የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ጴጥሮስ 5:1-14

1 ጴጥሮስ 5:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እንግዲህ ከእነርሱ ጋር እኔም ሽማግሌና የክርስቶስ መከራ ምስክር የሆንሁ፣ እንዲሁም ወደ ፊት የሚገለጠው ክብር ተካፋይ የምሆን፣ በመካከላችሁ ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤ በእናንተ ኀላፊነት ሥር ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ የምትጠብቁትም ከእግዚአብሔር እንደሚጠበቅባችሁ በግድ ሳይሆን በፈቃደኝነት፣ ለጥቅም በመስገብገብ ሳይሆን ለማገልገል ባላችሁ ጽኑ ፍላጎት ይሁን፤ እንዲሁም በዐደራ ለተሰጣችሁ መንጋ መልካም ምሳሌ በመሆን እንጂ በላያቸው በመሠልጠን አይሁን። የእረኞች አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማይጠፋውን አክሊል ትቀበላላችሁ። ጕልማሶች ሆይ፤ እናንተም እንዲሁ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርስ በመከባበር ትሕትናን ልበሱ፤ ምክንያቱም፣ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።” ስለዚህ እርሱ በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። ራሳችሁን የምትገዙ ሁኑ፣ ንቁም፤ ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ ወዲያ ወዲህ ይዞራልና። በዓለም ዙሪያ ያሉት ወንድሞቻችሁ ተመሳሳይ መከራ እንደሚቀበሉ ዐውቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። በክርስቶስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ፣ ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ እርሱ ራሱ መልሶ ያበረታችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል። ኀይል ከዘላለም እስከ ዘላለም ለእርሱ ይሁን፤ አሜን። እንደ ታማኝ ወንድም በምቈጥረው በስልዋኑስ አማካይነት ይህን ዐጭር መልእክት ጽፌላችኋለሁ፤ የጻፍሁላችሁም ልመክራችሁና ይህ እውነተኛ የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን ልመሰክርላችሁ ብዬ ነው። በዚህ ጸጋ ጸንታችሁ ቁሙ። ከእናንተ ጋር የተመረጠችው፣ በባቢሎን የምትገኘው ሰላምታ ታቀርብላችኋለች፤ እንዲሁም ልጄ ማርቆስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል። በፍቅር አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ።

1 ጴጥሮስ 5:1-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እንግዲህ እኔ ከእነርሱ ጋር አብሬ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ የሆንኩ፥ የክርስቶስም መከራ ምስክር የሆንኩ፥ እንዲሁም ወደፊት የሚገለጠው ክብር ተካፋይ የምሆን፥ በመካከላችሁ ያሉትን የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ። በዐደራ የተሰጣችሁን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ መንጋውን የምትጠብቁትም በግድ ሳይሆን እግዚአብሔር በሚፈልገው ዐይነት፥ በፈቃደኛነት ይሁን፤ ለገንዘብ በመስገብገብ ሳይሆን ለማገልገል ባላችሁ ፍላጎት ይሁን። እንዲሁም በእናንተ ኀላፊነት ሥር ያሉትን ጨቊኖ በመግዛት ሳይሆን ለመንጋው መልካም ምሳሌነትን በማሳየት ይሁን። ይህን ብታደርጉ ዋናው እረኛ በሚገለጥበት ጊዜ የማይበላሸውን የክብር አክሊል ትቀበላላችሁ። እንዲሁም እናንተ ጐልማሶች! ለሽማግሌዎች ታዘዙ፤ ሁላችሁም ትሕትናን እንደ ልብስ ለብሳችሁ አንዱ ሌላውን ያገልግል፤ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል ለትሑቶች ግን ጸጋን ይሰጣል” ተብሎ ተጽፎአልና። እንግዲህ እግዚአብሔር በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ ሥር ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ። እርሱ ለእናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሐሳብ ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። በመጠን ኑሩ፤ ንቁም! ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ በዙሪያችሁ ይንጐራደዳል። በዓለም ሁሉ ያሉ ወንድሞቻችሁ ይህን ዐይነት መከራ እንደሚቀበሉ በማወቅ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ በክርስቶስ ወደ ዘለዓለም ክብር የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ እርሱ ራሱ ከተቀበላችሁት መከራ ያድናችኋል፤ ይደግፋችኋል፤ ያጸናችኋል፤ ይመሠርታችኋልም። ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ክብርና ኀይል ለእርሱ ይሁን! አሜን። ታማኝ ወንድም ነው ብዬ በማስበው በሲላስ አማካይነት ይህን መልእክት ባጭሩ ጽፌላችኋለሁ፤ የጻፍኩላችሁም ልመክራችሁና ይህ እውነተኛ የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን ልገልጽላችሁ ብዬ ነው፤ ስለዚህ በዚህ በእግዚአብሔር ጸጋ ጸንታችሁ ቁሙ። እንደ እናንተ የተመረጠችው፥ በባቢሎን ያለችው እኅት ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ ታቀርብላችኋለች፤ ልጄ ማርቆስም ሰላምታ ያቀርብላችኋል። በክርስቲያናዊ ፍቅር እርስ በርስ በመሳሳም ሰላምታ ተለዋወጡ። የክርስቶስ ለሆናችሁት ለሁላችሁም ሰላም ይሁን።

1 ጴጥሮስ 5:1-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እንግዲህ እኔ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ የክርስቶስም መከራ ምስክር ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ፥ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤ በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኀይል አትግዙ፤ የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ። እንዲሁም ጐበዞች ሆይ! ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ልበሱ፤ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፤ ለትሑታኑ ግን ጸጋን ይሰጣል። እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኀይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። በመጠን ኑሩ፤ ንቁም፤ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ፥ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል፤ ያጸናችሁማል፤ ያበረታችሁማል። ለእርሱ ክብርና ኀይል እስከዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን። እየመከርኋችሁና የምትቆሙባት ጸጋ እውነትኛ የእግዚአብሔር ጸጋ እንድትሆን እየመሰከርሁላችሁ፥ የታመነ ወንድም እንደ ሆነ በቈጠርሁት በስልዋኖስ እጅ በአጭሩ ጽፌላችኋለሁ። ከእናንተ ጋር ተመርጣ በባቢሎን ያለች ቤተ ክርስቲያን፥ ልጄም ማርቆስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። በፍቅር አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። በክርስቶስ ላላችሁ ለሁላችሁ ሰላም ይሁን። አሜን።

1 ጴጥሮስ 5:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እንግዲህ እኔ፥ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ የክርስቶስም መከራ ምስክር ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ፥ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤ በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤ የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ። እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታኑ ግን ጸጋን ይሰጣል። እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁምል ያበረታችሁማል። ለእርሱ ክብርና ኃይል እስከዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን። እየመከርኋችሁና የምትቆሙባት ጸጋ እውነትኛ የእግዚአብሔር ጸጋ እንድትሆን እየመሰከርሁላችሁ፥ የታመነ ወንድም እንደ ሆነ በቈጠርሁት በስልዋኖስ እጅ በአጭሩ ጽፌላችኋለሁ። ከእናንተ ጋር ተመርጣ በባቢሎን ያለች ቤተ ክርስቲያን ልጄም ማርቆስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። በፍቅር አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። በክርስቶስ ላላችሁ ለሁላችሁ ሰላም ይሁን። አሜን።

1 ጴጥሮስ 5:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እንግዲህ እኔ ከእነርሱ ጋር አብሬ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ የሆንኩ፥ የክርስቶስም መከራ ምስክር የሆንኩ፥ እንዲሁም ወደ ፊት የሚገለጠው ክብር ተካፋይ የምሆን፥ በመካከላችሁ ያሉትን የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ። ኀላፊነት የተሰጣችሁን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ ይህም በግድ ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር ፍላጎት በፈቃደኝነት፥ ለጥቅም በመስገብገብ ሳይሆን በጽኑ ፍላጎት ይሁን፤ በእናንተ ኀላፊነት ሥር ላለው ለመንጋው መልካም ምሳሌ በመሆን እንጂ በኃይል በመግዛት አይሁን። የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማይደበዝዘውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ። እንዲሁም እናንተ ጐልማሶች! ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም ትሕትናን እንደ ልብስ ለብሳችሁ አንዱ ሌላውን ያገልግል፤ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታኑ ግን ጸጋን ይሰጣል” ተብሎ ተጽፎአልና። እንግዲህ እግዚአብሔር በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ ሥር ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ። እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። በመጠን ኑሩ፤ ንቁም! ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ ዙሪያውን ይንጐራደዳል። በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ይህን ዓይነት መከራ እንደሚቀበሉ በማወቅ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። በክርስቶስ ወደ ዘለዓለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ፥ እርሱ ራሱ ያበረታችኋል፤ ያጸናችኋል፤ ያቆማችኋል፤ ይመሠርታችኋልም። ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ክብርና ኃይል ለእርሱ ይሁን! አሜን። እንደ ታማኝ ወንድም በምቆጥረው በስልዋኖስ በኩል፥ ልመክራችሁና ጸንታችሁ የምትቆሙበት ይህ እውነተኛ የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን ልገልጽላችሁ በማለት፥ ይህን አጭር መልእክት ጽፌላችኋለሁ። ከእናንተ ጋር የተመረጠችው፥ በባቢሎን ያለችው ቤተ ክርስቲያን፥ ልጄ ማርቆስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። በፍቅር አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። በክርስቶስ ላላችሁ ለሁላችሁ ሰላም ይሁን።