እንግዲህ ከእነርሱ ጋር እኔም ሽማግሌና የክርስቶስ መከራ ምስክር የሆንሁ፣ እንዲሁም ወደ ፊት የሚገለጠው ክብር ተካፋይ የምሆን፣ በመካከላችሁ ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤ በእናንተ ኀላፊነት ሥር ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ የምትጠብቁትም ከእግዚአብሔር እንደሚጠበቅባችሁ በግድ ሳይሆን በፈቃደኝነት፣ ለጥቅም በመስገብገብ ሳይሆን ለማገልገል ባላችሁ ጽኑ ፍላጎት ይሁን፤ እንዲሁም በዐደራ ለተሰጣችሁ መንጋ መልካም ምሳሌ በመሆን እንጂ በላያቸው በመሠልጠን አይሁን። የእረኞች አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማይጠፋውን አክሊል ትቀበላላችሁ። ጕልማሶች ሆይ፤ እናንተም እንዲሁ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርስ በመከባበር ትሕትናን ልበሱ፤ ምክንያቱም፣ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።” ስለዚህ እርሱ በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። ራሳችሁን የምትገዙ ሁኑ፣ ንቁም፤ ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ ወዲያ ወዲህ ይዞራልና። በዓለም ዙሪያ ያሉት ወንድሞቻችሁ ተመሳሳይ መከራ እንደሚቀበሉ ዐውቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። በክርስቶስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ፣ ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ እርሱ ራሱ መልሶ ያበረታችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል። ኀይል ከዘላለም እስከ ዘላለም ለእርሱ ይሁን፤ አሜን። እንደ ታማኝ ወንድም በምቈጥረው በስልዋኑስ አማካይነት ይህን ዐጭር መልእክት ጽፌላችኋለሁ፤ የጻፍሁላችሁም ልመክራችሁና ይህ እውነተኛ የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን ልመሰክርላችሁ ብዬ ነው። በዚህ ጸጋ ጸንታችሁ ቁሙ። ከእናንተ ጋር የተመረጠችው፣ በባቢሎን የምትገኘው ሰላምታ ታቀርብላችኋለች፤ እንዲሁም ልጄ ማርቆስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል። በፍቅር አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ።
1 ጴጥሮስ 5 ያንብቡ
ያዳምጡ 1 ጴጥሮስ 5
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ጴጥሮስ 5:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos