የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 20

20
የንጉሥ ሕዝቅያስ ታሞ መዳን
(ኢሳ. 38፥1-821-222ዜ.መ. 32፥24-26)
1በዚያን ዘመን ንጉሥ ሕዝቅያስ በጠና ታሞ ለመሞት ተቃርቦ ነበር፤ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ሊጐበኘው ሄዶ “እግዚአብሔር ‘ከሕመምህ አትድንም፤ መሞትህም ስለማይቀር ሁሉን ነገር አስተካክል’ ብሎሃል” ሲል ነገረው።
2ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ፥ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጸለየ፦ 3“እግዚአብሔር ሆይ! በታማኝነትና በቅንነት እንዳገለገልኩህ፥ አንተ የምትደሰትበትንም ነገር ለማድረግ ዘወትር እጥር እንደ ነበር ታስብ ዘንድ እለምንሃለሁ!” እያለ በመጸለይ ምርር ብሎ አለቀሰ።
4ኢሳይያስ ከንጉሡ ፊት ወጥቶ የቤተ መንግሥቱን መካከለኛ አደባባይ አልፎ ከመሄዱ በፊት፥ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል መጣለት፦ 5“ሕዝቤን ወደሚመራው ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ተመልሰህ በመግባት እንዲህ በለው፦ ‘እኔ የቀድሞ አባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ እንባህንም ተመልክቻለሁ፤ እኔ እፈውስሃለሁ፤ ከሦስት ቀንም በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ ትወጣለህ፤ 6በዕድሜህም ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምርልሃለሁ፤ አንተንና ይህችን የኢየሩሳሌምን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ በመታደግ አድናለሁ፤ ስለ ክብሬና ለአገልጋዬ ለዳዊት ስለ ሰጠሁት የተስፋ ቃል ከተማይቱን በመከላከል እጠብቃታለሁ።’ ”
7ከዚህም በኋላ ኢሳይያስ የንጉሡን አገልጋዮች፥ “የበለስ ፍሬ ጥፍጥፍ አምጡልኝ” ብሎ አመጡለት፤ በቊስሉ ላይ ባደረጉለት ጊዜ የሕዝቅያስ ቊስል ተፈወሰ። 8ንጉሥ ሕዝቅያስም ኢሳይያስን “እግዚአብሔር እንደሚፈውሰኝና ከሦስት ቀን በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ መሄድ እንደምችል በምን ምልክት ዐውቃለሁ?” ሲል ጠየቀው።
9ኢሳይያስም “እግዚአብሔር የሰጠውን የተስፋ ቃል የሚፈጽም ስለ መሆኑ ራሱ ምልክት ይሰጥሃል፤ እንግዲህ አሁን የምትመርጠው ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ፊት እንዲሄድ ነው? ወይስ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ?” ሲል ጠየቀው።
10ሕዝቅያስም “ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ፊት እንዲሄድ ማድረግ ይቀላል፤ ስለዚህ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አድርግልኝ” አለው።
11ኢሳይያስም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ንጉሥ አካዝ ባሠራው ደረጃ ላይ ያረፈው ጥላ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደረገ።
ከባቢሎን የመጡ መልእክተኞች
(ኢሳ. 39፥1-8)
12በዚያኑ ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ የባላዳን ልጅ መሮዳክ ባላዳን፥ ንጉሥ ሕዝቅያስ ታሞ የነበረ መሆኑን ሰማ፤ ስለዚህም ከገጸ በረከት ጋር ደብዳቤ ላከለት፤ 13ሕዝቅያስም መልእክተኞቹን በደስታ ተቀበላቸው፤ በቤተ መንግሥቱም የዕቃ ግምጃ ቤት ያለውን ሀብት በሙሉ፥ ብሩንና ወርቁን፥ ቅመማ ቅመሙንና ሽቶውን፥ የጦር መሣሪያውንም ሁሉ አሳያቸው፤ በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤትም ሆነ በመንግሥቱ በማንኛውም ስፍራ ካለው ሀብት ሁሉ ሕዝቅያስ ያላሳያቸው አንድም አልነበረም። 14በዚያን ጊዜ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ሄዶ፥ “እነዚህ ሰዎች ከወዴት መጡ? ምንስ ነገሩህ?” ብሎ ጠየቀው።
ሕዝቅያስም “እነርሱ የመጡት ባቢሎን ከሚባል ከሩቅ አገር ነው” ሲል መለሰለት።
15ኢሳይያስም “በቤተ መንግሥቱ ምን አዩ” ሲል ጠየቀው።
ሕዝቅያስም “ሁሉን ነገር አይተዋል፤ በግምጃ ቤቱ ካለው ሀብት ሁሉ ለእነርሱ ያላሳየኋቸው አንድም ነገር የለም” አለ።
16ኢሳይያስም ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ #2ነገ. 24፥13፤ 2ዜ.መ. 36፥10። 17‘የቀድሞ አባቶችህ እስከዚህች ቀን ያከማቹት በቤተ መንግሥትህ ያለው ሀብት ሁሉ ተጠራርጎ ወደ ባቢሎን የሚወስድበት ጊዜ ይመጣል፤ ምንም ነገር አይቀርም፤ 18ከዘሮችህም አንዳንዶቹ ወደ ባቢሎን ተማርከው በመሄድ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ጃንደረቦች ሆነው እንዲያገለግሉ ይደረጋል።’ ” #2ነገ. 24፥14-15፤ ዳን. 1፥1-7።
19ንጉሥ ሕዝቅያስም በተለይ በእርሱ ዘመን በሰላም የመኖር ዋስትና እንዳለ ስለ ተረዳ “ከእግዚአብሔር ተልከህ የተናገርከኝ ቃል መልካም ነው” ሲል መለሰ።
የንጉሥ ሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ
(2ዜ.መ. 32፥32-33)
20ንጉሥ ሕዝቅያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ የጀግንነት ሥራው ጭምር፥ እንዲሁም የውሃ ማጠራቀሚያ ግድብ እንዴት እንደ ሠራና ወደ ከተማይቱ ውሃ ለማምጣት ያስቈፈረው የመሬት ውስጥ ቦይ አሠራር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። 21ሕዝቅያስም ሞተ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ምናሴ ነገሠ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ