ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 31

31
ንጉሥ ሕዝቅያስ ያደረገው መንፈሳዊ ተሐድሶ
1ከበዓሉ ፍጻሜ በኋላ መላው የእስራኤል ሕዝብ ወደ ይሁዳ ከተሞች ሁሉ በመሄድ ከድንጋይ የተሠሩትን የጣዖት ዐምዶች ሰባበሩ፤ አሼራ ተብላ በምትጠራው ሴት አምላክ ስም የቆሙ ምስሎችንም ሰባብረው ጣሉ፤ መሠዊያዎችንና የአሕዛብ መስገጃ ስፍራዎችንም ደመሰሱ፤ እንዲሁም በቀሩት በይሁዳ፥ በብንያም፥ በኤፍሬምና በምናሴ ግዛቶች ውስጥ የነበሩትን የጣዖት መስገጃዎችንና መሠዊያዎችን ሁሉ አፈራረሱ፤ ከዚያም በኋላ ወደየመኖሪያ ስፍራዎቻቸው ተመለሱ።
2ንጉሥ ሕዝቅያስ የካህናትንና የሌዋውያንን ሥርዓት እንደገና አቋቋመ፤ በዚህም ጉባኤ ውስጥ እያንዳንዱ ካህንና እያንዳንዱ ሌዋዊ የተለየ የሥራ ምድብ ነበረው፤ ይህም የሥራ ምድብ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕትን ማቅረብን፥ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሚከናወነው የአምልኮ ሥነ ሥርዓት መሳተፍን፥ በሌሎቹም በቤተ መቅደሱ ልዩ ልዩ ክፍሎች ምስጋናና ውዳሴ ማቅረብን የሚያጠቃልል ነበር፤ 3ዘወትር ጠዋትና ማታ ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ በሰንበቶች፥ በወር መባቻዎችና በእግዚአብሔር ሕግ በተወሰነው በሌሎች በዓላት ለሚቀርብ መሥዋዕት ንጉሥ ሕዝቅያስ የራሱ ንብረት ከሆኑ በጎችና የቀንድ ከብቶች ይሰጥ ነበር። #ዘኍ. 28፥1—29፥39።
4በተጨማሪም ካህናቱና ሌዋውያኑ ጊዜአቸውን በሙሉ የእግዚአብሔር ሕግ ለሚጠይቀው አገልግሎት ማዋል ይችሉ ዘንድ ለእነርሱ መሰጠት የሚገባውን ሁሉ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እንዲያመጡ ንጉሡ አዘዘ፤ 5እስራኤላውያን ይህን የንጉሡን ትእዛዝ እንደ ሰሙ ከእህላቸውና ከወይን ጠጃቸው፥ ከወይራ ዘይታቸውና ከማራቸው ከሌላውም የእርሻቸው ፍሬ ሁሉ ምርጥ የሆነውን በኲራት በልግሥና አበረከቱ፤ ከነበራቸውም ሀብት ሁሉ ዐሥራት አውጥተው ሰጡ፤ #ዘኍ. 18፥12—13፥21። 6በይሁዳ ከተሞች ሰዎችም ሕዝብም ሁሉ ከቀንድ ከብቶቻቸውና ከበጎቻቸው ዐሥራት አውጥተው ሰጡ፤ እንዲሁም ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር የተለየ ያደረጉትን ስጦታ አምጥተው ከመሩት፤ 7ስጦታዎቹንም ማምጣት የጀመሩት በሦስተኛው ወር ሲሆን፥ በተከታታይ ለአራት ወራት ስጦታቸውን እያመጡ መከመር ቀጠሉ፤ 8ንጉሥ ሕዝቅያስና ባለሟሎቹ የሆኑት ባለሥልጣኖች መጥተው፥ እጅግ የበዛውን የስጦታ ክምር ባዩ ጊዜ፥ እግዚአብሔርንና የእርሱ ወገኖች የሆኑትን የእስራኤልን ሕዝብ አመሰገኑ፤ 9ንጉሡ ከሕዝቡ ስለ ተበረከተው የስጦታ ክምር፥ ካህናቱንና ሌዋውያኑን ጠየቀ፤ 10የሳዶቅ ዘር የሆነው ሊቀ ካህናት ዐዛርያስም ንጉሡን፥ “ሕዝቡ ዐሥራቱን ወደ እግዚአብሔር ቤት ማምጣት ከጀመረ ወዲህ፥ እነሆ፥ በቂ ምግብ አለን፤ ብዙም ተርፎናል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለ ባረከ እነሆ፥ ይህን ሁሉ በብዛት አግኝተናል” አለው።
11ንጉሥ ሕዝቅያስም በቤተ መቅደሱ አካባቢ የዕቃ ግምጃ ቤት እንዲዘጋጅ፥ አዞ በተዘጋጀ ጊዜ 12ዐሥራቱንና በኲራቱን፥ የተቀደሱትንም ስጦታዎች ሁሉ በእምነት ወደዚያ አስገቡ፤ ኮናንያ ተብሎ የሚጠራው ሌዋዊ የዕቃ ግምጃ ቤቱ ኀላፊ ሆኖ ሲሾም፥ ወንድሙ ሺምዒ ደግሞ ረዳቱ ሆኖ ተሾመ፤ 13ከእነርሱም ሥር ሆነው የሚሠሩ ይሒኤል፥ ዐዛዝያ፥ ናሐት፥ ዐሣሄል፥ ይሪሞት፥ ዮዛባድ፥ ኤሊኤል፥ ዩስማክያ፥ ማሐትና በናያ ተብለው የሚጠሩ ዐሥር ሌዋውያን ተመደቡ። እነዚህን ሁሉ የሾሙ፥ ንጉሥ ሕዝቅያስና ሊቀ ካህናቱ ዐዛርያስ ናቸው፤ 14የቤተ መቅደሱ የምሥራቃዊ በር ዘብ ጠባቂዎች አለቃ ለነበረው ለሌዋዊው ዩምና ልጅ ለቆሬ ደግሞ፥ ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን የበጎ ፈቃድ ስጦታዎች ሁሉ የመቀበልና የማከፋፈል ኀላፊነት ተሰጠው። 15ካህናት በሚኖሩባቸው በሌሎች ከተሞች ቆሬን በታማኝነት የሚረዱ ዔደን፥ ሚንያሚን፥ ኢያሱ፥ ሸማዕያ፥ አማርያና ሸካንያ ተብለው የሚጠሩ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም በሥራቸው ምድብ መሠረት ምግቡን ወገኖቻቸው ለሆኑ ሌዋውያን በትክክል ያከፋፍሉ ነበር። 16በተጨማሪም በተለያዩ የየዕለት ተግባራቸው ወደ ቤተ መቅደስ ለሚገቡ ከሦስት ዓመት ዕድሜ በላይ ላላቸው ወንዶች እንደየ ኀላፊነታቸውና እንደየምድባቸው ድርሻ ድርሻቸውን ያከፋፍሉ ነበር፤ 17የካህናት ሥራ ምድብ በጐሣ በጐሣ ሲሆን፥ ዕድሜአቸው ኻያ ወይም ከዚያ በላይ የሆነ ሌዋውያን፥ የሥራ ምድብ ግን በሚያከናውኑት የሥራ ዐይነት የሚወሰን ነበር፤ 18እነዚህ ካህናትና ሌዋውያን ራሳቸውን የቀደሱ ታማኞች ስለ ነበሩ የሚመዘገቡት ከሚስቶቻቸው ከልጆቻቸውና በእነርሱ ሥር ከሚተዳደሩት ሰዎች ሁሉ ጋር በአንድነት ነበር፤ 19ለአሮን ልጆች በተመደቡ ከተሞች ወይም የእነዚህ ከተሞች ይዞታ በሆኑት የግጦሽ ቦታዎች ከሚኖሩት ካህናት መካከል ለካህናት ቤተሰቦችና በሌዋውያን ጐሣ የስም ዝርዝር በያዘ መዝገብ ውስጥ ስማቸው ለሚገኝ ወንዶች ሁሉ ምግብን ለማከፋፈል ኀላፊዎች የሆኑ ሰዎች ነበሩ።
20ንጉሥ ሕዝቅያስ በመላው የይሁዳ ግዛት መልካም የሆነውንና ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኘውን ነገር ሁሉ አደረገ፤ 21ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት ወይም ሕጉንና ትእዛዞቹን ለመጠበቅ ያከናወነው ሥራ ሁሉ ለአምላኩ ለእግዚአብሔር በፍጹም ታማኝነትና በመንፈሳዊ ቅናት ስለ ነበር ሁሉም ነገር ተሳካለት።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ