የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 12

12
የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአስ
(2ዜ.መ. 24፥1-16)
1ኢዩ በእስራኤል በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ኢዮአስ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ አርባ ዓመት ገዛ፤ የእርሱ እናት ጺቢያ ተብላ የምትጠራ የቤርሳቤህ ከተማ ተወላጅ ነበረች። 2ካህኑ ዮዳሄ ይመክረውና ያስተምረው ስለ ነበር፥ ኢዮአስ በዕድሜው ዘመን ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ፤ 3ይሁን እንጂ በየኰረብታዎች ላይ የሚገኙት የአሕዛብ ማምለኪያዎች ስላልተደመሰሱ፥ ሕዝቡ በዚያ ዕጣን እያጠኑ መሥዋዕት ማቅረባቸውን እንደ ቀጠሉ ነበር።
4ኢዮአስም ካህናቱን ጠርቶ በቤተ መቅደስ ከሚቀርበው መሥዋዕት ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ መባ ሆኖ የሚገባውን ገንዘብ ሁሉ በጥንቃቄ እንዲጠብቁ አዘዘ፤ ይኸውም ቋሚ ከሆነው ከዘወትር መሥዋዕት ጋር መባ ሆኖ የሚቀርበውንና በበጎ ፈቃድ ሕዝቡ የሚያመጣውን ስጦታ ሁሉ የሚያጠቃልል ነበር።#ዘፀ. 30፥11-16። 5እያንዳንዱ ካህን ከሚያገለግላቸው ሰዎች የሚገኘውን የገንዘብ መባ ሁሉ በጥንቃቄ የመጠበቅ ኀላፊነት ተሰጠው፤ ገንዘቡንም እንዳስፈላጊነቱ ለቤተ መቅደሱ ጥገና አገልግሎት እንዲያውሉት ነገራቸው።
6ነገር ግን ኢዮአስ እስከ ነገሠበት እስከ ኻያ ሦስተኛው ዓመት ድረስ ካህናቱ በቤተ መቅደሱ ላይ ምንም ዐይነት እድሳት አላደረጉም፤ 7ስለዚህም ኢዮአስ ዮዳሄንና ሌሎቹንም ካህናት ወደ እርሱ ጠርቶ “ቤተ መቅደሱን ያላደሳችሁበት ምክንያት ምንድን ነው? ከዛሬ ጀምሮ የምትቀበሉትን ገንዘብ መያዝ የለባችሁም፤ ለቤተ መቅደሱ እድሳት ይውል ዘንድ ገንዘቡን አስረክቡ” አላቸው። 8ካህናቱም በዚህ ተስማምተው ቤተ መቅደሱን ለማደስ የነበራቸውን ተግባር አቆሙ።
9ከዚህ በኋላ ዮዳሄ አንድ ሣጥን ወስዶ በመክደኛው ላይ ቀዳዳ አበጀ፤ ሣጥኑንም ወስዶ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገቡ በስተ ቀኝ በሚገኘው መሠዊያ አጠገብ አኖረው፤ የየዕለቱ ተረኞች የነበሩትም ካህናት ለስግደት የሚመጡት ሰዎች የሚሰጡትን የገንዘብ መባ እየተቀበሉ በሣጥኑ ውስጥ ያስገቡት ነበር፤ 10ሣጥኑም በሚሞላበት ጊዜ የቤተ መንግሥቱ ጸሐፊና ሊቀ ካህናቱ እየመጡ ብሩን በመቊጠር በከረጢት እያሰሩ ያኖሩት ነበር። 11ትክክለኛውንም ሒሳብ አጣርተው ከመዘገቡ በኋላ ለቤተ መቅደሱ እድሳት ሥራ ኀላፊዎች ያስረክቡ ነበር፤ እነርሱም ገንዘቡን ተረክበው ለአናጢዎችና፥ ለግንበኞች ይሰጡ ነበር፥ 12ለድንጋይ ጠራቢዎች፥ ለማደሻ አገልግሎት የሚውል እንጨትና ድንጋይ ለሚገዙና እንዲሁም ለልዩ ልዩ አስፈላጊ ነገሮች ለሚውል ተግባር ሁሉ ይከፍሉ ነበር። 13ሆኖም ከብር ለሚሠሩ ጐድጓዳ ሳሕኖች፥ የዐመድ ማጠራቀሚያ፥ ጐድጓዳ ወጭት፥ እምቢልታ ወይም ደግሞ ከብርም ሆነ ከወርቅ ለሚሠሩ ንዋያተ ቅድሳት ከዚያ ገንዘብ ላይ ተነሥቶ የሚከፈል ሒሳብ አልነበረም። 14ያ ገንዘብ በሙሉ በቤተ መቅደሱ እድሳት ተግባር ላይ ለተሰማሩት ሠራተኞች ብቻ የሚውል ነበር። 15ለሥራው ኀላፊነት የተመረጡትም ሰዎች ፍጹም ታማኞች ስለ ነበሩ ገንዘቡን የሰጡአቸውን ሰዎች አይቈጣጠሩአቸውም ነበር። #2ነገ. 22፥7። 16ስለ በደልና ስለ ኃጢአት መሥዋዕት የሚከፈለው ገንዘብ ግን ለካህናቱ ጥቅም የሚውል እንጂ ወደ ቤተ መቅደሱ ሣጥን ውስጥ አይገባም ነበር። #ዘሌ. 7፥7።
17በዚያን ጊዜ የሶርያ ንጉሥ አዛሄል በጋት ከተማ ላይ አደጋ ጥሎ ያዛት፤ ቀጥሎም በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ለመጣል ወሰነ። 18የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአስም ከእርሱ በፊት የነበሩትን ነገሥታት፥ ማለትም ኢዮሣፍጥ፥ ኢዮራምና አካዝያስ ለእግዚአብሔር ለይተው ያኖሩትን መባና የራሱን መባ ጨምሮ በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥት ግምጃ ቤቶች የነበረውን ወርቅ ሁሉ በመሰብሰብ ገጸ በረከት አድርጎ ለንጉሥ አዛሄል ላከለት፤ ሐዛኤልም ይህን ተቀብሎ ሠራዊቱን ከኢየሩሳሌም መለሰ።
19ንጉሥ ኢዮአስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል።
20-21ከዚህ በኋላ የንጉሥ ኢዮአስ ባለሟሎች የሆኑ ባለሥልጣኖች አደሙበት፤ ከእነርሱም ሁለቱ የሺምዓት ልጅ ዮዛካርና የሾሜር ልጅ ይሆዛባድ ወደ ሲላ በሚወስደው ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ በሚገኘው በተደለደለ መሬት ላይ በተሠራው ቤት ገደሉት፤ ኢዮአስም በዳዊት ከተማ በሚገኘው በነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አሜስያስ ነገሠ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ