የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1:8-14

2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1:8-14 አማ05

ወንድሞች ሆይ! በእስያ ክፍለ ሀገር በነበርንበት ጊዜ የደረሰብንን መከራ እንድታውቁ እንወዳለን፤ ይህም የደረሰብን መከራ ልንሸከመው ከምንችለው በላይ ወድቆብን ስለ ነበር በሕይወት ለመኖር የነበረን ተስፋ እንኳ ተቋርጦ ነበር። እንዲያውም ሞት እንደ ተፈረደብን ያኽል ተሰምቶን ነበር፤ ይህም ሁሉ የደረሰብን፥ የምንተማመነው ሙታንን በሚያስነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን ኀይል አለመሆኑን እንድንገነዘብ ነው። ስለዚህ እርሱ ለሞት ከሚያደርስ አደጋ አድኖናል፤ ያድነናልም፤ ደግሞም እንደሚያድነን ተስፋችን በእርሱ ነው። እናንተም እኛን በጸሎት ልትረዱን ይገባል፤ በብዙ ጸሎት እኛ የእግዚአብሔርን ርዳታ ስናገኝ ብዙ ሰዎች ደግሞ በእኛ ምክንያት እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ። የምንመካበት ነገር ይህ ነው፤ ይህም እውነት መሆኑን ኅሊናችን ይመሰክርልናል፤ ከሌሎች ሰዎችና በተለይም ከእናንተ ጋር የነበረን ግንኙነት ከእግዚአብሔር ባገኘነው ቅድስናና ቅንነት የተመሠረተ ነው፤ ይህም የሆነው በእግዚአብሔር ጸጋ ነበር እንጂ በሰው ጥበብ አልነበረም። አንብባችሁ ማስተዋል የምትችሉትን ነገር ካልሆነ ሌላ ምንም አንጽፍላችሁም፤ በሙሉ ማስተዋል እንደምትችሉ ተስፋ አደርጋለሁ፤ አሁን ስለ እኛ የምታውቁት በከፊል ነው፤ በኋላ ግን በሙላት እንደምታስተውሉት ተስፋ አደርጋለሁ፤ በዚህም ምክንያት ጌታ ኢየሱስ በሚመጣበት ቀን እኛ በእናንተ እንደምንመካ እናንተም በእኛ ትመካላችሁ።