ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 3

3
1የሰሎሞን አባት ንጉሥ ዳዊት ቤተ መቅደስ የሚሠራበትን ስፍራ በኢየሩሳሌም በሞሪያ ተራራ ለይ አስቀድሞ አዘጋጅቶ ነበር፤ ይህም ስፍራ እግዚአብሔር ለንጉሥ ዳዊት የተገለጠበት፥ ኢያቡሳዊው ኦርና አውድማ አድርጎ ይጠቀምበት የነበረ ነው። #ዘፍ. 22፥2። 2ሰሎሞን በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ በሁለተኛው ወርና በሁለተኛው ቀን የቤተ መቅደሱን ሥራ ጀመረ፤ 3ንጉሥ ሰሎሞን ያሠራው ቤተ መቅደስ ርዝመቱ ኻያ ሰባት ሜትር ሲሆን፥ ወርዱ ዘጠኝ ሜትር ነበር፤ 4በመግቢያው በር ያለው በረንዳም ቁመቱ ኀምሳ አራት ሜትር ሲሆን፥ ወርዱ ልክ እንደ ቤተ መቅደሱ ወርድ ዘጠኝ ሜትር ነው፤ ውስጡም በንጹሕ ወርቅ እንዲለበጥ አደረገ። 5የቤተ መቅደሱ ዋና ክፍል በጥድ እንጨትና በንጹሕ ወርቅ የተለበጠ ሆኖ የዘንባባና የሰንሰለት ቅርጽ ተስሎበት ነበር። 6ንጉሥ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን እጅግ ውብ በሆነ የከበረ ድንጋይና ከፋርዋይም አገር በመጣ ወርቅ አስጊጦት ነበር። 7የቤተ መቅደሱን ግድግዳዎች፥ የጣራውን ክፈፎች፥ መቃኖችና መዝጊያዎቹን በወርቅ ለበጣቸው፤ በግድግዳዎቹም ላይ የኪሩቤልን ምስሎች ቀረጸባቸው። 8ቅድስተ ቅዱሳን ተብሎ የሚጠራው የውስጠኛው ክፍል ርዝመት ዘጠኝ ሜትር ሲሆን፥ ወርዱ ልክ እንደ ርዝመቱ ዘጠኝ ሜትር ነው፤ የቅድስተ ቅዱሳኑም ግንቦች ኻያ ሺህ ኪሎ ያኽል ክብደት ባለው ንጹሕ ወርቅ ተለብጠው ነበር። #ዘፀ. 26፥33-34። 9ምስማሮቹን ለማሠራት አምስት መቶ ሰባ ግራም ወርቅ ፈጅቶበታል፤ የፎቁ ክፍሎች ግንቦችም በወርቅ ተለብጠው ነበር።
10ንጉሥ ሰሎሞን ሠራተኞቹ የኪሩቤል ምስሎችን ቀርጸው በወርቅ እንዲለብጡአቸውና በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ እንዲያቆሙአቸው አዘዘ። 11-13ኪሩቤል በቅድስተ ቅዱሳን መግቢያ ትይዩ ጐን ለጐን ቆመው ነበር፤ እያንዳንዱ ኪሩብም ሁለት ክንፎች ነበሩት፤ የእያንዳንዱም ክንፍ ርዝመት ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ነበር፤ ሁለቱ ክንፎች በየአቅጣጫው የተዘረጉ ሆነው በክፍሉ መኻል ላይ እርስ በርሳቸው ይነካካሉ፤ ሌሎቹ ሁለቱ ክንፎቻቸው ደግሞ እያንዳንዱ በየአቅጣጫው ያለውን ግድግዳ የሚነካ ሲሆን፥ የእነዚህ የተዘረጉ ክንፎች ጠቅላላ ወርድ ዘጠኝ ሜትር ያኽል ነበር። #ዘፀ. 25፥18-20። 14ለቅድስተ ቅዱሳኑ ከበፍታና ከሌላም ዐይነት ጨርቅ የተሠራ መጋረጃ ተደርጎለት ነበር፤ የመጋረጃውም ቀለም ሰማያዊ፥ ሐምራዊና ቀይ ሲሆን በላዩም ላይ የኪሩቤል ምስሎች ተቀርጸውበት ነበር። #ዘፀ. 26፥31።
ከነሐስ የተሠሩ ሁለት ምሰሶዎች
(1ነገ. 7፥15-22)
15ንጉሥ ሰሎሞን የእያንዳንዱ ቁመት ዐሥራ አምስት ሜትር ተኩል የሆነ ሁለት ምሰሶዎችን ሠርቶ፥ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት አቆማቸው፤ በእያንዳንዱም ምሰሶ ጫፍ ላይ ቁመታቸው ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር የሆነ ሁለት ጉልላቶች ነበሩ፤ 16የምሰሶዎቹም ጫፎች የመርበብ ቅርጽ ባላቸው ሰንሰለቶችና ከነሐስ በተሠሩ ቊጥራቸው አንድ መቶ በሆነ የሮማን ፍሬ አምሳል የተሠራ ቅርጽ ተስሎባቸው ነበር፤ 17ምሰሶዎቹም የቆሙት በቤተ መቅደሱ መግቢያ በር ግራና ቀኝ ነበር፤ በደቡብ በኩል የቆመው ምሰሶ “ያኪን” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፥ በሰሜን በኩል የቆመው ደግሞ “ቦዔዝ” ተብሎ ይጠራ ነበር። #3፥17 ያኪን፦ እግዚአብሔር ያቆማል ማለት ነው።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ