ወደ እናንተ ስመጣ ይህ ሦስተኛዬ መሆኑ ነው፤ “ነገር ሁሉ በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች አፍ ስለሚጸና።” በሁለተኛው ጕብኝቴ እናንተ ዘንድ በነበርሁበት ጊዜ አስጠንቅቄአችሁ ነበር፤ አሁንም በሩቅ ሆኜ እንደ ገና አስጠነቅቃችኋለሁ፤ ወደ እናንተም ተመልሼ ስመጣ፣ ከዚህ በፊት ኀጢአት ለሠሩትም ሆነ ለሌሎች አልራራላቸውም፤ ይህም የሚሆነው ክርስቶስ በእኔ ዐድሮ እንደሚናገር ማስረጃ በመፈለጋችሁ ነው። እርሱም በመካከላችሁ ብርቱ እንጂ ደካማ አልነበረም። የተሰቀለው በድካም ቢሆንም፣ በእግዚአብሔር ኀይል ሕያው ሆኖ ይኖራል። እኛም በርሱ ደካሞች ብንሆንም፣ እናንተን ለማገልገል ግን በእግዚአብሔር ኀይል ከርሱ ጋራ ሕያዋን ሆነን እንኖራለን። በእምነት መሆናችሁን ለማወቅ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ። ከፈር የወጣችሁ ካልሆነ በቀር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በውስጣችሁ እንዳለ አታውቁምን? እኛ ግን ብቁ መሆናችንን እንደምትገነዘቡ ተስፋ አደርጋለሁ። አሁንም ምንም ክፉ ነገር እንዳታደርጉ ወደ እግዚአብሔር እንጸልያለን፤ የምንጸልየውም እኛ ብቁዎች እንደ ሆንን ሰዎች እንዲያዩልን አይደለም፤ ነገር ግን እኛ ምንም እንኳ ብቁዎች ባንሆንም እናንተ መልካም የሆነውን ነገር እንድታደርጉ ነው። ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ማድረግ አንችልምና። እኛ ደካሞች ስንሆን፣ እናንተ ግን ብርቱዎች ስትሆኑ ደስ ይለናል፤ ጸሎታችንም እናንተ ፍጹማን እንድትሆኑ ነው። ከእናንተ ርቄ ሳለሁ እነዚህን ነገሮች የምጽፍላችሁ ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ ሥልጣኔን በኀይል እንዳልጠቀም ነው፤ ጌታም ይህን ሥልጣን የሰጠኝ እናንተን ለማነጽ እንጂ ለማፍረስ አይደለም። በተረፈ ወንድሞች ሆይ፤ ደኅና ሁኑ፤ ፍጹማን ሁኑ፤ ምክሬን ስሙ፤ አንድ ሐሳብ ይኑራችሁ፤ በሰላምም ኑሩ። የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋራ ይሆናል። በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋራ ይሁን።
2 ቆሮንቶስ 13 ያንብቡ
ያዳምጡ 2 ቆሮንቶስ 13
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ቆሮንቶስ 13:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos