የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 13

13
የእስራኤል ንጉሥ ኢዮአካዝ
1የአካዝያስ ልጅ ኢዮአስ በይሁዳ በነገሠ በሃያ ሦስተኛው ዓመት የኢዩ ልጅ ኢዮአካዝ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ ዐሥራ ሰባት ዓመት ገዛ፤ 2እርሱም ከእርሱ በፊት እንደ ነበረው እንደ ንጉሥ ኢዮርብዓም ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ እስራኤልንም ወደ ኃጢአት መራ፤ ከክፉ ሥራውም ከቶ አልተገታም። 3ስለዚህም እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ ላይ ተቈጥቶ ለሶርያ ንጉሥ አዛሄል፥ እንዲሁም ለልጁ ለቤንሀዳድ በተደጋጋሚ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋል። 4ከዚህ በኋላ ኢዮአካዝ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም የሶርያ ንጉሥ በእስራኤላውያን ላይ የፈጸመባቸው ግፍ እጅግ ከባድ መሆኑን ተመልክቶ የኢዮአካዝን ጸሎት ሰማ። 5ስለዚህም እግዚአብሔር እስራኤልን ከሶርያውያን እጅ ነጻ የሚያወጣቸው መሪ ላከላቸው፤ እነርሱም ከዚያ በፊት በነበረው ዐይነት በሰላም ኖሩ። 6ይህም ሁሉ ሆኖ ንጉሥ ኢዮርብዓም እስራኤልን ወደ ኃጢአት ከመራበት ከበደል ሥራቸው አልተመለሱም፤ ይህን በማድረግ ፈንታ በኃጢአታቸው ጸንተው አሼራ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ ምስል በሰማርያ ማምለክ ቀጠሉ።
7ንጉሥ ኢዮአካዝ ከኀምሳ ፈረሰኞች፥ ከዐሥር ሠረገሎችና ከዐሥር ሺህ ወታደሮች በቀር ሌላ የተደራጀ የጦር ኀይል አልነበረውም፤ ይህም የሆነበት ምክንያት ሌላውን ሠራዊቱን የሶርያ ንጉሥ በአውድማ እንዳለ እብቅ ስለ ደመሰሰበት ነው።
8ንጉሥ ኢዮአካዝ የፈጸመው ሌላው ተግባርና የጀግንነት ሥራው ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። 9ኢዮአካዝ ሞተ፤ በሰማርያም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ዮአስ ነገሠ።
የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ
10የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአስ በነገሠ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ። 11እርሱም እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ ምሳሌነት በመከተል ኃጢአት በመሥራቱ እግዚአብሔርን አሳዘነ። 12ዮአስ የፈጸመው ሌላው ነገር ሁሉ እንዲሁም በይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ ላይ ባደረገው ጦርነት የፈጸመው ጀግንነት ጭምር በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። 13ከዚህ በኋላ ዮአስ ሞተ፤ በሰማርያም በሚገኘው መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ዳግማዊ ኢዮርብዓም ነገሠ።
የኤልሳዕ መሞት
14ነቢዩ ኤልሳዕ በብርቱ ደዌ ታሞ ነበር፤ ተኝቶም ሊሞት በሚያጣጥርበት ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ሊጠይቀው ሄዶ፥ ድምፁን ከፍ በማድረግ “አባቴ ሆይ! አባቴ ሆይ! አንተ እኮ የእስራኤል ሕዝብ ኀይላቸውና ጋሻ መከታቸው ነህ!” እያለ አለቀሰለት። #2ነገ. 2፥12።
15ኤልሳዕም ንጉሡን “አንድ ቀስትና ፍላጻዎች ውሰድ” ሲል አዘዘው፤ ዮአስም እንደታዘዘው አደረገ፤ 16ኤልሳዕም “ፍላጻዎቹን ለማስፈንጠር ተዘጋጅ” አለው፤ ንጉሡም እንደታዘዘው አደረገ፤ ኤልሳዕም እጆቹን በንጉሡ እጆች ላይ አኖረ። 17ኤልሳዕ “የምሥራቁን መስኮት ክፈት” አለ፤ ንጉሡም ከፈተው፤ ኤልሳዕም “ፍላጻውን አስፈንጥር!” አለው፤ ንጉሡም ፍላጻውን እንዳስፈነጠረ ወዲያውኑ ኤልሳዕ፥ “ፍላጻ ነህ፤ በአንተም አማካይነት እግዚአብሔር ሶርያውያንን ድል ያደርጋል፤ ሶርያውያንን ድል እስክትነሣቸው ድረስ በአፌቅ ከተማ ትወጋቸዋለህ።”
18ከዚህም በኋላ ኤልሳዕ ንጉሡን “ሌሎቹንም ፍላጻዎች አንሥተህ በእነርሱ ምድርን ምታ!” አለው። ንጉሡም ምድርን ሦስት ጊዜ መትቶ አቆመ፤ 19ይህም ኤልሳዕን አስቈጣው፤ ስለዚህም ንጉሡን “አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መተህ ቢሆን ኖሮ በሶርያውያን ላይ ፍጹም ድልን ትቀዳጅ ነበር፤ አሁን ግን ሦስት ጊዜ ብቻ ድል ትነሣቸዋለህ” አለው።
20ኤልሳዕም ሞተ፤ ተቀበረም።
ከሞአብ የሚመጡ አደጋ ጣዮች በየዓመቱ የእስራኤልን ምድር ይወሩ ነበር። 21አንድ ጊዜ የአንድ ሰው ሥርዓተ ቀብር በሚፈጽምበት ሰዓት ከእነዚያ አደጋ ጣዮች መካከል አንድ ቡድን ሲመጣ ስለ ታየ፥ የሚቀበረውን ሬሳ ወደ ኤልሳዕ መቃብር ውስጥ በችኰላ በመወርወር ጥለውት ሸሹ፤ ያም ሬሳ ከኤልሳዕ አስከሬን ጋር በተገናኘበት ቅጽበት ወዲያውኑ ከሞት ተነሥቶ ቆመ።
በእስራኤልና በሶርያ መካከል የተደረገ ጦርነት
22ኢዮአካዝ በነገሠበት ዘመን ሁሉ የሶርያ ንጉሥ አዛሄል እስራኤላውያንን በመጨቈን ያስጨንቃቸው ነበር፤ 23እግዚአብሔር ግን በቸርነቱ ምሕረትን በማድረግ ረዳቸው እንጂ እንዲደመሰሱ አልፈቀደም፤ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ የሰጠውን ቃል ኪዳን በማሰብ ሕዝቡን ስላልረሳው ነው።
24የሶርያ ንጉሥ አዛሄል በሞተ ጊዜ፥ በእርሱ እግር ተተክቶ ልጁ ቤንሀዳድ ነገሠ። 25ከዚህም በኋላ የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ቤንሀዳድን ሦስት ጊዜ ድል ነሥቶ በአባቱ በኢዮአካዝ ዘመነ መንግሥት ቤንሀዳድ ይዞአቸው የነበሩትን ከተሞች አስመለሰ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ