የሐጊት ልጅ አዶንያስ ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ ሄደ፤ ቤርሳቤህም “ወደ እኔ የመጣኸው በሰላም ነውን?” ስትል ጠየቀችው። እርሱም “አዎን በሰላም ነው የመጣሁት” ሲል መለሰ። ቀጠል አድርጎም “እኔ የምጠይቅሽ ጉዳይ አለኝ” አላት። እርስዋም “ጉዳይህ ምንድን ነው?” አለችው። አዶንያስም እንዲህ አላት፦ “ንጉሥ መሆን የሚገባኝ እኔ እንደ ነበርኩና ይህንንም በእስራኤል ምድር የሚኖር ሁሉ በተስፋ ይጠባበቅ እንደ ነበር አንቺ ራስሽ ታውቂያለሽ፤ ነገር ግን ጉዳዩ ከእግዚአብሔር ስለ ተወሰነ ለእኔ መሰጠት የሚገባው መንግሥት ተላልፎ ለወንድሜ ሆኖአል። አሁንም የምጠይቅሽ አንድ ጉዳይ ስላለኝ እምቢ በማለት አታሳፍሪኝ።” ቤርሳቤህም “ጉዳይህ ምንድን ነው?” ስትል ጠየቀችው። እርሱም “ንጉሥ ሰሎሞን አንቺን እምቢ እንደማይልሽ ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ አቢሻግ ተብላ የምትጠራውን ሹኔማይት ልጃገረድ በሚስትነት እንዲድርልኝ እባክሽ አማልጅኝ” አላት። እርስዋም “መልካም ነው! ይህን ለንጉሡ እነግርልሃለሁ” አለችው። ስለዚህም ቤርሳቤህ የአዶንያስን ጉዳይ ልትነግር ወደ ንጉሡ ገባች፤ ንጉሡም ከተቀመጠበት ተነሥቶ እናቱን እጅ በመንሣት ተቀበላት፤ እርሱም በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠ በኋላ ሌላ ዙፋን አስመጥቶ በቀኙ አስቀመጣት፤ እርስዋም “እንድትፈጽምልኝ የምጠይቅህ አንድ ትንሽ ጉዳይ አለኝ፤ እባክህ እምቢ በማለት አታሳፍረኝ” አለችው። ንጉሡም “እናቴ ሆይ! አላሳፍርሽም፤ ጉዳዩ ምንድን ነው” አላት። እርስዋም “ወንድምህ አዶንያስ አቢሻግን ሚስት አድርጎ ያገባ ዘንድ ፍቀድለት” አለችው። ንጉሡም “አቢሻግን በሚስትነት እንድድርለት ብቻ ለምን ትጠይቂኛለሽ? መንግሥቴንም ጭምር እንድለቅለት ለምን አልጠየቅሽኝም? እርሱ እኮ ታላቅ ወንድሜ ነው፤ ለምን ለካህኑ አብያታርና ለኢዮአብም ልዩ አስተያየት እንዳደርግላቸው አትጠይቂላቸውም!” አላት። ከዚህ በኋላ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ስም እንዲህ ሲል ማለ፦ “አዶንያስ ይህን በማቀዱ በሕይወቱ እንዲከፈል ባላደርግ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ በበለጠም ይቅጣኝ! እግዚአብሔር በአባቴ በዳዊት ዙፋን ላይ አስቀምጦ መንግሥቴን የጸና አድርጎልኛል፤ ይህን መንግሥት ለእኔና ለዘሮቼ በመስጠት ቃሉን ጠብቆአል፤ እንግዲህ አዶንያስ በዚህ በዛሬው ቀን በሞት እንደሚቀጣ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ!” ስለዚህም አዶንያስን እንዲገድለው ንጉሥ ሰሎሞን ለዮዳሄ ልጅ ለበናያ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ በናያም ሄዶ አዶንያስን ገደለው። ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን ካህኑን አብያታርን እንዲህ አለው፤ “ወደ ትውልድ አገርህ ወደ ዐናቶት ሂድ፤ አንተ በሞት ልትቀጣ ይገባህ ነበር፤ ነገር ግን የልዑል እግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት በአባቴ በዳዊት ፊት ትሸከም ስለ ነበርክ ከእርሱም ጋር የመከራው ሁሉ ተካፋይ ስለ ነበርክ እኔ አሁን አልገድልህም ከዚህም በኋላ ሰሎሞን አብያታርን የእግዚአብሔር ካህን ሆኖ ከሚያገለግልበት የክህነት ሥልጣን ሽሮ አባረረው፤ በዚህም ዐይነት እግዚአብሔር በሴሎ ስለ ካህኑ ዔሊና ስለ ትውልዱ የተናገረው ቃል ተፈጸመ።” በአንድ በኩል የአዶንያስ ደጋፊ፥ በሌላ በኩል ደግሞ የአቤሴሎም ተቃዋሚ የሆነው ኢዮአብ ይህን የተፈጸመውን ነገር ሁሉ ሰማ፤ ስለዚህም ሸሽቶ ወደ ተቀደሰው ድንኳን ሄደ፤ በዚያም የመሠዊያውን ቀንዶች ይዞ ተማጠነ፤ ኢዮአብ ወደ ተቀደሰ ድንኳን ሸሽቶ መሄዱንና በመሠዊያው አጠገብ መገኘቱን ሰሎሞን በሰማ ጊዜ፥ ኢዮአብን እንዲገድለው ለበናያ ትእዛዝ አስተላለፈ። እርሱም ወደ ተቀደሰው ድንኳን ሄዶ ኢዮአብን “ከዚህ ድንኳን እንድትወጣ ንጉሡ አዞሃል” አለው። ኢዮአብ ግን “አልወጣም! እዚሁ እሞታለሁ!” አለ። በናያም ተመልሶ ኢዮአብ ያለውን ለንጉሡ ነገረው። ሰሎሞንም በናያን እንዲህ አለው፦ “ኢዮአብ እንዳለህ ግደለውና ቅበረው፤ በዚህ አኳኋን ኢዮአብ ካፈሰሰው ንጹሕ ደም በደል የእኔንና የአባቴን ቤት የነጻን አድርገን። አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ኢዮአብ ስለ ገደላቸው ስለ እነዚያ ሰዎች ደም እግዚአብሔር ኢዮአብን ይቀጣዋል፤ ኢዮአብ ከእርሱ የተሻሉትን ሁለት ንጹሓን ሰዎች ገድሎአል፤ እነርሱም የእስራኤል ጦር አዛዥ አበኔርና የይሁዳ ጦር አዛዥ ዐማሣ ነበሩ። ኢዮአብ እነዚህን ሰዎች በመግደሉ በእርሱ ላይ የተፈጸመበት ቅጣት በእርሱና በዘሮቹ ላይ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኑር፤ በዙፋኑ ላይ ለሚቀመጡት ለዳዊት ዘሮች ግን የእግዚአብሔር ሰላም ለዘለዓለም አይለያቸው።” ስለዚህ በናያ በታዘዘው መሠረት ኢዮአብን ገደለው፤ በቤቱም አጠገብ በሚገኘው በረሓ ተቀበረ። ንጉሥ ሰሎሞን በኢዮአብ ፈንታ በናያን የሠራዊቱ አዛዥ፥ በአብያታርም ፈንታ ሳዶቅን ካህን አድርጎ ሾመ። ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን ሽምዒን አስጠርቶ እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “በዚህ በኢየሩሳሌም የራስህን መኖሪያ ቤት ሠርተህ ተቀመጥ፤ ከዚያ ወደየትም አትሂድ፤ ከከተማይቱ ወጥተህ የቄድሮንን ወንዝ ተሻግረህ ብትገኝ በእርግጥ ትሞታለህ፤ ለደምህም ተጠያቂ ራስህ ነህ።” ሺምዒም “ንጉሥ ሆይ! ውሳኔህ ትክክል ነው፤ እኔ አገልጋይህ አንተ ጌታዬ እንዳልከው አደርጋለሁ” ሲል መለሰ፤ ስለዚህ በኢየሩሳሌም ብዙ ጊዜ ተቀመጠ። ከሦስት ዓመት በኋላ ግን ሁለቱ የሺምዒ አገልጋዮች የማዕካ ልጅ ወደ ሆነው አኪሽ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ጋት ንጉሥ ኰብልለው ሄዱ፤ ሺምዒም ባሪያዎቹ በጋት መኖራቸው ተነገረው፤ አህያውን ጭኖ እነርሱን ለማግኘት በጋት ወደሚኖረው ወደ ንጉሥ አኪሽ ሄደ፤ እነርሱንም በዚያ ስላገኛቸው ወደ ቤቱ መልሶ አመጣቸው። ሰሎሞን ሺምዒ ከኢየሩሳሌም ወደ ጋት ሄዶ መመለሱን ሰማ። ንጉሡም ሽምዒን አስጠርቶ “ከኢየሩሳሌም እንዳትወጣ በእግዚአብሔር ስም አስምዬህ አልነበረምን? ወጥተህ ብትገኝ ግን በእርግጥ እንደምትሞት አስጠንቅቄህ አልነበረምን? በዚህስ ተስማምተህ ትእዛዜን እንደምትፈጽም ቃል ገብተህልኝ አልነበረምን?” አለው። “ታዲያ፥ በእግዚአብሔር ስም ከማልክ በኋላ የእግዚአብሔርን መሐላ ለምን አልጠበቅህም? ትእዛዜንስ ስለምን አላከበርክም? በአባቴ በንጉሥ ዳዊት ላይ የፈጸምከውን በደል ሁሉ በደንብ ታውቃለህ፤ አንተ ስላደረግኸው ክፉ ነገር እግዚአብሔር ራሱ ይቀጣሃል፤ እኔን ግን እግዚአብሔር ይባርከኛል፤ የዳዊት መንግሥትም ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል።” ከዚህም በኋላ ለዮዳሄ ልጅ ለበናያ ሺምዒን እንዲገድል ትእዛዝ አስተላለፈ፤ በናያም ሄዶ ሺምዒን ገደለው፤ በዚህም ዐይነት መንግሥቱ በሰሎሞን እጅ የጸና ሆነ።
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 2 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 2:13-46
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች