የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13:1-14

2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13:1-14 አማ05

እንግዲህ ወደ እናንተ ስመጣ ይህ ሦስተኛዬ ነው፤ መቼም ሁሉ ነገር የሚረጋገጠው በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች ነው። በሁለተኛው ጒብኝቴ ከእናንተ ጋር በነበርኩ ጊዜ በማስጠንቀቅ ተናግሬ ነበር፤ አሁንም ደግሞ በሩቅ ሆኜ ከዚህ ቀደም ኃጢአት ለሠሩትና ለሌሎችም በማስጠንቀቅ እናገራለሁ፤ አሁን ወደ እናንተ ተመልሼ በምመጣበት ጊዜ ለማንም አልራራም፤ እናንተ በእኔ ዐድሮ የሚናገረው ክርስቶስ መሆኑን ለማረጋገጥ ትፈልጋላችሁ፤ በእናንተ ዘንድ የሚታየውም የእርሱ ኀይል ነው እንጂ ድካሙ አይደለም። እርሱ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሞተው በደካማነት ቢሆንም አሁን በእግዚአብሔር ኀይል በሕይወት ይኖራል፤ እኛም ከእርሱ ጋር ደካሞች ሆነናል፤ ከእናንተ ጋር ባለን ግንኙነት ግን ከእርሱ ጋር በእግዚአብሔር ኀይል እንኖራለን። በእምነታችሁ የጸናችሁ መሆናችሁን ለማረጋገጥ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በውስጣችሁ መሆኑን አልተገነዘባችሁምን? አለበለዚያ በፈተና ወድቃችኋል ማለት ነው፤ እኛ በፈተና አለመውደቃችንን እንደምትገነዘቡ ተስፋ እናደርጋለን። ክፉ ነገር እንዳታደርጉ ወደ እግዚአብሔር እንጸልያለን፤ የምንጸልየውም ምንም እንኳ እኛ ብቁዎች ሆነን ሳንታይ ብንቀር እናንተ ዘወትር መልካም የሆነውን ነገር እንድታደርጉ ነው እንጂ የእኛን ብቃት ለማሳየት አይደለም። እኛ ስለ እውነት እንሠራለን እንጂ የእውነት ተቃራኒ የሆነ ምንም ነገር አንሠራም። እኛ ደካሞች ሆነን እናንተ ግን ብርቱዎች ስትሆኑ ደስ ይለናል፤ የእኛ ጸሎት እናንተ ፍጹሞች እንድትሆኑ ነው። ይህን መልእክት ከእናንተ ርቄ ሳለሁ የጻፍኩላችሁ በዚሁ ምክንያት ነው፤ በዚህ ዐይነት ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ ጌታም በሰጠኝ ሥልጣን አላስጨንቃችሁም፤ ጌታ ሥልጣን የሰጠኝ እናንተን ለማነጽ እንጂ እናንተን ለማፍረስ አይደለም። በተረፈውስ ወንድሞቼ ሆይ! ደኅና ሁኑ! አኗኗራችሁን አስተካክሉ፤ ምክሬን ተከተሉ፤ እርስ በእርሳችሁ ተስማሙ፤ በሰላምም ኑሩ፤ የፍቅርና የሰላም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል። በተቀደሰ መሳሳም እየተሳሳማችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ፤ ምእመናን ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፥ የእግዚአብሔር ፍቅር፥ የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን።