ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 30
30
ለፋሲካ በዓል አከባበር የተደረገ ዝግጅት
1-3ራሳቸውን ያነጹ በቂ ካህናት ስላልነበሩና በኢየሩሳሌም ብዙ ሕዝብ ስላልተሰበሰበ፥ ሕዝቡ የፋሲካን በዓል እንደ ተለመደው በመጀመሪያው ወር ሊያከብር አልቻለም፤ ስለዚህ ንጉሥ ሕዝቅያስ፥ ባለሟሎቹ የሆኑት ባለሥልጣኖችና የኢየሩሳሌም ሕዝብ የፋሲካ በዓል በሁለተኛው ወር እንዲከበር ተስማምተው ወሰኑ፤ በዚህ መሠረት ንጉሡ ለመላው የእስራኤልና የይሁዳ እንዲሁም የኤፍሬምና የምናሴ ሕዝብ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ክብር በፋሲካ በዓል ተካፋዮች ይሆኑ ዘንድ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ እንዲመጡ የጥሪ ደብዳቤ ላከላቸው፤ #ዘኍ. 9፥9-11። 4ንጉሡና ሕዝቡም በዚሁ ዕቅዳቸው ደስ ተሰኙ። 5በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሠረት የእስራኤል አምላክ የእግዚአብሔር ፋሲካ ለብዙ ጊዜ ብዛት ባለው ሕዝብ ስላልተከበረ ንጉሡና ሕዝቡ በሰሜን ከሚገኘው ከዳን በደቡብ እስከሚገኘው እስከ ቤርሳቤህ ለሚገኙ እስራኤላውያን በኢየሩሳሌም ተሰብስበው እንዲያከብሩት ዐዋጅ ይታወጅ ዘንድ ወሰኑ። 6በንጉሡ ትእዛዝ መልእክተኞቹ እንዲህ የሚለውን የንጉሡንና የሕዝቡን ደብዳቤ ይዘው ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ሁሉ ሄዱ።
“የእስራኤል ልጆች ሆይ! ከአሦር ንጉሥ ምርኮ የተረፋችሁት ወደ እናንተ ይመለስ ዘንድ፥ ወደ አብርሃም፥ ወደ ይስሐቅና ወደ ያዕቆብ አምላክ ተመለሱ፤ 7ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ታማኞች እንዳልሆኑት እንደ ቀድሞ አባቶቻችሁና እንደ ወገኖቻችሁ እስራኤላውያን አትሁኑ፤ እንደምታውቁት እግዚአብሔር እነርሱን ለጥፋት አሳልፎ ሰጥቶአቸዋል፤ 8ለእግዚአብሔር ታዘዙ እንጂ እንደ እነርሱ ልበ ደንዳኖች አትሁኑ፤ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር ስጡ፤ ለዘለዓለም ወደ ቀደሰው በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ ኑ፤ ከእንግዲህ ወዲህ እግዚአብሔር ቊጣውን ከእናንተ እንዲመልስ እርሱን ብቻ አምልኩ፤ 9ወደ እግዚአብሔር ብትመለሱ፥ እነዚያ ልጆቻችሁንና ዘመዶቻችሁን ማርከው የወሰዱ ሰዎች ለእነርሱ በመራራት ወደየመኖሪያ ስፍራቸው ተመልሰው እንዲመጡ ይፈቅዱላቸዋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ ስለ ሆነ እናንተ ወደ እርሱ ብትመለሱ እርሱ ፊቱን ከእናንተ አያዞርም።”
10መልእክተኞቹ በኤፍሬምና በምናሴ ነገዶች ግዛት ወደሚገኙ ከተማዎች ሁሉ በመሄድ እስከ ዛብሎን ነገድ ሰሜናዊ ግዛት ድረስ ዘለቁ፤ እነዚያ ግን በንቀት እየሳቁ ተሳለቁባቸው፤ 11ይሁን እንጂ ለእግዚአብሔር ትሕትናን በማሳየት ወደ ኢየሩሳሌም ፈቃደኞች ሆነው የመጡ ከአሴር፥ ከምናሴና ከዛብሎን ነገዶች አንዳንድ ሰዎች ነበሩ፤ 12ደግሞም አንድ ልብ ይሰጣቸው ዘንድ፥ በእግዚአብሔር ቃል የሆነውን የንጉሡንና የባለሥልጣኖቹን ትእዛዝ ያደርጉ ዘንድ እግዚአብሔር የይሁዳን ሕዝብ ልብ አነሣሣ።
የፋሲካ በዓል መከበር
13በሁለተኛው ወር የቂጣን በዓል ለማክበር ብዙ ሰዎች በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። 14በኢየሩሳሌም መሥዋዕትን ለማቅረብና ዕጣንን ለማጠን አገልግሎት ይውሉ የነበሩትን የጣዖቶች መሠዊያዎች ሁሉ አንሥተው በመውሰድ በቄድሮን ሸለቆ ጣሉአቸው፤ 15የሁለተኛው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን የበግ ጠቦቶችን ለፋሲካ በዓል መሥዋዕት አድርገው ዐረዱ፤ በዚህ ጊዜ ራሳቸውን ያላነጹ ካህናትና ሌዋውያን በጣም አፈሩ፤ ከዚህም የተነሣ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ለዩ፤ ከዚያም በኋላ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ማቅረብ ቻሉ። 16የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ በሰጠውም ሕግ መመሪያ መሠረት በቤተ መቅደሱ ውስጥ በተመደበላቸው ቦታ ቆሙ፤ ሌዋውያኑም የመሥዋዕቱን ደም ለካህናቱ አቀረቡ፤ ካህናቱም ደሙን በመሠዊያው ላይ ረጩ፤ 17ከሕዝቡ መካከል ብዙዎቹ ራሳቸውን ያላነጹ ስለ ነበሩ ለፋሲካ የሚሆኑትን የበግ ጠቦቶች ለማረድ አልተፈቀደላቸውም ነበር፤ ስለዚህ ሌዋውያን በእነርሱ ምትክ የበግ ጠቦቶቹን በማረድ ለእግዚአብሔር አቀረቡላቸው፤ 18በተጨማሪም ከኤፍሬም፥ ከምናሴ ከይሳኮርና ከዛብሎን ነገዶች የመጡት ብዙ ሰዎች የነጹ ስላልነበሩ የፋሲካን በዓል በሚገባ አላከበሩም፤ ንጉሥ ሕዝቅያስም ስለ እነርሱ፥ 19“የቀድሞ አባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን በሥርዓት ያላነጹ ቢሆኑም እንኳ እነሆ በፍጹም ልባቸው አንተን በማምለክ ላይ ይገኛሉ፤ ስለዚህ በቸርነትህ ይቅር በላቸው!” ሲል ጸለየ፤ 20እግዚአብሔርም የሕዝቅያስን ጸሎት ሰምቶ ይቅር አላቸው፤ አንዳች ጒዳትም አላደረሰባቸውም። 21በኢየሩሳሌም የተሰበሰበውም ሕዝብ ሰባት ቀን ሙሉ የቂጣን በዓል በታላቅ ደስታ አከበረ፤ ሌዋውያኑና ካህናቱም በየቀኑ በዜማ መሣሪያዎቻቸው በመታጀብ እየዘመሩ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር፤ 22ሕዝቅያስም ለእግዚአብሔር የተደረገውን የአምልኮ ሥነ ሥርዓት በመምራት ከፍ ያለ ችሎታ ስላሳዩ ሌዋውያኑን አመሰገነ።
ለቀድሞ አባቶቻቸው አምላክ ለእግዚአብሔር ክብር ሰባት ቀን የኅብረት መሥዋዕት አቅርበው ከበሉ በኋላ፥ 23በተጨማሪ ለሰባት ቀን በዓል እንዲያደርጉ በአንድነት ወስነው በዓሉን በደስታ አከበሩ። 24ንጉሥ ሕዝቅያስ አንድ ሺህ ኰርማዎችን፥ ሰባት ሺህ በጎችንና ፍየሎችን፥ ባለሟሎቹ የሆኑት ባለሥልጣኖች ደግሞ አንድ ሺህ ኰርማዎችን፥ ዐሥር ሺህ በጎችንና ፍየሎችን ዐርደው እንዲበሉ ለሕዝቡ ሰጡ፤ ቊጥራቸው እጅግ የበዛ ካህናትም ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ለዩ፤ 25ስለዚህ የይሁዳ ሕዝብ፥ ካህናቱ፥ ሌዋውያኑ፥ ከሰሜን ግዛቶች የመጡ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ምድር ለዘለቄታው የሰፈሩ መጻተኞች ሁሉ እጅግ ደስ አላቸው። 26ከዳዊት ልጅ ከሰሎሞን ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ይህንን የመሰለ በዓል በኢየሩሳሌም ተከብሮ ስለማያውቅ የኢየሩሳሌም ከተማ ሰዎች እጅግ ተደሰቱ። 27ካህናቱና ሌዋውያኑም ቆመው የእግዚአብሔር በረከት በሕዝቡ ላይ እንዲወርድ ጸለዩ፤ እግዚአብሔርም በተቀደሰ መኖሪያው በሰማይ ሆኖ ጸሎታቸውን ሰማ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 30: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997