2 ነገሥት 13:10-21
2 ነገሥት 13:10-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአስ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ዐሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ። በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኀጢአት አልራቀም፤ ነገር ግን በእርስዋ ሄደ። የቀረውም የዮአስ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ከይሁዳም ንጉሥ ከአሜስያስ ጋር የተዋጋበት ኀይሉ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ዮአስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ኢዮርብዓምም በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ዮአስም በሰማርያ ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ። ኤልሳዕም በሚሞትበት በሽታ ታመመ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ ወደ እርሱ ወርዶ በፊቱ አለቀሰና፥ “አባቴ ሆይ፥ አባቴ ሆይ፥ የእስራኤል ሰረገላቸውና ፈረሰኛቸው” አለ። ኤልሳዕም፥ “ቀስትህንና ፍላጻዎችህን ውሰድ” አለው፤ ቀስቱንና ፍላጻዎቹንም ወሰደ። የእስራኤልንም ንጉሥ አለው፥ “እጅህን በቀስቱ ላይ ጫን።” ዮአስም እጁን በቀስቱ ላይ ጫነ፤ ኤልሳዕም እጁን በንጉሡ እጅ ላይ ጫነ፦ “የምሥራቁንም መስኮት ክፈት” አለ፤ ከፈተውም። ኤልሳዕም፥ “ወርውር” አለው፤ ወረወረውም እርሱም፥ “የእግዚአብሔር መድኀኒት ፍላጻ ነው፤ ከሶርያ የመዳን ፍላጻ ነው፤ እስክታጠፋቸውም ድረስ ሶርያውያንን በአፌቅ ትመታለህ” አለ። ኤልሳዕም ደግሞ፥ “ፍላጻዎችህን ውሰድ” አለው ወሰዳቸውም። የእስራኤልንም ንጉሥ፥ “ምድሩን ምታው” አለው። ንጉሡም ሦስት ጊዜ መትቶ ቆመ። የእግዚአብሔርም ሰው አዝኖ፥ “አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መትተኸው ቢሆን ኖሮ ሶርያውያንን እስክታጠፋቸው ድረስ በመታኻቸው ነበር፤ አሁን ግን ሦስት ጊዜ ብቻ ሶርያን ትመታለህ” አለ። ኤልሳዕም ሞተ፤ ቀበሩትም። ከሞዓብም አደጋ ጣዮች በየዓመቱ መጀመሪያ ወደ ሀገሩ ይገቡ ነበር። ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዮችን አዩ፤ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ላይ ጣሉት፤ የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውዬው ድኖ በእግሩ ቆመ።
2 ነገሥት 13:10-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአስ ዘመን፣ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት፣ የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በሰማርያ ከተማ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ዐሥራ ስድስት ዓመትም ገዛ። እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠራ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ከአሳተበት ኀጢአት ሁሉ አልራቀም፤ በዚያው ገፋበት። ዮአስ በዘመነ መንግሥቱ ያከናወነው ሌላ ሥራ፣ ያደረገውና የፈጸመው ሁሉ እንዲሁም በይሁዳ ንጉሥ በአሜስያስ ላይ ያካሄደው ጦርነት ጭምር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? ዮአስም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ ኢዮርብዓም በእግሩ ተተክቶ በዙፋኑ ተቀመጠ። ዮአስም በሰማርያ ከእስራኤል ነገሥታት ጋራ ተቀበረ። በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ ለሞት ባደረሰው ሕመም ታምሞ ነበር። የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ ሊጠይቀው ወርዶ አለቀሰለት፤ “ወየው አባቴን! ወየው አባቴን! ወየው የእስራኤል ሠረገሎችና ፈረሰኞች!” እያለም ጮኸ። ኤልሳዕም፣ “አንድ ቀስትና ፍላጾች አምጣ” አለው፤ እርሱም አመጣ፤ የእስራኤልንም ንጉሥ፣ “ቀስቱን በእጅህ ያዘው” አለው፤ ቀስቱን በያዘውም ጊዜ ኤልሳዕ እጆቹን በንጉሡ እጆች ላይ አኖረ። ቀጥሎም፣ “የምሥራቁን መስኮት ክፈት” አለው፤ ከፈተውም፤ ኤልሳዕም፣ “በል አስፈንጥረው” አለው፤ አስፈነጠረውም፤ ከዚያም፣ “የእግዚአብሔር የድል ቀስት! ሶርያ ድል የምትሆንበት ቀስት!” አለ። ኤልሳዕም እንደ ገና “ሶርያውያንንም አፌቅ ላይ ፈጽመህ ድል ታደርጋቸዋለህ” አለው። ቀጥሎም፣ “በል ቀስቶቹን ውሰድ” አለው፤ የእስራኤልም ንጉሥ ወሰደ። ኤልሳዕም፣ “መሬቱን ውጋ” አለው፤ እርሱም ሦስት ጊዜ ወግቶ አቆመ። የእግዚአብሔርም ሰው ተቈጣውና፣ “መሬቱን ዐምስት ወይም ስድስት ጊዜ መውጋት ነበረብህ፤ እንዲህ ብታደርግ ኖሮ ሶርያን ታሸንፍና ፈጽመህ ትደመስሳት ነበር፤ አሁን ግን የምታሸንፈው ሦስት ጊዜ ብቻ ነው” አለው። ኤልሳዕ ሞተ፤ ቀበሩትም። በዚህም ጊዜ ሞዓባውያን አደጋ ጣዮች በየዓመቱ በጸደይ ወራት ወደ እስራኤል ምድር እየሰረጉ ይገቡ ነበር። አንድ ጊዜ እስራኤላውያን ሰው ሞቶ ሲቀብሩ፣ አንድ የአደጋ ጣይ ቡድን በድንገት አዩ፤ ስለዚህ የሞተውን ሰው ሬሳ ኤልሳዕ መቃብር ውስጥ ጣሉት፤ ሬሳው የኤልሳዕን ዐፅም እንደ ነካም ወዲያውኑ ሰውየው ድኖ በእግሩ ቆመ።
2 ነገሥት 13:10-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአስ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ነገሠ፤ ዐሥራ ስድስትም ዓመት ነገሠ። በእግዚአብሔር ፊት ክፋ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን በሳተው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም ኀጢአት ሁሉ ሄደ እንጂ ከእርስዋ አልራቀም። የቀረውም የዮአስ ነገር ያደረገውም ሁሉ፥ ከይሁዳም ከአሜስያስ ጋር የተዋጋበት ጭከና፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ዮአስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ኢዮርብዓምም በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ዮአስም በሰማርያ ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ። ኤልሳዕም በሚሞትበት በሽታ ታመመ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ ወደ እርሱ ወርዶ በፊቱ አለቀሰና “አባቴ ሆይ! አባቴ ሆይ! የእስራኤል ሠረገላና ፈረሰኞች፤” አለ። ኤልሳዕም “ቀስትና ፍላጻዎች ውሰድ፤” አለው፤ ቀስቱንና ፍላጻዎችንም ወሰደ። የእስራኤልንም ንጉሥ “እጅህን በቀስቱ ላይ ጫን፤” አለው። እጁንም ጫነበት፤ ኤልሳዕም እጁን በንጉሡ እጅ ላይ ጭኖ “የምሥራቁን መስኮት ክፈት፤” አለ፤ ከፈተውም። ኤልሳዕም “ወርውር!” አለ፤ ወረወረውም። እርሱም “የእግዚአብሔር መድኃኒት ፍላጻ ነው፤ በሶርያ ላይ የመድኃኒት ፍላጻ ነው፤ እስክታጠፋቸው ድረስ ሶርያውያንን በአፌቅ ትመታለህ፤” አለ። ደግሞም “ፍላጻዎቹን ውሰድ፤” አለው፤ ወሰዳቸውም። የእስራኤልንም ንጉሥ “ምድሩን ምታው፤” አለው። ሦስት ጊዜም መትቶ ቆመ። የእግዚአብሔርም ሰው ተቆጥቶ “አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መትተኸው ቢሆን ኖሮ ሶርያን እስክታጠፋው ድረስ በመታኸው ነበር፤ አሁን ግን ሦስት ጊዜ ብቻ ሶርያን ትመታለህ፤” አለ። ኤልሳዕም ሞተ፤ ቀበሩትም። ከሞዓብም አደጋ ጣዮች በየዓመቱ ወደ አገሩ ይገቡ ነበር። ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዮችን አዩ፤ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ውስጥ ጣሉት፤ የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውዮው ድኖ በእግሩ ቆመ።
2 ነገሥት 13:10-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአስ በነገሠ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ። እርሱም እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ ምሳሌነት በመከተል ኃጢአት በመሥራቱ እግዚአብሔርን አሳዘነ። ዮአስ የፈጸመው ሌላው ነገር ሁሉ እንዲሁም በይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ ላይ ባደረገው ጦርነት የፈጸመው ጀግንነት ጭምር በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። ከዚህ በኋላ ዮአስ ሞተ፤ በሰማርያም በሚገኘው መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ዳግማዊ ኢዮርብዓም ነገሠ። ነቢዩ ኤልሳዕ በብርቱ ደዌ ታሞ ነበር፤ ተኝቶም ሊሞት በሚያጣጥርበት ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ሊጠይቀው ሄዶ፥ ድምፁን ከፍ በማድረግ “አባቴ ሆይ! አባቴ ሆይ! አንተ እኮ የእስራኤል ሕዝብ ኀይላቸውና ጋሻ መከታቸው ነህ!” እያለ አለቀሰለት። ኤልሳዕም ንጉሡን “አንድ ቀስትና ፍላጻዎች ውሰድ” ሲል አዘዘው፤ ዮአስም እንደታዘዘው አደረገ፤ ኤልሳዕም “ፍላጻዎቹን ለማስፈንጠር ተዘጋጅ” አለው፤ ንጉሡም እንደታዘዘው አደረገ፤ ኤልሳዕም እጆቹን በንጉሡ እጆች ላይ አኖረ። ኤልሳዕ “የምሥራቁን መስኮት ክፈት” አለ፤ ንጉሡም ከፈተው፤ ኤልሳዕም “ፍላጻውን አስፈንጥር!” አለው፤ ንጉሡም ፍላጻውን እንዳስፈነጠረ ወዲያውኑ ኤልሳዕ፥ “ፍላጻ ነህ፤ በአንተም አማካይነት እግዚአብሔር ሶርያውያንን ድል ያደርጋል፤ ሶርያውያንን ድል እስክትነሣቸው ድረስ በአፌቅ ከተማ ትወጋቸዋለህ።” ከዚህም በኋላ ኤልሳዕ ንጉሡን “ሌሎቹንም ፍላጻዎች አንሥተህ በእነርሱ ምድርን ምታ!” አለው። ንጉሡም ምድርን ሦስት ጊዜ መትቶ አቆመ፤ ይህም ኤልሳዕን አስቈጣው፤ ስለዚህም ንጉሡን “አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መተህ ቢሆን ኖሮ በሶርያውያን ላይ ፍጹም ድልን ትቀዳጅ ነበር፤ አሁን ግን ሦስት ጊዜ ብቻ ድል ትነሣቸዋለህ” አለው። ኤልሳዕም ሞተ፤ ተቀበረም። ከሞአብ የሚመጡ አደጋ ጣዮች በየዓመቱ የእስራኤልን ምድር ይወሩ ነበር። አንድ ጊዜ የአንድ ሰው ሥርዓተ ቀብር በሚፈጽምበት ሰዓት ከእነዚያ አደጋ ጣዮች መካከል አንድ ቡድን ሲመጣ ስለ ታየ፥ የሚቀበረውን ሬሳ ወደ ኤልሳዕ መቃብር ውስጥ በችኰላ በመወርወር ጥለውት ሸሹ፤ ያም ሬሳ ከኤልሳዕ አስከሬን ጋር በተገናኘበት ቅጽበት ወዲያውኑ ከሞት ተነሥቶ ቆመ።
2 ነገሥት 13:10-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአስ በነገሠ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ። እርሱም እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ ምሳሌነት በመከተል ኃጢአት በመሥራቱ እግዚአብሔርን አሳዘነ። ዮአስ የፈጸመው ሌላው ነገር ሁሉ እንዲሁም በይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ ላይ ባደረገው ጦርነት የፈጸመው ጀግንነት ጭምር በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። ከዚህ በኋላ ዮአስ ሞተ፤ በሰማርያም በሚገኘው መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ዳግማዊ ኢዮርብዓም ነገሠ። ነቢዩ ኤልሳዕ በብርቱ ደዌ ታሞ ነበር፤ ተኝቶም ሊሞት በሚያጣጥርበት ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ሊጠይቀው ሄዶ፥ ድምፁን ከፍ በማድረግ “አባቴ ሆይ! አባቴ ሆይ! አንተ እኮ የእስራኤል ሕዝብ ኀይላቸውና ጋሻ መከታቸው ነህ!” እያለ አለቀሰለት። ኤልሳዕም ንጉሡን “አንድ ቀስትና ፍላጻዎች ውሰድ” ሲል አዘዘው፤ ዮአስም እንደ ታዘዘው አደረገ፤ ኤልሳዕም “ፍላጻዎቹን ለማስፈንጠር ተዘጋጅ” አለው፤ ንጉሡም እንደ ታዘዘው አደረገ፤ ኤልሳዕም እጆቹን በንጉሡ እጆች ላይ አኖረ። ኤልሳዕ “የምሥራቁን መስኮት ክፈት” አለ፤ ንጉሡም ከፈተው፤ ኤልሳዕም “ፍላጻውን አስፈንጥር!” አለው፤ ንጉሡም ፍላጻውን እንዳስፈነጠረ ወዲያውኑ ኤልሳዕ፥ “ፍላጻ ነህ፤ በአንተም አማካይነት እግዚአብሔር ሶርያውያንን ድል ያደርጋል፤ ሶርያውያንን ድል እስክትነሣቸው ድረስ በአፌቅ ከተማ ትወጋቸዋለህ።” ከዚህም በኋላ ኤልሳዕ ንጉሡን “ሌሎቹንም ፍላጻዎች አንሥተህ በእነርሱ ምድርን ምታ!” አለው። ንጉሡም ምድርን ሦስት ጊዜ መትቶ አቆመ፤ ይህም ኤልሳዕን አስቆጣው፤ ስለዚህም ንጉሡን “አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መተህ ቢሆን ኖሮ በሶርያውያን ላይ ፍጹም ድልን ትቀዳጅ ነበር፤ አሁን ግን ሦስት ጊዜ ብቻ ድል ትነሣቸዋለህ” አለው። ኤልሳዕም ሞተ፤ ተቀበረም። ከሞዓብ የሚመጡ አደጋ ጣዮች በየዓመቱ የእስራኤልን ምድር ይወሩ ነበር። አንድ ጊዜ የአንድ ሰው ሥርዓተ ቀብር በሚፈጽምበት ሰዓት ከእነዚያ አደጋ ጣዮች መካከል አንድ ቡድን ሲመጣ ስለ ታየ፥ የሚቀበረውን ሬሳ ወደ ኤልሳዕ መቃብር ውስጥ በችኰላ በመወርወር ጥለውት ሸሹ፤ ያም ሬሳ ከኤልሳዕ አስከሬን ጋር በተገናኘበት ቅጽበት ወዲያውኑ ከሞት ተነሥቶ ቆመ።