ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 4
4
ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎች
(1ነገ. 7፥23-51)
1ንጉሥ ሰሎሞን ወርዱም ርዝመቱም ዘጠኝ ሜትር፥ ቁመቱ አራት ሜትር ተኩል የሆነ መሠዊያ ከነሐስ አሠራ። #ዘፀ. 27፥1-2። 2እንዲሁም ጥልቀቱ ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር፥ የጐኑ አጋማሽ አራት ሜትር ከአርባ ሳንቲ ሜትር፥ ዙሪያው ዐሥራ ሦስት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር የሆነ ክብ ገንዳ አሠራ፤ 3የገንዳው የውጪው ክፈፍ ዙሪያው በሙሉ አንዱ በሌላው ላይ የተነባበረ ሆኖ በሁለት ረድፍ የተሠሩ ጌጦች ነበሩት፤ እነዚህም ጌጦች በሙሉ ከገንዳው ጋር አንድ ወጥ ሆነው በበሬዎች ቅርጽ የተሠሩ ናቸው። 4በርሜሉም ከነሐስ በተሠሩና ፊታቸውን ወደ ውጪ ባዞሩ በዐሥራ ሁለት የበሬዎች ምስሎች ጀርባ ላይ ተቀምጦ ነበር፤ የኰርማዎቹ ምስሎችም ሦስቱ ወደ ሰሜን፥ ሦስቱ ወደ ደቡብ፥ ሦስቱ ወደ ምሥራቅ፥ ሦስቱ ደግሞ ወደ ምዕራብ የሚመለከቱ ነበሩ። 5የሁሉም ጀርባቸው ወደ ውስጥ ነበር። የገንዳው ጐኖች ውፍረት ሰባ አምስት ሚሊ ሜትር ሲሆን፥ ክፈፉም እንደ ኩባያ ክፈፍ ሆኖ እንደ አሸንድዬ አበባ ወደ ውጪ የተቀለበሰ ነው፤ በርሜሉ ሥልሳ ሺህ ሊትር ያኽል ውሃ የሚይዝ ነበር። 6ሰሎሞን ዐሥር የመታጠቢያ ገንዳዎችን አሠርቶ፥ አምስቱን በቤተ መቅደሱ ደቡባዊ ጐን የቀሩትን አምስቱን ደግሞ በቤተ መቅደሱ ሰሜናዊ ጐን አኖራቸው፤ እነዚህ ገንዳዎች ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚታረድ እንስሳ ሥጋ ሁሉ የሚታጠብባቸው ነበሩ፤ በትልቁ ገንዳ ያለው ውሃ ደግሞ ለካህናቱ መታጠቢያ የሚውል ነበር። #ዘፀ. 30፥17-21። 7ሰሎሞን በተዘጋጀው ዕቅድ መሠረት ዐሥር መቅረዞችን ከወርቅ አሠርቶ በቤተ መቅደሱ ዋና ክፍል ውስጥ አምስቱን በሰሜን፥ አምስቱን በደቡብ በኩል አኖራቸው። #ዘፀ. 25፥31-40።
8እንዲሁም ዐሥር ጠረጴዛዎችን አሠርቶ በቤተ መቅደሱ ዋና ክፍል ውስጥ አምስቱን በሰሜን፥ አምስቱን በደቡብ በኩል አኖራቸው፤ በተጨማሪም አንድ መቶ ማንቈርቈሪያዎችን ከወርቅ አሠራ። #ዘፀ. 25፥23-30።
9ሰሎሞን ለካህናቱ አገልግሎት የሚውለውን ውስጠኛ አደባባይ፥ እንዲሁም ታላቁን አደባባይ አሠራ፤ እንዲሁም በሁለቱ አደባባዮች መካከል የሚገኙትን በሮች አሠርቶ በነሐስ እንዲለበጡ አደረገ። 10ትልቁ ገንዳ የቆመው በቤተ መቅደሱ ደቡባዊ ምሥራቅ ማእዘን አጠገብ ነው።
11-16ሑራም በተጨማሪ ምንቸቶችን፥ መጫሪያዎችንና ማንቈርቈሪያዎችንም ሠራ፤ በዚህ ሁኔታም ሑራም ለንጉሥ ሰሎሞን እንዲሠራለት ቃል በገባለት መሠረት ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት የሚውለውን ዕቃ ሁሉ ሠርቶ ፈጸመ፤ የሠራቸውም ዕቃዎች ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ናቸው፦
ሁለት ምሰሶዎች፥
በምሰሶዎቹ ጫፍ ላይ የሚገኙት የሳሕን ቅርጽ ያላቸው ሁለት ጒልላቶች፥
ሁለቱን ጉልላቶች ለማስጌጥ
በእያንዳንዱ ጒልላት ላይ የሚገኙት በመርበብ አምሳል የተቀረጹት ሁለት ሰንሰለቶች፥
ጉልላቶቹን ለማስጌጥ በእያንዳንዱ ጒልላት ላይ በሁለት ዙር የተቀረጹ ከነሐስ የተሠሩ አራት መቶ የሮማን ፍሬ ምስሎች፥
ዐሥሩ ባለመንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎች፥
ዐሥሩ የመታጠቢያ ገንዳዎች፥
ትልቁ ገንዳ፥
በርሜሉን ደግፈው የያዙት የዐሥራ ሁለቱ በሬዎች ቅርጾች፥
ምንቸቶች፥ መጫሪያዎች፥ ሜንጦዎችና ሌሎችም እነዚህን የመሳሰሉ ዕቃዎች በእጅ ጥበብ ሠራ።
ታዋቂ የሆነው ሑራም በንጉሥ ሰሎሞን ትእዛዝ መሠረት ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገልግሎት ይውሉ ዘንድ እነዚህን ዕቃዎች ሁሉ የሠራው ከተወለወለ ነሐስ ነበር።
17ንጉሥ ሰሎሞን እነዚህን ዕቃዎች ሁሉ ያሠራው በዮርዳኖስ ሸለቆ፥ በሱኮትና በጸሬዳ መካከል በሚገኘው በነሐስ ማቅለጫ ስፍራ ነበር። 18በዚህ ዐይነት የተሠሩት ዕቃዎች እጅግ ብዙ ስለ ነበሩ እነርሱን ለማሠራት የተጠቀመበት ጠቅላላ የነሐስ ክብደት ምን ያኽል እንደ ሆነ ማንም ሊያውቅ አልቻለም።
19እንዲሁም ንጉሥ ሰሎሞን ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት የሚውሉ የሚከተሉትን ዕቃዎች ከወርቅ አሠርቶአል፦ መሠዊያውና ለእግዚአብሔር መባ ሆኖ የሚቀርበው ኅብስት ማኖሪያ ጠረጴዛ፥ 20ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ መቅረዞችና በተወሰነው ዕቅድ መሠረት በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት የሚያበሩ ቀንዲሎቻቸው፥ 21የአበባ ቅርጽ ያላቸው ጌጦች፥ ቀንዲሎችና መኰስተሪያዎች፥ 22የመብራት ማብሪያና ማጥፊያዎች፥ ማንቈርቈሪያዎች፥ ጥናዎችና የእሳት መጫሪያዎች፤ እነዚህ ዕቃዎች ሁሉ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ናቸው፤ የቤተ መቅደሱ የውጪ በሮችና የቅድስተ ቅዱሳኑ በሮችም በወርቅ የተለበጡ ነበሩ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 4: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997