የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 የጴጥሮስ መልእክት 5:1-14

1 የጴጥሮስ መልእክት 5:1-14 አማ05

እንግዲህ እኔ ከእነርሱ ጋር አብሬ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ የሆንኩ፥ የክርስቶስም መከራ ምስክር የሆንኩ፥ እንዲሁም ወደፊት የሚገለጠው ክብር ተካፋይ የምሆን፥ በመካከላችሁ ያሉትን የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ። በዐደራ የተሰጣችሁን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ መንጋውን የምትጠብቁትም በግድ ሳይሆን እግዚአብሔር በሚፈልገው ዐይነት፥ በፈቃደኛነት ይሁን፤ ለገንዘብ በመስገብገብ ሳይሆን ለማገልገል ባላችሁ ፍላጎት ይሁን። እንዲሁም በእናንተ ኀላፊነት ሥር ያሉትን ጨቊኖ በመግዛት ሳይሆን ለመንጋው መልካም ምሳሌነትን በማሳየት ይሁን። ይህን ብታደርጉ ዋናው እረኛ በሚገለጥበት ጊዜ የማይበላሸውን የክብር አክሊል ትቀበላላችሁ። እንዲሁም እናንተ ጐልማሶች! ለሽማግሌዎች ታዘዙ፤ ሁላችሁም ትሕትናን እንደ ልብስ ለብሳችሁ አንዱ ሌላውን ያገልግል፤ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል ለትሑቶች ግን ጸጋን ይሰጣል” ተብሎ ተጽፎአልና። እንግዲህ እግዚአብሔር በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ ሥር ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ። እርሱ ለእናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሐሳብ ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። በመጠን ኑሩ፤ ንቁም! ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ በዙሪያችሁ ይንጐራደዳል። በዓለም ሁሉ ያሉ ወንድሞቻችሁ ይህን ዐይነት መከራ እንደሚቀበሉ በማወቅ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ በክርስቶስ ወደ ዘለዓለም ክብር የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ እርሱ ራሱ ከተቀበላችሁት መከራ ያድናችኋል፤ ይደግፋችኋል፤ ያጸናችኋል፤ ይመሠርታችኋልም። ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ክብርና ኀይል ለእርሱ ይሁን! አሜን። ታማኝ ወንድም ነው ብዬ በማስበው በሲላስ አማካይነት ይህን መልእክት ባጭሩ ጽፌላችኋለሁ፤ የጻፍኩላችሁም ልመክራችሁና ይህ እውነተኛ የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን ልገልጽላችሁ ብዬ ነው፤ ስለዚህ በዚህ በእግዚአብሔር ጸጋ ጸንታችሁ ቁሙ። እንደ እናንተ የተመረጠችው፥ በባቢሎን ያለችው እኅት ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ ታቀርብላችኋለች፤ ልጄ ማርቆስም ሰላምታ ያቀርብላችኋል። በክርስቲያናዊ ፍቅር እርስ በርስ በመሳሳም ሰላምታ ተለዋወጡ። የክርስቶስ ለሆናችሁት ለሁላችሁም ሰላም ይሁን።