የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 14

14
የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ
(2ዜ.መ. 25፥1-24)
1የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በእስራኤል ላይ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ 2በነገሠም ጊዜ ዕድሜው ኻያ አምስት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ኻያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ፤ እናቱም ከኢየሩሳሌም ይሆዓዲን ተብላ የምትጠራ ነበረች። 3አሜስያስ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠርቶአል፤ ይሁን እንጂ እንደ ቀድሞ አያቱ እንደ ንጉሥ ዳዊት አልነበረም፤ እንደ ዳዊት በመሆን ፈንታ የአባቱን የኢዮአስን ፈለግ ተከተለ። 4ይኸውም በየኰረብታዎች ላይ የተሠሩትን የአሕዛብ ማምለኪያዎችን አላፈረሰም፤ ከዚህም የተነሣ ሕዝቡ በየኮረብታዎቹ መሥዋዕት ማቅረቡንና ዕጣን ማጠኑን እንደ ቀጠለ ነበር።
5አሜስያስ መንግሥቱን አደላድሎ እንደ ያዘ ወዲያውኑ፥ ቀደም ሲል ነግሦ የነበረውን አባቱን የገደሉትን ባለሥልጣኖች በሞት ቀጣ፤ 6ይሁን እንጂ ልጆቻቸውን አልገደለም፤ ይልቁንም በኦሪት ሕግ እግዚአብሔር “ልጆቻቸው በፈጸሙት ኃጢአት ወላጆች በሞት አይቀጡበትም፤ ወላጆችም በፈጸሙት ኃጢአት ልጆች በሞት አይቀጡበትም፤ እያንዳንዱ ሰው ራሱ በፈጸመው ወንጀል ብቻ በሞት ይቀጣ” ሲል የሰጠውን ትእዛዝ ፈጽሞአል። #ዘዳ. 24፥16።
7አሜስያስ “የጨው ሸለቆ” እየተባለ በሚጠራው ስፍራ ዐሥር ሺህ የሚሆኑ የኤዶም ወታደሮችን ፈጀ፤ ሴላዕ ተብላ የምትጠራውንም ከተማ ይዞ “ዮቅትኤል” ብሎ ጠራት፤ እስከ አሁንም በዚሁ ስም ትጠራለች።
8ከዚህ በኋላ አሜስያስ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዩ ልጅ ወደ ዮአስ መልእክተኞች በመላክ “እንግዲህ ና ይዋጣልን!” ሲል ለጦርነት አነሣሣው፤ 9ንጉሥ ዮአስ ግን እንዲህ ሲል መለሰለት “አንድ ጊዜ በሊባኖስ ተራራ ላይ የምትገኝ ኲርንችት የሊባኖስ ዛፍ ‘ለወንድ ልጄ ሚስት ትሆነው ዘንድ ሴት ልጅህን ስጠኝ’ ስትል መልእክት ላከችበት፤ ነገር ግን አንድ የሊባኖስ አውሬ እግረ መንገዱን በዚያ ሲያልፍ ስለ ረገጣት ያቺ ኲርንችት ሞተች፤ 10አሜስያስ ሆይ! እነሆ፥ አንተም ኤዶማውያንን ድል ስላደረግህ ልብህ በትዕቢት ተሞልቶአል፤ በአገኘኸውም ድል በመደሰት ዐርፈህ በቤትህ ብትቀመጥ ይሻልሃል፤ በአንተና በሕዝብህ ላይ መቅሠፍትን የሚያስከትል ነገር ለመቈስቈስ ስለምን ትፈልጋለህ?”
11አሜስያስ ግን የዮአስን መልስ ከምንም አልቈጠረውም፤ ስለዚህም ንጉሥ ዮአስ ሠራዊቱን አስከትሎ በአሜስያስ ላይ በመዝመት በይሁዳ ምድር በምትገኘው በቤትሼሜሽ ጦርነት ገጠመው፤ 12ይሁዳም ድል ተመታ፤ ወታደሮቹም ሁሉ ተበታትነው ወደየቤታቸው ተመለሱ። 13ዮአስም የአካዝያስን ልጅ፥ የኢዮአስን ልጅ አሜስያስን ከነሕይወቱ ማረከው፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ለመድረስ ገሠገሠ፤ እዚያም እንደ ደረሰ ከኤፍሬም ቅጽር በር “የማእዘን ቅጽር በር” ተብሎ እስከሚጠራው በር ድረስ ጠቅላላ ርዝመቱ ሁለት መቶ ሜትር የሆነውን የቅጽር ግንብ አፈረሰ። 14በዚያም ያገኘውን ወርቅና ብር ሁሉ፥ የቤተ መቅደሱን ንዋያተ ቅድሳትና የቤተ መንግሥቱን ሀብት ሁሉ ጭኖ ወደ ሰማርያ ተመለሰ፤ በመያዣ ስም የተማረኩ ሰዎችንም ይዞ ሄደ።
15ንጉሥ ዮአስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ እንዲሁም በይሁዳ ንጉሥ በአሜስያስ ላይ ባደረገው ጦርነት የፈጸመው የጀግንነት ሥራ ጭምር በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። 16ዮአስ ሞተ፤ በሰማርያ በሚገኘውም የነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ዳግማዊ ኢዮርብዓም ነገሠ።
የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ መሞት
(2ዜ.መ. 25፥25-28)
17የእስራኤል ንጉሥ የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ ከሞተ በኋላ፥ የይሁዳ ንጉሥ የዮአስ ልጅ አሜስያስ ዐሥራ አምስት ዓመት ቈየ፤ 18አሜስያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል።
19አሜስያስን ለመግደል በኢየሩሳሌም ሤራ ተጠንስሶ ነበር፤ ስለዚህ አሜስያስ ሸሽቶ ወደ ላኪሽ ከተማ ሄደ፤ ነገር ግን ጠላቶች ወደ ላኪሽ ሰዎችን ልከው እዚያ አስገደሉት። 20ሬሳውም በፈረስ ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘውም የነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ። 21የይሁዳም ሕዝብ ዐሥራ ስድስት ዓመት ዕድሜ የነበረውን ልጁን ዖዝያን አነገሡ፤ 22ዖዝያም ቀድሞ ተይዛ የነበረችውን ኤላትን ከአባቱ ሞት በኋላ በጦር ኀይል ድል ነሥቶ በማስመለስ እንደገና ሠራት።
የእስራኤል ንጉሥ ዳግማዊ ኢዮርብዓም
23የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ በይሁዳ በነገሠ በዐሥራ አምስተኛው ዓመት የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓም በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ አርሱም መኖሪያውን በሰማርያ አድርጎ አርባ አንድ ዓመት ገዛ። 24ዳግማዊ ኢዮርብዓምም እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ ከእርሱ በፊት የነበረውን የናባጥ ልጅ የኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት በመከተል ኃጢአት በመሥራቱ እግዚአብሔርን አሳዘነ። 25ቀድሞ የእስራኤል ይዞታ የነበረውን በስተ ሰሜን ከሐማት መተላለፊያ ጀምሮ በስተ ደቡብ እስከ ሙት ባሕር የሚገኘውን ግዛት ሁሉ ድል ነሥቶ እንደገና አስመለሰ፤ ይህም ሁሉ የተፈጸመው በጋትሔፌር ተወላጅ አገልጋይ በሆነው በአሚታይ ልጅ በነቢዩ ዮናስ አማካይነት የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በሰጠው የተስፋ ቃል መሠረት ነው። #ዮናስ 1፥1።
26እግዚአብሔር የእስራኤላውያንን አሠቃቂ መከራ ተመለከተ፤ በእስራኤል ውስጥ ባሪያዎችም ሆኑ ነጻ ሰዎች፥ ረዳት አልነበራቸውም። 27ይሁን እንጂ እነርሱ ለዘለዓለም ፈጽሞ እንዲደመሰሱ ደግሞ የእግዚአብሔር ፈቃድ አልነበረም፤ ስለዚህም በዳግማዊ ኢዮርብዓም አማካይነት አዳናቸው።
28ዳግማዊ ኢዮርብዓም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ፥ በጦርነት ላይ ያሳየው ጀግንነት፥ እንዲሁም የይሁዳ ግዛት የነበሩት ደማስቆና ሐማት ለእስራኤል እንዲመለሱ ያደረገበት ታሪካዊ ዝክረ ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። 29ከዚህ በኋላ ዳግማዊ ኢዮርብዓም ሞተ፤ በነገሥታት መካነ መቃብርም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ዘካርያስ ነገሠ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ