ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 5
5
1ንጉሥ ሰሎሞን የቤተ መቅደሱን ሥራ ሁሉ ከፈጸመ በኋላ አባቱ ዳዊት ለእግዚአብሔር የተለዩ ያደረጋቸውን ብርና ወርቅ እንዲሁም ሌሎችን ዕቃዎች ሁሉ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሚገኘው የዕቃ ግምጃ ቤት አኖራቸው። #2ሳሙ. 8፥11፤ 1ዜ.መ. 18፥11።
የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ቤተ መቅደስ መግባቱ
(1ነገ. 8፥1-9)
2ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት የዳዊት ከተማ ከሆነችው ከጽዮን ወደ ቤተ መቅደሱ ያመጡ ዘንድ የእስራኤል ሽማግሌዎች፥ የነገድና የቤተሰብ አለቆች ሁሉ በኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ ትእዛዝ ሰጠ። #2ሳሙ. 6፥12-15፤ 1ዜ.መ. 15፥25-28። 3በሰባተኛው ወር በሚከበረው በዳስ በዓል ጊዜ ሁሉም መጥተው በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ፤ 4-5መሪዎቹ ሁሉ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ ሌዋውያን የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክመው፥ ወደ ቤተ መቅደሱ አመጡት፤ እንዲሁም ካህናቱና ሌዋውያኑ እግዚአብሔር የሚመለክበትን ድንኳንና በውስጡ የነበሩትን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ ወደ ቤተ መቅደሱ አመጡ። 6ንጉሥ ሰሎሞንና ሕዝቡ ሁሉ በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ለፊት ተሰበሰቡ፤ ከዚህም በኋላ ከብዛታቸው የተነሣ ሊቈጠሩ የማይችሉ እጅግ ብዙ በጎችንና የቀንድ ከብቶችን መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። 7ካህናቱም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ወደ ቤተ መቅደሱ አግብተው በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ከኪሩቤል ክንፎች በታች በሚገኘው ስፍራ አኖሩት። 8የተዘረጉት የኪሩቤል ክንፎች የቃል ኪዳኑን ታቦትና የታቦቱን መሎጊያዎች ሸፍነዋቸው ነበር። 9መሎጊያዎቹ እጅግ ረጃጅሞች ስለ ነበሩ በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት የቆመ ማንኛውም ሰው ሊያያቸው ይችላል፤ በሌላ አቅጣጫ የቆመ ግን ፈጽሞ ሊያያቸው አይችልም ነበር፤ እነዚህ መሎጊያዎች እስከ ዛሬ ድረስ በዚያው ይገኛሉ፤ 10እስራኤላውያን ከግብጽ እንደ ወጡ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን በገባ ጊዜ ሙሴ በሲና ተራራ በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ ጽላቶች በቀር በታቦቱ ውስጥ ሌላ ነገር አልነበረም። #ዘዳ. 10፥5።
የእግዚአብሔር ክብር መገለጥ
11እዚያ የነበሩት ካህናት ሁሉ የአገልግሎት ምድባቸውን ሳይመለከቱ በአንድነት ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ሰጥተው ነበር፤ 12መዘምራን የሆኑ ሌዋውያን ሁሉ፥ አሳፍ፥ ሄማንና ይዱታን እንዲሁም ወንዶች ልጆቻቸውና ዘመዶቻቸው ሁሉ ጥሩ የበፍታ ልብስ ለብሰው ነበር፤ ሌዋውያኑ ጸናጽልና መሰንቆ በመያዝ በስተ ምሥራቅ በኩል ከመሠዊያው አጠገብ ቆመው ነበር፤ 13-14ከእነርሱም ጋር እምቢልታ የሚነፉ አንድ መቶ ኻያ ካህናት ነበሩ፤ እነዚህ መዘምራን ሁሉ በመለከት፥ በጸናጽል፥ በበገናና በሌሎችም የሙዚቃ መሣሪያዎች እየታጀቡ፦
“ቸር ስለ ሆነ፥ ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ስለ ሆነ
እግዚአብሔርን አመስግኑ”
በማለት በአንድ ድምፅ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር።
በዚህ ጊዜ በድንገት የእግዚአብሔርን ክብር የሚገልጥ አንጸባራቂ ብርሃን የሞላበት ደመና የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ስለ ሞላው ካህናቱ የአምልኮ አገልግሎታቸውን ሊያከናውኑ አልቻሉም። #1ዜ.መ. 16፥34፤ 2ዜ.መ. 7፥3፤ ዕዝ. 3፥11፤ መዝ. 100፥5፤ 106፥1፤ 107፥1፤ 118፥1፤ 136፥1፤ ኤር. 33፥11። #ዘፀ. 40፥34-35።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 5: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997