የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 የጴጥሮስ መልእክት 5

5
የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማስተዳደር የተሰጠ መመሪያ
1እንግዲህ እኔ ከእነርሱ ጋር አብሬ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ የሆንኩ፥ የክርስቶስም መከራ ምስክር የሆንኩ፥ እንዲሁም ወደፊት የሚገለጠው ክብር ተካፋይ የምሆን፥ በመካከላችሁ ያሉትን የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ። 2በዐደራ የተሰጣችሁን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ መንጋውን የምትጠብቁትም በግድ ሳይሆን እግዚአብሔር በሚፈልገው ዐይነት፥ በፈቃደኛነት ይሁን፤ ለገንዘብ በመስገብገብ ሳይሆን ለማገልገል ባላችሁ ፍላጎት ይሁን። #ዮሐ. 21፥15-17። 3እንዲሁም በእናንተ ኀላፊነት ሥር ያሉትን ጨቊኖ በመግዛት ሳይሆን ለመንጋው መልካም ምሳሌነትን በማሳየት ይሁን። 4ይህን ብታደርጉ ዋናው እረኛ በሚገለጥበት ጊዜ የማይበላሸውን የክብር አክሊል ትቀበላላችሁ።
5እንዲሁም እናንተ ጐልማሶች! ለሽማግሌዎች ታዘዙ፤ ሁላችሁም ትሕትናን እንደ ልብስ ለብሳችሁ አንዱ ሌላውን ያገልግል፤
“እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል
ለትሑቶች ግን ጸጋን ይሰጣል” ተብሎ ተጽፎአልና። #ምሳ. 3፥34።
6እንግዲህ እግዚአብሔር በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ ሥር ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ። #ማቴ. 23፥12፤ ሉቃ. 14፥11፤ 18፥14። 7እርሱ ለእናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሐሳብ ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።
8በመጠን ኑሩ፤ ንቁም! ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ በዙሪያችሁ ይንጐራደዳል። 9በዓለም ሁሉ ያሉ ወንድሞቻችሁ ይህን ዐይነት መከራ እንደሚቀበሉ በማወቅ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። 10ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ በክርስቶስ ወደ ዘለዓለም ክብር የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ እርሱ ራሱ ከተቀበላችሁት መከራ ያድናችኋል፤ ይደግፋችኋል፤ ያጸናችኋል፤ ይመሠርታችኋልም። 11ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ክብርና ኀይል ለእርሱ ይሁን! አሜን።
የመጨረሻ ሰላምታ
12ታማኝ ወንድም ነው ብዬ በማስበው በሲላስ አማካይነት ይህን መልእክት ባጭሩ ጽፌላችኋለሁ፤ የጻፍኩላችሁም ልመክራችሁና ይህ እውነተኛ የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን ልገልጽላችሁ ብዬ ነው፤ ስለዚህ በዚህ በእግዚአብሔር ጸጋ ጸንታችሁ ቁሙ። #ሐ.ሥ. 15፥22፤40።
13እንደ እናንተ የተመረጠችው፥ በባቢሎን ያለችው እኅት ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ ታቀርብላችኋለች፤ ልጄ ማርቆስም ሰላምታ ያቀርብላችኋል። #ሐ.ሥ. 12፥12፤25፤ 13፥13፤ 15፥37-39፤ ቆላ. 4፥10፤ ፊልሞና 24። 14በክርስቲያናዊ ፍቅር እርስ በርስ በመሳሳም ሰላምታ ተለዋወጡ።
የክርስቶስ ለሆናችሁት ለሁላችሁም ሰላም ይሁን።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ