ከሚጠራው ስፍራ አንድ ሰው በመከር ጊዜ በመጀመሪያ ከተወቃው ገብስ የተጋገሩ ኻያ የዳቦ ሙልሙሎችና አዲስ የተቈረጠ እሸት ለኤልሳዕ ይዞለት መጣ፤ ኤልሳዕም “ለነቢያት ጉባኤ አቅርብላቸውና ይብሉ” ብሎ አገልጋዩን አዘዘው፤ 43አገልጋዩ ግን “ይህ ለመቶ ሰው የሚበቃ ይመስልሃልን?” ሲል ጠየቀው።
ኤልሳዕም “እንዲበሉ አቅርብላቸው፤ በልተው መጥገብ ብቻ ሳይሆን እንደሚተርፋቸውም እግዚአብሔር ተናግሮአል” አለው። 44ስለዚህም አገልጋዩ ምግቡን አቀረበላቸው፤ እግዚአብሔርም በተናገረው መሠረት ሁሉም በልተው ከጠገቡ በኋላም የተረፈ ምግብ ነበር።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 4: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997