የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 21

21
የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ
(2ዜ.መ. 33፥1-20)
1ምናሴ በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ኀምሳ አምስት ዓመት ገዛ፤ እናቱም ሔፍጺባ ተብላ የምትጠራ ነበረች፤ 2እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ አገር በሚገቡበት ጊዜ እግዚአብሔር ከፊታቸው ነቃቅሎ ያጠፋቸውን የአሕዛብን አሳፋሪ ልማድ በመከተል ምናሴ የሠራው ኃጢአት እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ #ኤር. 15፥4። 3ምናሴ አባቱ ሕዝቅያስ ደምስሶአቸው የነበሩትን የአሕዛብ መስገጃ ስፍራዎች እንደገና እንዲሠሩ አደረገ፤ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ ባደረገውም ዐይነት ባዓል ተብሎ ለሚጠራው ባዕድ አምላክ መሠዊያዎችን፥ አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስልን ሠራ፤ የሰማይ ከዋክብትንም አመለከ። 4እግዚአብሔር እንዲመለክበት ባዘዘው ስፍራ ማለትም በቤተ መቅደስ ውስጥ አረማዊ መሠዊያዎችን አቆመ። #2ሳሙ. 7፥13። 5በሁለቱም የቤተ መቅደሱ አደባባዮች የሰማይ ከዋክብት የሚመለኩባቸውን መሠዊያዎች ሠራ፤ 6የገዛ ልጁንም መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ እርሱም ራሱ ሟርተኛና አስማተኛ ሆኖ ከጠንቋዮችና ከሙታን ጠሪዎች ምክርን ይጠይቅ ነበር፤ በዚህም ሁሉ አድራጎቱ ታላቅ ኃጢአት በመሥራቱ የእግዚአብሔርን ቊጣ አነሣሣ። 7በቤተ መቅደሱም ውስጥ የአሼራን ምስል አኖረ፤ ይህም ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን “ይህ በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ እኔ ለዘለዓለም እመለክበት ዘንድ ከዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ግዛት ሁሉ የመረጥኩት ስፍራ ነው፤ 8የእስራኤል ሕዝብ ትእዛዞቼን ቢጠብቁና ለአገልጋዬ ለሙሴ የሰጠሁትንም ሕግ ቢፈጽሙ፥ ለቀድሞ አባቶቻቸው ከሰጠኋቸው ከዚህች ምድር ተነቃቅለው እንዲጠፉ አላደርግም” ሲል ነግሮአቸው የነበረው ነው፤ #1ነገ. 9፥3-5፤ 2ዜ.መ. 7፥12-18። 9የይሁዳ ሰዎች ግን ለእግዚአብሔር ቃል ታዛዦች ሆነው አልተገኙም፤ ይልቁንም ምናሴ እስራኤላውያን ወደፊት እየገፉ ሲመጡ እግዚአብሔር ከፊታቸው ነቃቅሎ ያጠፋላቸው ሕዝቦች ይፈጽሙት ከነበረው ይበልጥ ወደ ከፋ ኃጢአት መራቸው።
10እግዚአብሔርም በአገልጋዮቹ በነቢያት አማካይነት እንዲህ ሲል ተናገረ፦ 11“የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ ይህን ሁሉ አሳፋሪ ነገር አደረገ፤ ይኸውም ቀድሞ ከነዓናውያን ይፈጽሙት ከነበረው ሁሉ የከፋ ነው፤ በሠራቸውም ጣዖቶች የይሁዳን ሕዝብ ወደ ኃጢአት መራ፤ 12ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እኔ እግዚአብሔር በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ የማመጣው በጣም ከባድ መቅሠፍት ይህ ነው፤ ስለ እርሱም የሚሰማ ሰው ሁሉ በድንጋጤ ጭው ይላል፤ 13ሰማርያንና የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ከነዘሮቹ እንደ ቀጣሁ ሁሉ ኢየሩሳሌምንም እቀጣለሁ፤ ሳሕን ከተወለወለ በኋላ ተደፍቶ እንደሚቀመጥ፥ እኔም ኢየሩሳሌምን ከኃጢአት አጸዳታለሁ። 14ከጥፋት የተረፈውን ሕዝቤን ለጠላቶቹ ተላልፎ እንዲሰጥ እተወዋለሁ፤ እርሱም ይማረካል፤ ንብረቱም ይዘረፋል። 15በእነርሱም ላይ ይህን ሁሉ የማደርግበት ምክንያት የቀድሞ አባቶቻቸው ከግብጽ ከወጡበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ ኃጢአት ሠርተው እኔን በማሳዘናቸውና ቊጣዬን በማነሣሣታቸው ነው።”
16ምናሴ የይሁዳን ሕዝብ ወደ ጣዖት አምልኮና እግዚአብሔርን ወደሚያሳዝን ኃጢአት ከመምራት አልፎ፥ ንጹሓን የሆኑትን ብዙ ሰዎችን በመፍጀት የኢየሩሳሌምን መንገዶች በደም እንዲጥለቀለቁ አድርጎአል።
17ምናሴ ያደረገው ሌላው ነገርና የፈጸመው ኃጢአት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ 18ምናሴ ሞተ፤ በቤተ መንግሥቱ ግቢ “የዑዛ የአትክልት ስፍራ” ተብሎ በሚጠራው ቦታ ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አሞን ነገሠ።
የይሁዳ ንጉሥ አሞን
(2ዜ.መ. 33፥21-25)
19አሞን በይሁዳ በነገሠ ጊዜ፥ ዕድሜው ኻያ ሁለት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሁለት ዓመት ገዛ፤ እናቱም መሹሌሜት ተብላ የምትጠራ የያጥባ ከተማ ተወላጅ የሐሩጽ ልጅ ነበረች፤ 20አሞን እንደ አባቱ እንደ ምናሴ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሠራ። 21የአባቱንም መጥፎ አርአያነት ሁሉ ተከተለ፤ አባቱ ይሰግድላቸው የነበሩትንም ጣዖቶች አመለከ፤ 22የቀድሞ አባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርንም ተወ፤ ለእግዚአብሔርም ቃል ለመታዘዝን ፈቃደኛ አልሆነም።
23ባለሟሎቹ የሆኑ ባለሥልጣኖችም በአሞን ላይ አድመው በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ገደሉት፤ 24የይሁዳም ሕዝብ የአሞንን ገዳዮች ደምስሰው ልጁን ኢዮስያስን አነገሡ።
25አሞን ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። 26አሞን “የዑዛ የአትክልት ስፍራ” ተብሎ በሚጠራው መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢዮስያስ ነገሠ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ