ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 1
1
ንጉሥ ሰሎሞን እግዚአብሔር ጥበብን እንዲሰጠው መለመኑ
(1ነገ. 3፥1-15)
1የዳዊት ልጅ ንጉሥ ሰሎሞን መንግሥቱን አጠናከረ፤ እግዚአብሔር አምላኩም ባረከው፤ እጅግ በጣም ገናናም አደረገው።
2ንጉሥ ሰሎሞን ለእስራኤላውያን ሁሉ፥ ለሺህ አለቆችና ለመቶ አለቆች፥ እንዲሁም ለመንግሥቱ ባለ ሥልጣኖች፥ ለቤተሰብ መሪዎችና ሕዝብ በሙሉ፥ 3በገባዖን ወደሚገኘው ኰረብታማ የማምለኪያ ስፍራ አብረውት እንዲሄዱ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ ወደዚያ የሄዱበትም ምክንያት፥ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው፥ እግዚአብሔር የሚመለክበት ድንኳን በዚያው በገባዖን ስለሚገኝ ነው። 4የቃል ኪዳኑ ታቦት ግን ንጉሥ ዳዊት ከቂርያትይዓሪም ባመጣው ጊዜ በኢየሩሳሌም አዘጋጅቶለት በነበረው ድንኳን ውስጥ ይገኝ ነበር። #2ሳሙ. 6፥1-17፤ 1ዜ.መ. 13፥5-14፤ 15፥25—16፥1። 5የሑር የልጅ ልጅ፥ የኡሪ ልጅ ባጽልኤል ከነሐስ የሠራው መሠዊያም በዚያው በገባዖን በድንኳኑ ፊት ለፊት ነበረ፤ በዚያም ንጉሥ ሰሎሞንና ሕዝቡ ሁሉ ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ #ዘፀ. 38፥1-7። 6ንጉሡም እግዚአብሔር በሚመለክበት ድንኳን ፊት ለፊት ባለው ከነሐስ በተሠራው መሠዊያ ላይ መሥዋዕት በማቅረብ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ አንድ ሺህ እንስሶችንም አሳርዶ በመሠዊያው ላይ እንዲቃጠሉ አደረገ።
7በዚያችም ሌሊት እግዚአብሔር ለሰሎሞን ተገልጦ “ምን እንድሰጥህ ትፈልጋለህ?” ሲል ጠየቀው።
8ሰሎሞንም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አንተ ለአባቴ ለዳዊት ታላቅ ፍቅርህን ባለማቋረጥ አሳይተኸዋል፤ አሁንም እኔ በአባቴ እግር ተተክቼ እንድነግሥ አድርገሃል፤ 9እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! ለአባቴ የሰጠኸው የተስፋ ቃል እንዲፈጸም አድርግ፤ እነሆ ከብዛቱ የተነሣ ሊቈጠር በማይችል ሕዝብ ላይ አንግሠኸኛል፤ #ዘፍ. 13፥16፤ 28፥14። 10ስለዚህ ሕዝብህን በትክክል ለመምራት የሚያስችለኝን ጥበብና ዕውቀት ስጠኝ፤ ይህ ካልሆነ ግን ታላቅ ሕዝብህን እንዴት ልመራ እችላለሁ?”
11እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ለራስህ ባለጸግነትን ወይም ሀብትን፥ ዝናን ወይም የጠላቶችህን ሞት፥ ወይም ረጅም ዕድሜን ሳይሆን በእነርሱ ላይ እንድትነግሥ ያደረግኩህን ሕዝቤን በትክክል ለመምራት የሚያስችልህን ጥበብና ዕውቀት በመጠየቅህ፥ 12ስለዚህ እነሆ የጠየቅኸውን ጥበብና ዕውቀት እሰጥሃለሁ፤ በተጨማሪም ከዚህ በፊት ማንም ንጉሥ ካገኘውና ወደፊትም ማንም ሊያገኘው ከሚችለው የሚበልጥ ብልጽግና፥ ሀብትና ዝና እሰጥሃለሁ።”
የንጉሥ ሰሎሞን ሥልጣንና ሀብት
(1ነገ. 10፥26-29)
13ሰሎሞን እግዚአብሔር የሚመለክበት ድንኳን ካለበት፥ በገባዖን ከሚገኘው ኰረብታማ ማምለኪያ ስፍራ ተነሥቶ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ በእስራኤል ላይ ነገሠ።
14ሰሎሞን በአንድ ሺህ አራት መቶ ሠረገሎችና በዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሶች የተጠናከረ ሠራዊትን አደራጀ፤ ከእነርሱም ከፊሉን በኢየሩሳሌም፥ የቀረውን ደግሞ በሌሎች ልዩ ልዩ ከተሞች በመመደብ በዚያው እንዲኖሩ አደረገ። #1ነገ. 4፥26።
15በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት በኢየሩሳሌም ወርቅና ብር ከመብዛቱ የተነሣ እንደ ድንጋይ ተራ ነገር ነበር፤ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ብዛት በይሁዳ ኰረብቶች ግርጌ በየትኛውም ስፍራ እንደሚበቅል ሾላ ዛፍ ይቈጠር ነበር። 16የንጉሡም ፈረሶች የሚመጡት፥ ከግብጽና ከቀዌ ነበር፤ የንጉሡም ነጋዴዎች ከቀዌ ይገዙአቸው ነበር። 17ከግብጽ ለሚገዛው ለያንዳንዱ ሠረገላ ስድስት መቶ ጥሬ ብር ለያንዳንዱ ፈረስ አንድ መቶ ኀምሳ ጥሬ ብር ይከፍሉ ነበር። እነርሱም መልሰው ለሒታውያንና ለሶርያ ነገሥታት ይሸጡላቸው ነበር። #ዘዳ. 17፥16።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 1: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997