መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 13
13
የእስራኤል ንጉሥ ኢዮአካዝ
1በይሁዳ ንጉሥ በአካዝያስ ልጅ በኢዮአስ በሃያ ሦስተኛው ዓመት የኢዩ ልጅ ኢዮአካዝ በሰማርያ ነገሠ፤ ዐሥራ ሰባት ዓመትም ነገሠ። 2በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልንም ያሳተውን የናባጥን ልጅ የኢዮርብዓምን ኀጢአት ተከተለ፤ ከእርስዋም አልራቀም። 3እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ በጣም ተቈጣ፤ በዘመኑም ሁሉ በሶርያው ንጉሥ በአዛሄል እጅ፥ በአዛሄልም ልጅ በወልደ አዴር እጅ አሳልፎ ሰጣቸው። 4ኢዮአካዝም እግዚአብሔርን ለመነ፤ እግዚአብሔርም የሶርያ ንጉሥ እስራኤልን ያስጨነቀበትን ጭንቀት አይቶአልና ሰማው። 5እግዚአብሔርም ለእስራኤል ታዳጊን ሰጠ፤ ከሶርያውያንም እጅ ዳኑ፤ የእስራኤልም ልጆች እንደ ቀድሞው ጊዜ በድንኳናቸው ተቀመጡ። 6ነገር ግን በእርስዋ ሄዱ እንጂ እስራኤልን ካሳተበት ከኢዮርብዓም ቤት ኀጢአት አልራቁም፤ ደግሞም የማምለኪያ ዐፀድ በሰማርያ ቆሞ ነበረ። 7ለኢዮአካዝም ከኀምሳ ፈረሰኞች፥ ከዐሥርም ሰረገሎች፥ ከዐሥር ሺህም እግረኞች በቀር ሕዝብ አልቀረለትም፤ የሶርያ ንጉሥ አጥፍቶአቸዋልና፥ በአውድማም እንዳለ ዕብቅ አድቅቆአቸዋልና። 8የቀረውም የኢዮአካዝ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ኀይሉም፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 9ኢዮአካዝም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በሰማርያም ቀበሩት፥ ልጁም ዮአስ በፋንታው ነገሠ።
10በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአስ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ዐሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ። 11በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኀጢአት አልራቀም፤ ነገር ግን በእርስዋ ሄደ። 12የቀረውም የዮአስ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ከይሁዳም ንጉሥ ከአሜስያስ ጋር የተዋጋበት ኀይሉ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 13ዮአስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ኢዮርብዓምም በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ዮአስም በሰማርያ ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ።
የነቢዩ ኤልሳዕ ሞት
14ኤልሳዕም በሚሞትበት በሽታ ታመመ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ ወደ እርሱ ወርዶ በፊቱ አለቀሰና፥ “አባቴ ሆይ፥ አባቴ ሆይ፥ የእስራኤል ሰረገላቸውና ፈረሰኛቸው” አለ። 15ኤልሳዕም፥ “ቀስትህንና ፍላጻዎችህን ውሰድ” አለው፤ ቀስቱንና ፍላጻዎቹንም ወሰደ። 16የእስራኤልንም ንጉሥ አለው፥ “እጅህን በቀስቱ ላይ ጫን።” ዮአስም እጁን በቀስቱ ላይ ጫነ፤ ኤልሳዕም እጁን በንጉሡ እጅ ላይ ጫነ፦ 17“የምሥራቁንም መስኮት ክፈት” አለ፤ ከፈተውም። ኤልሳዕም፥ “ወርውር” አለው፤ ወረወረውም እርሱም፥ “የእግዚአብሔር መድኀኒት ፍላጻ ነው፤ ከሶርያ የመዳን ፍላጻ ነው፤ እስክታጠፋቸውም ድረስ ሶርያውያንን በአፌቅ ትመታለህ” አለ። 18ኤልሳዕም ደግሞ፥ “ፍላጻዎችህን ውሰድ” አለው ወሰዳቸውም። የእስራኤልንም ንጉሥ፥ “ምድሩን ምታው” አለው። ንጉሡም ሦስት ጊዜ መትቶ ቆመ። 19የእግዚአብሔርም ሰው አዝኖ፥ “አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መትተኸው ቢሆን ኖሮ ሶርያውያንን እስክታጠፋቸው ድረስ በመታኻቸው ነበር፤ አሁን ግን ሦስት ጊዜ ብቻ ሶርያን ትመታለህ” አለ።
20ኤልሳዕም ሞተ፤ ቀበሩትም። ከሞዓብም አደጋ ጣዮች በየዓመቱ መጀመሪያ ወደ ሀገሩ ይገቡ ነበር። 21ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዮችን አዩ፤ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ላይ ጣሉት፤ የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውዬው ድኖ በእግሩ ቆመ።
22አዛሄልም በኢዮአካዝ ዘመን ሁሉ እስራኤልን አስጨነቀ፤ 23እግዚአብሔር ግን ራራላቸው፤ ማራቸውም፤ ከአብርሃምና ከይስሐቅ፥ ከያዕቆብም ጋር ስላደረገው ቃል ኪዳን እነርሱን ተመለከተ፤ ሊያጠፋቸውም አልወደደም፤ ፈጽሞም ከፊቱ አልጣላቸውም። 24የሶርያም ንጉሥ አዛሄል ሞተ፤ ልጁም ወልደ አዴር በፋንታው ነገሠ። 25አዛሄልም ከአባቱ ከኢዮአካዝ እጅ በሰልፍ የወሰዳቸውን ከተሞች የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ መልሶ ከአዛሄል ልጅ ከወልደ አዴር እጅ ወሰደ። ዮአስም ሦስት ጊዜ መታው፤ የእስራኤልንም ከተሞች መለሰ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 13: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ