የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአስ በነገሠ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ። እርሱም እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ ምሳሌነት በመከተል ኃጢአት በመሥራቱ እግዚአብሔርን አሳዘነ። ዮአስ የፈጸመው ሌላው ነገር ሁሉ እንዲሁም በይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ ላይ ባደረገው ጦርነት የፈጸመው ጀግንነት ጭምር በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። ከዚህ በኋላ ዮአስ ሞተ፤ በሰማርያም በሚገኘው መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ዳግማዊ ኢዮርብዓም ነገሠ። ነቢዩ ኤልሳዕ በብርቱ ደዌ ታሞ ነበር፤ ተኝቶም ሊሞት በሚያጣጥርበት ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ሊጠይቀው ሄዶ፥ ድምፁን ከፍ በማድረግ “አባቴ ሆይ! አባቴ ሆይ! አንተ እኮ የእስራኤል ሕዝብ ኀይላቸውና ጋሻ መከታቸው ነህ!” እያለ አለቀሰለት። ኤልሳዕም ንጉሡን “አንድ ቀስትና ፍላጻዎች ውሰድ” ሲል አዘዘው፤ ዮአስም እንደታዘዘው አደረገ፤ ኤልሳዕም “ፍላጻዎቹን ለማስፈንጠር ተዘጋጅ” አለው፤ ንጉሡም እንደታዘዘው አደረገ፤ ኤልሳዕም እጆቹን በንጉሡ እጆች ላይ አኖረ። ኤልሳዕ “የምሥራቁን መስኮት ክፈት” አለ፤ ንጉሡም ከፈተው፤ ኤልሳዕም “ፍላጻውን አስፈንጥር!” አለው፤ ንጉሡም ፍላጻውን እንዳስፈነጠረ ወዲያውኑ ኤልሳዕ፥ “ፍላጻ ነህ፤ በአንተም አማካይነት እግዚአብሔር ሶርያውያንን ድል ያደርጋል፤ ሶርያውያንን ድል እስክትነሣቸው ድረስ በአፌቅ ከተማ ትወጋቸዋለህ።” ከዚህም በኋላ ኤልሳዕ ንጉሡን “ሌሎቹንም ፍላጻዎች አንሥተህ በእነርሱ ምድርን ምታ!” አለው። ንጉሡም ምድርን ሦስት ጊዜ መትቶ አቆመ፤ ይህም ኤልሳዕን አስቈጣው፤ ስለዚህም ንጉሡን “አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መተህ ቢሆን ኖሮ በሶርያውያን ላይ ፍጹም ድልን ትቀዳጅ ነበር፤ አሁን ግን ሦስት ጊዜ ብቻ ድል ትነሣቸዋለህ” አለው። ኤልሳዕም ሞተ፤ ተቀበረም። ከሞአብ የሚመጡ አደጋ ጣዮች በየዓመቱ የእስራኤልን ምድር ይወሩ ነበር። አንድ ጊዜ የአንድ ሰው ሥርዓተ ቀብር በሚፈጽምበት ሰዓት ከእነዚያ አደጋ ጣዮች መካከል አንድ ቡድን ሲመጣ ስለ ታየ፥ የሚቀበረውን ሬሳ ወደ ኤልሳዕ መቃብር ውስጥ በችኰላ በመወርወር ጥለውት ሸሹ፤ ያም ሬሳ ከኤልሳዕ አስከሬን ጋር በተገናኘበት ቅጽበት ወዲያውኑ ከሞት ተነሥቶ ቆመ።
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 13 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 13:10-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos