ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 2

2
ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የተደረጉ ዝግጅቶች
(1ነገ. 5፥1-18)
1ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስና ለራሱ ቤተ መንግሥት ለመሥራት ወሰነ፤ 2ስለዚህም ዕቃን የሚያጓጒዙ ሰባ ሺህ፥ ድንጋይ የሚፈልጡ ሰማኒያ ሺህ ሰዎችን በሥራ ላይ አሰማራ፤ ሥራውን የሚቈጣጠሩ ደግሞ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎችን መደበ።
3ከዚህም በኋላ ለጢሮስ ንጉሥ ኪራም የሚከተለውን መልእክት ላከ፤ “አባቴ ንጉሥ ዳዊት ቤተ መንግሥቱን በሠራበት ጊዜ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ትልክለት እንደ ነበር ለእኔም ላክልኝ፤ 4አሁን እኔ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስን ለመሥራት በመዘጋጀት ላይ ነኝ፤ ይህም ቤተ መቅደስ እኔና ሕዝቤ በእግዚአብሔር ፊት ጣፋጭ ሽታ ያለውን ዕጣን የምናጥንበት የተቀደሰውን ኅብስት ሳናቋርጥ ለእግዚአብሔር የምናቀርብበት፥ በየቀኑ ጠዋትና ማታ፥ እንዲሁም በሰንበቶች፥ በወር መባቻዎችና በሌሎችም በተቀደሱ በዓላት እግዚአብሔር አምላካችንን ለማክበር የሚቃጠለውን መሥዋዕት የምናቀርብበት የተቀደሰ ስፍራ ይሆናል፤ የእስራኤል ሕዝብ ይህን ለዘለዓለም እንዲያደርጉ እግዚአብሔር አዞአል። 5የእኛ አምላክ ከሌሎች አማልክት ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ስለ ሆነ ታላቅ ቤተ መቅደስ ልሠራለት ዐቅጃለሁ። 6እንደ እውነቱ ከሆነ ለእግዚአብሔር በቂ የሚሆን ቤተ መቅደስን ለመሥራት የሚችል ማንም የለም፤ የሰማይና የምድር ስፋት እንኳ እግዚአብሔርን ሊይዘው አይችልም፤ ታዲያ ለእግዚአብሔር ዕጣን ለማጠን የሚበቃ ቤት ከመሥራት በቀር ለእርሱ ማደሪያ ሊሆን የሚችል ቤተ መቅደስ ለመሥራት የምሞክር እኔ ማን ነኝ? #1ነገ. 8፥27፤ 2ዜ.መ. 6፥18። 7እንግዲህ ቅርጽን የማውጣት፥ ወርቅን፥ ብርን፥ ነሐስንና ብረትን የማቅለጥ፥ ሰማያዊ፥ ሐምራዊና ቀይ ልብስ የመሥራት ችሎታ ያለውን ብልኀተኛ ሰው ላክልኝ፤ እርሱም አባቴ ዳዊት ከመረጣቸው በይሁዳና በኢየሩሳሌም ካሉት ብልኀተኞች ሰዎች ጋር ይሠራል። 8የአንተ እንጨት ቈራጮች እጅግ የሠለጠኑ መሆናቸውን ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ ከሊባኖስ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት የዝግባና የሰንደል እንጨት ላክልኝ። 9ይህ እኔ ልሠራ ያቀድኩት ቤተ መቅደስ ሰፊና እጅግ የተዋበ መሆን ስለሚገባው እኔም ብዙ እንጨት ቈርጠው በማዘጋጀት የአንተን ሰዎች የሚረዱ፥ የእኔን ሰዎች ወደ አንተ ለመላክ ዝግጁ ነኝ። 10እንጨት ለሚቈርጡ ለሠራተኞችህ ስንቅ የሚሆን ሁለት ሚሊዮን ኪሎ ስንዴ፥ ሁለት ሚሊዮን ኪሎ ገብስ፥ አራት መቶ ሺህ ሊትር የወይን ጠጅና አራት መቶ ሺህ ሊትር የወይራ ዘይት እልክልሃለሁ።”
11ንጉሥ ኪራምም ለንጉሥ ሰሎሞን በደብዳቤ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለሚወድ አንተ በእነርሱ ላይ እንድትነግሥ አደረገ።” 12ንጉሥ ኪራምም በመቀጠል፦ “ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስንና ለራሱ ቤተ መንግሥትን የሚሠራ በጥበብ፥ በማስተዋልና፥ በብልኀት የተሞላ ልጅን ለንጉሥ ዳዊት የሰጠ፥ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን!” አለ። 13“እነሆ ጥበበኛና በእጅ ሥራ የሠለጠነ ሑራም አቢ ተብሎ የሚጠራ ብልኀተኛ ሰው ልኬልሃለሁ። 14የሑራም አቢ እናት ከዳን ነገድ ስትሆን፥ አባቱም የጢሮስ ተወላጅ ነው፤ ሑራም አቢ ከወርቅ፥ ከብር፥ ከነሐስ፥ ከብረት፥ ከድንጋይና ከእንጨት ልዩ ልዩ ነገሮችን የመሥራት ችሎታ አለው፤ እንዲሁም ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ጨርቅና ከበፍታ የተለያየ ልብስ መሥራት ይችላል፤ ከዚህም ሌላ ልዩ ልዩ ቅርጽ ማውጣትና በተሰጠውም ንድፍ መሠረት ሁሉን ነገር መሥራት ይችላል፤ ስለዚህ ይህን ሰው በእጅ ሥራ ከሠለጠኑ ከአንተ ሰዎችና ከእነዚያ ለአባትህ ይሠሩ ከነበሩ ሰዎች ጋር እንዲሠራ አድርገው። 15እንግዲህ ልትልክልን በሰጠኸን ቃል መሠረት ስንዴውን፥ ገብሱን፥ የወይን ጠጁንና የወይራ ዘይቱን ላክልን፤ 16እኛም የምትፈልገውን ግንድ ሁሉ ከሊባኖስ ተራራዎች ቈርጠን አንድ ላይ በማሰር በባሕር ላይ ተንሳፍፎ እስከ ኢዮጴ እንዲደርስ እናደርጋለን፤ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ልትወስደው ትችላለህ።”
የቤተ መቅደሱ ሥራ አጀማመር
(1ነገ. 6፥1-38)
17ንጉሥ ሰሎሞን ከዚህ በፊት አባቱ ዳዊት ባደረገው ዐይነት በእስራኤል ምድር የሚኖሩትን የውጪ አገር ሰዎች ቈጠረ፤ በዚህም ዐይነት በግዛቱ ውስጥ አንድ መቶ ኀምሳ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ መጻተኞች መኖራቸው ተረጋገጠ፤ 18ከእነርሱም መካከል ሰባው ሺህ ዕቃ እንዲያጓጒዙ፥ ሰማኒያው ሺህ በተራራዎች ላይ ድንጋይ እንዲፈልጡ አደረገ፤ ደግሞም ሥራው በትክክል መካሄዱን የሚቈጣጠሩ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎችን ሾመ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ