1 ነገሥት 2:13-46

1 ነገሥት 2:13-46 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

የአ​ጊት ልጅ አዶ​ን​ያ​ስም ወደ ሰሎ​ሞን እናት ወደ ቤር​ሳ​ቤህ መጣ፤ ሰገ​ደ​ላ​ትም፤ እር​ስ​ዋም፥ “ወደ እኔ መም​ጣ​ትህ በሰ​ላም ነውን?” አለ​ችው። እር​ሱም፥ “በሰ​ላም ነው” አለ። ደግ​ሞም፥ “ከአ​ንቺ ጋር ጉዳይ አለኝ” አለ፤ እር​ስ​ዋም፥ “ተና​ገር” አለ​ችው። እር​ሱም፥ “መን​ግ​ሥቱ ለእኔ እንደ ነበረ፥ እስ​ራ​ኤ​ልም ሁሉ ንጉሥ እሆን ዘንድ ፊታ​ቸ​ውን ወደ እኔ አድ​ር​ገው እንደ ነበረ አንቺ ታው​ቂ​ያ​ለሽ፤ ነገር ግን ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ሆኖ​ለ​ታ​ልና መን​ግ​ሥት ተመ​ልሳ ለወ​ን​ድሜ ሆና​ለች። አሁ​ንም አን​ዲት ልመና እለ​ም​ን​ሻ​ለሁ ፤ ፊት​ሽ​ንም አት​መ​ል​ሺ​ብኝ” አላት። እር​ስ​ዋም፥ “ተና​ገር” አለ​ችው፤ እር​ሱም፥ “ፊቱን አይ​መ​ል​ስ​ብ​ሽ​ምና፥ ሱነ​ማ​ዪ​ቱን አቢ​ሳን ይድ​ር​ልኝ ዘንድ ለን​ጉሡ ለሰ​ሎ​ሞን እን​ድ​ት​ነ​ግ​ሪው እለ​ም​ን​ሻ​ለሁ” አለ። ቤር​ሳ​ቤ​ህም፥ “መል​ካም ነው፤ ስለ አንተ ለን​ጉሡ እነ​ግ​ረ​ዋ​ለሁ” አለች። ቤር​ሳ​ቤ​ህም የአ​ዶ​ን​ያ​ስን ነገር ትነ​ግ​ረው ዘንድ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎ​ሞን ገባች፤ ንጉ​ሡም ሊቀ​በ​ላት ተነሣ፤ ሳማ​ትም፤ በዙ​ፋ​ኑም ተቀ​መጠ፤ ለን​ጉ​ሡም እናት ወን​በር አስ​መ​ጣ​ላት፤ በቀ​ኙም ተቀ​መ​ጠች። እር​ስ​ዋም፥ “አን​ዲት ትንሽ ልመና እለ​ም​ን​ሃ​ለሁ፤ ፊት​ህን አት​መ​ል​ስ​ብኝ” አለች። ንጉ​ሡም፥ “እናቴ ሆይ! ፊቴን አል​መ​ል​ስ​ብ​ሽ​ምና ለምኚ” አላት። እር​ስ​ዋም፥ “ሚስት ትሆ​ነው ዘንድ ለወ​ን​ድ​ምህ ለአ​ዶ​ን​ያስ ሱነ​ማ​ዪቱ አቢ​ሳን ይስ​ጡት” አለች። ንጉ​ሡም ሰሎ​ሞን ለእ​ናቱ መልሶ፥ “ሱነ​ማ​ዪ​ቱን አቢ​ሳን ለአ​ዶ​ን​ያስ ለምን ትለ​ም​ኚ​ለ​ታ​ለሽ? ታላቅ ወን​ድሜ ነውና መን​ግ​ሥ​ትን ደግሞ ለም​ኚ​ለት፤ ካህ​ኑም አብ​ያ​ታ​ርና የሶ​ር​ህያ ልጅ የጭ​ፍ​ሮች አለቃ ኢዮ​አብ ደግሞ ከእ​ርሱ ጋር ናቸው” አላት። ንጉ​ሡም ሰሎ​ሞን፦ እን​ዲህ ሲል በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ማለ። “አዶ​ን​ያስ ይህን ቃል በሕ​ይ​ወቱ ላይ እንደ ተና​ገረ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይህን ያድ​ር​ግ​ብኝ፤ ይህ​ንም ይጨ​ም​ር​ብኝ። አሁ​ንም ያጸ​ናኝ፥ በአ​ባ​ቴም በዳ​ዊት ዙፋን ላይ ያስ​ቀ​መ​ጠኝ፥ እንደ ተና​ገ​ረ​ውም ቤትን የሠ​ራ​ልኝ ሕያው እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን! ዛሬ አዶ​ን​ያስ ፈጽሞ ይገ​ደ​ላል። ንጉ​ሡም ሰሎ​ሞን የዮ​ዳ​ሄን ልጅ በና​ያ​ስን ላከ፤ እር​ሱም አረ​ደው፤ ያን​ጊ​ዜም አዶ​ን​ያስ ሞተ። ንጉ​ሡም ካህ​ኑን አብ​ያ​ታ​ርን፥ “አንተ ዛሬ የሞት ሰው ነበ​ርህ፤ ነገር ግን የአ​ም​ላ​ክን የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ታቦት በአ​ባቴ በዳ​ዊት ፊት ስለ ተሸ​ከ​ምህ፥ አባ​ቴም የተ​ቀ​በ​ለ​ውን መከራ ሁሉ አንተ ስለ ተቀ​በ​ልህ አል​ገ​ድ​ል​ህ​ምና በዓ​ና​ቶት ወዳ​ለው ወደ እር​ሻህ ፈጥ​ነህ ሂድ” አለው። በሴ​ሎም በዔሊ ቤት ላይ የተ​ና​ገ​ረው የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቃል ይፈ​ጸም ዘንድ ሰሎ​ሞን አብ​ያ​ታ​ርን ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ክህ​ነት አወ​ጣው። ለሶ​ር​ህያ ልጅ ለኢ​ዮ​አ​ብም ወሬ ደረ​ሰ​ለት፤ ኢዮ​አብ ከአ​ዶ​ን​ያስ ጋር ተባ​ብሮ ተከ​ተ​ለው እንጂ ከሰ​ሎ​ሞን ጋር አል​ተ​ባ​በ​ረም፤ አል​ተ​ከ​ተ​ለ​ው​ምም ነበ​ርና። ኢዮ​አ​ብም ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ድን​ኳን ሸሽቶ የመ​ሠ​ዊ​ያ​ውን ቀንድ ያዘ። ንጉ​ሡም ሰሎ​ሞን ኢዮ​አብ ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ድን​ኳን ሸሽቶ የመ​ሠ​ዊ​ያ​ውን ቀንድ እንደ ያዘ ሰማ፤ ንጉሥ ሰሎ​ሞ​ንም ወደ ኢዮ​አብ እን​ዲህ ሲል ላከ፤ “በመ​ሠ​ዊ​ያው ቀንድ የተ​ማ​ጠ​ንህ ምን ሆነህ ነው?” ኢዮ​አ​ብም፥ “ፈር​ቼ​ሃ​ለ​ሁና በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ተማ​ጠ​ንሁ” አለ። ሰሎ​ሞ​ንም የዮ​ዳ​ሄን ልጅ በን​ያ​ስን ልኮ፥ “ሂድ ግደ​ልና ቅበ​ረው” ብሎ አዘ​ዘው። የዮ​ዳሄ ልጅ በን​ያ​ስም ወደ ኢዮ​አብ ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ድን​ኳን መጥቶ፥ “ንጉሡ፦ ውጣ ይል​ሃል” አለው፤ ኢዮ​አ​ብም፥ “በዚህ እሞ​ታ​ለሁ እንጂ አል​ወ​ጣም” አለ። የዮ​ዳሄ ልጅ በን​ያ​ስም፦ ተመ​ልሶ “ኢዮ​አብ የተ​ና​ገ​ረው ቃል፥ የመ​ለ​ሰ​ል​ኝም እን​ዲህ ነው” ብሎ ለን​ጉሡ ነገ​ረው። ንጉ​ሡም አለው፥ “ሂድና እንደ ነገ​ረህ አድ​ርግ፤ ገድ​ለ​ህም ቅበ​ረው፤ ኢዮ​አ​ብም በከ​ንቱ ያፈ​ሰ​ሰ​ውን ደም ከእ​ኔና ከአ​ባቴ ቤት ታር​ቃ​ለህ። አባቴ ዳዊት ሳያ​ውቅ ከእ​ርሱ የሚ​ሻ​ሉ​ትን ሁለ​ቱን ጻድ​ቃን ሰዎች፥ የእ​ስ​ራ​ኤ​ልን ሠራ​ዊት አለቃ የኔ​ርን ልጅ አበ​ኔ​ርን፥ የይ​ሁ​ዳ​ንም ሠራ​ዊት አለቃ የኢ​ያ​ቴ​ርን ልጅ አሜ​ሳ​ይን በሰ​ይፍ ገድ​ሎ​አ​ልና እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የዐ​መፅ ደሙን በራሱ ላይ መለሰ። ደማ​ቸ​ውም በኢ​ዮ​አብ ራስና በዘሩ ራስ ላይ ለዘ​ለ​ዓ​ለም ይመ​ለስ፤ ለዳ​ዊት ግን ለዘ​ሩና ለቤቱ፥ ለዙ​ፋ​ኑም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሰላም ለዘ​ለ​ዓ​ለም ይሁን።” የዮ​ዳ​ሄም ልጅ በን​ያስ ወጥቶ ያዘው፤ ገደ​ለ​ውም፤ በም​ድረ በዳም ባለው በራሱ ቤት ቀበ​ረው። ንጉ​ሡም በእ​ርሱ ፋንታ የዮ​ዳ​ሄን ልጅ በን​ያ​ስን የሠ​ራ​ዊቱ አለቃ አድ​ርጎ ሾመ፤ መን​ግ​ሥ​ቱም በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ጸናች። በአ​ብ​ያ​ታ​ርም ፋንታ ካህ​ኑን ሳዶ​ቅን ሾመ። ንጉ​ሡም ልኮ ሳሚን አስ​ጠ​ራ​ውና እን​ዲህ አለው፥ “በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ቤት ሠር​ተህ ተቀ​መጥ፤ ወዲ​ህና ወዲ​ያም አት​ውጣ። በም​ት​ወ​ጣ​በ​ትና የቄ​ድ​ሮ​ን​ንም ፈፋ በም​ት​ሻ​ገ​ር​በት ቀን ፈጽ​መህ እን​ደ​ም​ት​ሞት ዕወቅ፤ ደም​ህም በራ​ስህ ላይ ይሆ​ናል።” ያን​ጊ​ዜም ንጉሡ አማ​ለው። ሳሚም ንጉ​ሡን፥ “ጌታዬ ንጉሥ የተ​ና​ገ​ር​ኸው ቃል መል​ካም ነው፤ አገ​ል​ጋ​ይ​ህም እን​ዲሁ ያደ​ር​ጋል” አለው፤ ሳሚም በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ሦስት ዓመት ተቀ​መጠ። ከሦ​ስት ዓመ​ትም በኋላ ከሳሚ አገ​ል​ጋ​ዮች ሁለቱ ወደ ጌት ንጉሥ ወደ መዓካ ልጅ ወደ አን​ኩስ ኰበ​ለሉ፤ ለሳ​ሚም፥ “እነሆ፥ አገ​ል​ጋ​ዮ​ችህ በጌት ናቸው” ብለው ነገ​ሩት። ሳሚም ተነሣ፤ አህ​ያ​ው​ንም ጭኖ አገ​ል​ጋ​ዮ​ቹን ይሻ ዘንድ ወደ ጌት ወደ አን​ኩስ ዘንድ ሄደ፤ ሳሚም ሄዶ አገ​ል​ጋ​ዮ​ቹን ከጌት አመጣ። ሰሎ​ሞ​ንም ሳሚ ከኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ወደ ጌት ሄዶ አገ​ል​ጋ​ዮ​ቹን እን​ዳ​መጣ ሰማ። ንጉ​ሡም ልኮ ሳሚን አስ​ጠ​ራና፥ “ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ለመ​ሄድ በም​ት​ወ​ጣ​በት ቀን ፈጽ​መህ እን​ድ​ት​ሞት ዕወቅ ብዬ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አላ​ስ​ማ​ል​ሁ​ህ​ምን? ወይስ አላ​ስ​መ​ሰ​ከ​ር​ሁ​ብ​ህ​ምን? የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን መሐላ፥ እኔም ያዘ​ዝ​ሁ​ትን ትእ​ዛዝ ስለ​ምን አል​ጠ​በ​ቅ​ህም?” አለው። ንጉ​ሡም ደግሞ ሳሚን፥ “አንተ በአ​ባቴ በዳ​ዊት ላይ የሠ​ራ​ኸ​ውን፥ ልብ​ህም ያሰ​በ​ውን ክፋት ሁሉ ታው​ቃ​ለህ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ክፋ​ት​ህን በራ​ስህ ላይ ይመ​ል​ሳል። ንጉሡ ሰሎ​ሞን ግን የተ​ባ​ረከ ይሆ​ናል፤ የዳ​ዊ​ትም ዙፋን በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ለዘ​ለ​ዓ​ለም ይጸ​ናል” አለው። ሰሎ​ሞ​ንም የዮ​ዳ​ሄን ልጅ በን​ያ​ስን አዘ​ዘው፤ ወጥ​ቶም ገደ​ለው። የሰ​ሎ​ሞ​ንም መን​ግ​ሥት በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ጸና።

1 ነገሥት 2:13-46 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በዚህ ጊዜ የአጊት ልጅ አዶንያስ ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ ሄደ። ቤርሳቤህም፣ “የመጣኸው በሰላም ነውን?” ስትል ጠየቀችው። እርሱም፣ “አዎን በሰላም ነው” ብሎ መለሰ። ከዚያም፣ “የምነግርሽ ጕዳይ አለኝ” አላት። እርሷም፣ “ዕሺ ተናገር” ብላ መለሰች። እርሱም፣ “መንግሥቱ የእኔ እንደ ነበረና እስራኤልም ሁሉ እኔ እንድነግሥ ዐይናቸውን ጥለውብኝ እንደ ነበር አንቺ ራስሽ ታውቂአለሽ፤ ሆኖም ነገሩ ከእግዚአብሔር የተቈረጠለት ሆነና ሁኔታዎች ተለዋውጠው፣ መንግሥቱ ለወንድሜ ተላለፈ። አሁንም አንዲት ነገር እለምንሻለሁ፤ አታሳፍሪኝ” አላት። እርሷም፣ “በል ዕሺ ተናገር” አለችው። እርሱም፣ “ንጉሥ ሰሎሞን መቼም እንቢ አይልሽምና ሱነማዪቱን አቢሳን እንዲድርልኝ ለምኚልኝ” አላት። ቤርሳቤህም፣ “መልካም ነው፤ ይህንኑ ለንጉሡ እነግርልሃለሁ” ብላ መለሰች። ስለዚህም ቤርሳቤህ የአዶንያስን ጕዳይ ልትነግረው ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ሄደች፤ ንጉሡም ሊቀበላት ተነሣ፤ እጅ ከነሣትም በኋላ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ንጉሡም ለእናቱ ሌላ ዙፋን አስመጥቶ በቀኙ አስቀመጣት። እርሷም፣ “የምለምንህ አንዲት ነገር አለችኝና እባክህ ዕሺ በለኝ” አለችው። ንጉሡም፣ “እናቴ ሆይ፤ አላሳፍርሽምና ንገሪኝ” ሲል መለሰላት። ስለዚህም፣ “ሱነማዪቱን አቢሳን ወንድምህ አዶንያስ ቢያገባትስ?” አለችው። ንጉሥ ሰሎሞንም እናቱን፣ “ስለ ምን ሱነማዪቱን አቢሳን ብቻ ለአዶንያስ ትጠይቂለታለሽ? ታላቅ ወንድሜ ስለ ሆነ መንግሥቱንም ጠይቂለት እንጂ፤ ለርሱ ብቻ ሳይሆን እንዲሁም ለካህኑ ለአብያታርና ለጽሩያ ልጅ ለኢዮአብ ጠይቂላቸው” አላት። ከዚያም ንጉሥ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ስም እንዲህ ሲል ማለ፤ “አዶንያስ ይህን ስለ ጠየቀ በሞት ሳይቀጣ ቢቀር፣ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጣብኝ፤ አሁንም በሚገባ ያጸናኝ፤ በአባቴ በዳዊት ዙፋን ያስቀመጠኝና በሰጠውም ተስፋ መሠረት ሥርወ መንግሥትን የመሠረተልኝ ሕያው እግዚአብሔርን አዶንያስ ዛሬ ይሞታል!” ስለዚህም አዶንያስን እንዲገድለው ንጉሥ ሰሎሞን፣ የዮዳሄን ልጅ በናያስን አዘዘው፤ በናያስም አዶንያስን መትቶ ገደለው። ንጉሡም ካህኑን አብያታርን፣ “ሞት የሚገባህ ሰው ነበርህ፤ ነገር ግን የጌታ እግዚአብሔርን ታቦት በአባቴ በዳዊት ፊት ስለ ተሸከምህ፣ አባቴ የተቀበለውንም መከራ ሁሉ ዐብረኸው ስለ ተቀበልህ፣ እኔ አሁን አልገድልህም፤ ዓናቶት ወዳለው ዕርሻህ ሂድ” አለው። ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ዔሊ ቤት በሴሎ የተናገረውን ቃል ለመፈጸም፣ ሰሎሞን አብያታርን ከእግዚአብሔር ክህነት አስወገደው። ከአቤሴሎም ጋራ ሳይሆን ከአዶንያስ ጋራ አሢሮ የነበረው ኢዮአብም ይህን በሰማ ጊዜ፣ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ የመሠዊያውን ቀንድ ያዘ። ኢዮአብ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ መሄዱንና በመሠዊያው አጠገብ መሆኑን ንጉሥ ሰሎሞን በሰማ ጊዜ፣ የዮዳሄን ልጅ በናያስን፣ “ሂድና ግደለው!” ብሎ አዘዘው። ስለዚህም በናያስ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ገብቶ ኢዮአብን፣ “ንጉሡ፣ ‘ከዚህ ውጣ’ ይልሃል” አለው። እርሱ ግን “አልወጣም፣ እዚሁ እሞታለሁ” አለው። በናያስም፣ “ኢዮአብ የሰጠኝ መልስ ይህ ነው” በማለት ለንጉሡ ተናገረ። ንጉሡም በናያስን እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “በል እንዳለው አድርግ፤ ግደልና ቅበረው፤ ኢዮአብ በከንቱ ካፈሰሰው ንጹሕ ደምም እኔንና የአባቴን ቤት አንጻን። አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ኢዮአብ በሁለቱ ሰዎች ላይ አደጋ ጥሎ በሰይፍ ገድሏቸዋልና ስላፈሰሰው ደም እግዚአብሔር ይበቀለዋል። የእስራኤል ሰራዊት አዛዥ የኔር ልጅ አበኔርና የይሁዳ ሰራዊት አዛዥ የዬቴር ልጅ አሜሳይ ሁለቱም ከርሱ የተሻሉና ይበልጥ ትክክለኛ ሰዎች ነበሩ። የደማቸውም ዕዳ ለዘላለም በኢዮአብና በዘሩ ራስ ላይ ይሁን። ነገር ግን በዳዊትና በዘሩ፣ በቤቱና በዙፋኑ ላይ የእግዚአብሔር ሰላም ለዘላለም ጸንቶ ይኑር።” ስለዚህም የዮዳሄ ልጅ በናያስ ወጣ፤ ኢዮአብንም መትቶ ገደለው፤ እርሱም በምድረ በዳ ባለው በገዛ ምድሩ ተቀበረ። ንጉሡም በኢዮአብ ቦታ የዮዳሄን ልጅ በናያስን በሰራዊቱ ላይ ሾመ፤ በአብያታርም ቦታ ካህኑን ሳዶቅን ተካ። ከዚያም ንጉሡ ሳሚን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “በኢየሩሳሌም ቤት ሠርተህ እዚያው ተቀመጥ፤ ከዚያ ግን የትም እንዳትሄድ፤ ነገር ግን ከዚያ ወጥተህ የቄድሮንን ሸለቆ ከተሻገርህ እንደምትሞት ዕወቅ፤ ደምህም በራስህ ላይ ይሆናል።” ሳሚም መልሶ ንጉሡን፣ “መልካም፤ ባሪያህ ጌታዬ ንጉሡ ያለውን ይፈጽማል” አለው፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ብዙ ጊዜ ተቀመጠ። ከሦስት ዓመት በኋላ ግን፣ ከሳሚ አገልጋዮች ሁለቱ ወደ ጋት ንጉሥ፣ ወደ መዓካ ልጅ ወደ አንኩስ ኰበለሉ፤ ለሳሚም፣ “እነሆ፣ አገልጋዮችህ በጋት ናቸው” ተብሎ ተነገረው። ሳሚ ይህን ሲሰማም አህዮቹን ጭኖ አገልጋዮቹን ለመፈለግ ጌት ወዳለው ወደ አንኩስ ሄደ፤ አገልጋዮቹንም ከጋት መልሶ አመጣቸው። ሳሚ ከኢየሩሳሌም ወደ ጋት ሄዶ መመለሱን ሰሎሞን በሰማ ጊዜ፣ ንጉሡ ሳሚን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ ‘ወደ ሌላ ቦታ የሄድህ ዕለት እንደምትሞት ዕወቅ’ ብዬ በእግዚአብሔር ስም አስምዬ አስጠንቅቄህ አልነበረምን? በዚያ ጊዜ አንተም፣ ‘መልካም ነው፤ እኔም እታዘዛለሁ’ ብለኸኝ ነበር፤ ታዲያ ለእግዚአብሔር የማልኸውን መሐላ ያልጠበቅኸውና እኔም የሰጠሁህን ትእዛዝ ያልፈጸምኸው ለምንድን ነው?” ንጉሡም መልሶ ሳሚን እንዲህ አለው፤ “በአባቴ በዳዊት ላይ ያደረግህበትን ክፉ ነገር ሁሉ ልብህ ያውቀዋል፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ክፉ ሥራህ ብድሩን ይከፍልሃል። ንጉሥ ሰሎሞን ግን ይባረካል፤ የዳዊትም ዙፋን በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” ከዚያም ንጉሡ የዮዳሄን ልጅ በናያስን አዘዘው፤ በናያስም ወጣ፤ ሳሚንም መትቶ ገደለው። በዚህ ጊዜም መንግሥቱ በሰሎሞን እጅ ጸና።

1 ነገሥት 2:13-46 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

የአጊት ልጅ አዶንያስም ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ መጣ፤ እርስዋም “ወደ እኔ መምጣትህ በሰላም ነውን?” አለች፤ እርሱም “በሰላም ነው፤” አለ። ደግሞም “ከአንቺ ጋር ጉዳይ አለኝ፤” አለ፤ እርስዋም “ተናገር፤” አለች። እርሱም “መንግሥቱ ለእኔ እንደ ነበረ፥ እስራኤልም ሁሉ ንጉሥ እሆን ዘንድ ፊታቸውን ወደ እኔ አድርገው እንደ ነበረ አንቺ ታውቂያለሽ፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆኖለታልና መንግሥቱ ከእኔ አልፎ ለወንድሜ ሆኖአል። አሁንም አንዲት ልመና እለምንሻለሁ፤ አታሳፍሪኝ፤” አለ። እርስዋም “ተናገር፤” አለችው። እርሱም “አያሳፍርሽምና ሱነማይቱን አቢሳን ይድርልኝ ዘንድ ለንጉሡ ለሰሎሞን እንድትነግሪው እለምንሻለሁ፤” አለ። ቤርሳቤህም “መልካም ነው፤ ስለ አንተ ለንጉሡ እነግረዋለሁ፤” አለች። ቤርሳቤህም የአዶንያስን ነገር ትነግረው ዘንድ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ገባች፤ ንጉሡም ሊቀበላት ተነሣ፤ ሳማትም፤ በዙፋኑም ተቀመጠ፤ ለንጉሡም እናት ወንበር አስመጣላት፤ በቀኙም ተቀመጠች። እርስዋም “አንዲት ታናሽ ልመና እለምንሃለሁ፤ አታሳፍረኝ፤” አለች። ንጉሡም “እናቴ ሆይ! አላሳፍርሽምና ለምኝ፤” አላት። እርስዋም “ሱነማይቱ አቢሳ ለወንድምህ ለአዶንያስ ትዳርለት፤” አለች። ንጉሡም ሰሎሞን ለእናቱ መልሶ “ሱነማይቱን አቢሳን ለአዶንያስ ለምን ትለምኝለታለሽ? ታላቅ ወንድሜ ነውና መንግሥትን ደግሞ ለምኚለት፤ ካህኑም አብያታርና የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ ደግሞ ከእርሱ ጋር ናቸው፤” አላት። ንጉሡም ሰሎሞን “አዶንያስ ይህን ቃል በሕይወቱ ላይ አለመናገሩ እንደ ሆነ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፤ ይህንም ይጨምርብኝ። አሁንም ያጸናኝ፥ በአባቴም በዳዊት ዙፋን ላይ ያስቀመጠኝ፥ እንደ ተናገረውም ቤትን የሠራልኝ ሕያው እግዚአብሔርን! ዛሬ አዶንያስ ፈጽሞ ይገደላል፤” ብሎ በእግዚአብሔር ማለ። ንጉሡም ሰሎሞን የዮዳሄን ልጅ በናያስን ላከ፤ እርሱም ወደቀበት፤ ሞተም። ንጉሡም ካህኑን አብያታርን “አንተ ዛሬ የሞት ሰው ነበርህ፤ ነገር ግን የአምላክን የእግዚአብሔርን ታቦት በአባቴ በዳዊት ፊት ስለ ተሸከምህ፥ አባቴም የተቀበለውን መከራ ሁሉ አንተ ስለ ተቀበልህ አልገድልህምና በዓናቶት ወዳለው ወደ እርሻህ ሂድ፤” አለው። በሴሎም በዔሊ ቤት ላይ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ ሰሎሞን አብያታርን ከእግዚአብሔር ክህነት አወጣው። ለኢዮአብም ወሬ ደረሰለት፤ ኢዮአብም አቤሴሎምን አልተከተለም ነበር ነገር ግን አዶንያስን ተከትሎ ነበር። ኢዮአብም ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ የመሠዊያውን ቀንድ ያዘ። ንጉሡም ሰሎሞን ኢዮአብ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ መሠዊያውን እንደ ያዘ ሰማ፤ ሰሎሞንም የዮዳሄን ልጅ በናያስን “ሂድ፤ ውደቅበት፤” ብሎ አዘዘው። በናያስም ወደ እግዚአብሔር ድንኳን መጥቶ “ንጉሡ ‘ውጣ’ ይልሃል፤” አለው፤ እርሱም “በዚህ እሞታለሁ እንጂ አልወጣም፤” አለ። በናያስም “ኢዮአብ የተናገረው ቃል የመለሰልኝም እንዲህ ነው፤” ብሎ ወደ ንጉሡ ወሬ አመጣ። ንጉሡም አለው “እንደ ነገረህ አድርግ፤ ኢዮአብም በከንቱ ያፈሰሰውን ደም ከእኔና ከአባቴ ቤት ታርቅ ዘንድ ገድለህ ቅበረው። አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ከእርሱ የሚሻሉትን ሁለቱን ጻድቃን ሰዎች፥ የእስራኤልን ሠራዊት አለቃ የኔርን ልጅ አበኔርን፥ የይሁዳንም ሠራዊት አለቃ የዬቴርን ልጅ አሜሳይን፥ በሰይፍ ገድሎአልና እግዚአብሔር ደሙን በራሱ ላይ ይመልሰው። ደማቸውም በኢዮአብ ራስና በዘሩ ራስ ላይ ለዘላለም ይመለስ፤ ለዳዊት ግን ለዘሩና ለቤቱ ለዙፋኑም የእግዚአብሔር ሰላም ለዘላለም ይሁን።” የዮዳሄም ልጅ በናያስ ወጥቶ ወደቀበት፤ ገደለውም፤ በምድረ በዳም ባለው በቤቱ ተቀበረ። ንጉሡም በእርሱ ፋንታ የዮዳሄን ልጅ በናያስን የሠራዊቱ አለቃ አደረገ፤ በአብያታርም ፋንታ ካህኑን ሳዶቅን አደረገ። ንጉሡም ልኮ ሳሚን አስጠራውና “በኢየሩሳሌም ቤት ሠርተህ ተቀመጥ፤ ወዲህና ወዲያም አትውጣ። በወጣህበትም ቀን፥ የቄድሮንንም ፈፋ በተሻገርህበት ቀን ፈጽመህ እንድትሞት እወቅ፤ ደምህ በራስህ ላይ ይሆናል፤” አለው። ሳሚም ንጉሡን “ነገሩ መልካም ነው፤ ጌታዬ ንጉሥ እንደ ተናገረ ባሪያህ እንዲሁ ያደርጋል፤” አለው፤ ሳሚም በኢየሩሳሌም ብዙ ቀን ተቀመጠ። ከሦስት ዓመትም በኋላ ከሳሚ ባሪያዎች ሁለቱ ወደ ጌት ንጉሥ ወደ መዓካ ልጅ ወደ አንኩስ ኮበለሉ፤ ሳሚንም “እነሆ፥ ባሪያዎችህ በጌት ናቸው፤” ብለው ነገሩት። ሳሚም ተነሣ፤ አህያውንም ጭኖ ባሪያዎቹን ይሻ ዘንድ ወደ ጌት ወደ አንኩስ ዘንድ ሄደ፤ ሳሚም ሄዶ ባሪያዎቹን ከጌት አመጣ። ሰሎሞንም ሳሚ ከኢየሩሳሌም ወደ ጌት ሄዶ እንደ ተመለሰ ሰማ። ንጉሡም ልኮ ሳሚን አስጠራና “ወዲህና ወዲያ ለመሄድ በወጣህ ቀን ፈጽመህ እንድትሞት እወቅ ብዬ በእግዚአብሔር አላስማልሁህምን? ወይስ አላስመሰከርሁብህምን? አንተም ‘ቃሉ መልካም ነው፤ ሰምቻለሁ፤’ አልኸኝ። የእግዚአብሔርን መሐላ እኔስ ያዘዝሁህን ትእዛዝ ስለ ምን አልጠበቅህም?” አለው። ንጉሡም ደግሞ ሳሚን “አንተ በአባቴ በዳዊት ላይ የሠራኸውን ልብህም ያሰበውን ክፋት ሁሉ ታውቃለህ፤ እግዚአብሔርም ክፋትህን በራስህ ላይ ይመልሳል። ንጉሡ ሰሎሞን ግን የተባረከ ይሆናል፤ የዳዊትም ዙፋን በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም ይጸናል፤” አለው። ንጉሡም የዮዳሄን ልጅ በናያስን አዘዘው፤ ወጥቶም ወደቀበት፤ ሞተም። መንግሥትም በሰሎሞን እጅ ጸና።

1 ነገሥት 2:13-46 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

የሐጊት ልጅ አዶንያስ ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ ሄደ፤ ቤርሳቤህም “ወደ እኔ የመጣኸው በሰላም ነውን?” ስትል ጠየቀችው። እርሱም “አዎን በሰላም ነው የመጣሁት” ሲል መለሰ። ቀጠል አድርጎም “እኔ የምጠይቅሽ ጉዳይ አለኝ” አላት። እርስዋም “ጉዳይህ ምንድን ነው?” አለችው። አዶንያስም እንዲህ አላት፦ “ንጉሥ መሆን የሚገባኝ እኔ እንደ ነበርኩና ይህንንም በእስራኤል ምድር የሚኖር ሁሉ በተስፋ ይጠባበቅ እንደ ነበር አንቺ ራስሽ ታውቂያለሽ፤ ነገር ግን ጉዳዩ ከእግዚአብሔር ስለ ተወሰነ ለእኔ መሰጠት የሚገባው መንግሥት ተላልፎ ለወንድሜ ሆኖአል። አሁንም የምጠይቅሽ አንድ ጉዳይ ስላለኝ እምቢ በማለት አታሳፍሪኝ።” ቤርሳቤህም “ጉዳይህ ምንድን ነው?” ስትል ጠየቀችው። እርሱም “ንጉሥ ሰሎሞን አንቺን እምቢ እንደማይልሽ ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ አቢሻግ ተብላ የምትጠራውን ሹኔማይት ልጃገረድ በሚስትነት እንዲድርልኝ እባክሽ አማልጅኝ” አላት። እርስዋም “መልካም ነው! ይህን ለንጉሡ እነግርልሃለሁ” አለችው። ስለዚህም ቤርሳቤህ የአዶንያስን ጉዳይ ልትነግር ወደ ንጉሡ ገባች፤ ንጉሡም ከተቀመጠበት ተነሥቶ እናቱን እጅ በመንሣት ተቀበላት፤ እርሱም በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠ በኋላ ሌላ ዙፋን አስመጥቶ በቀኙ አስቀመጣት፤ እርስዋም “እንድትፈጽምልኝ የምጠይቅህ አንድ ትንሽ ጉዳይ አለኝ፤ እባክህ እምቢ በማለት አታሳፍረኝ” አለችው። ንጉሡም “እናቴ ሆይ! አላሳፍርሽም፤ ጉዳዩ ምንድን ነው” አላት። እርስዋም “ወንድምህ አዶንያስ አቢሻግን ሚስት አድርጎ ያገባ ዘንድ ፍቀድለት” አለችው። ንጉሡም “አቢሻግን በሚስትነት እንድድርለት ብቻ ለምን ትጠይቂኛለሽ? መንግሥቴንም ጭምር እንድለቅለት ለምን አልጠየቅሽኝም? እርሱ እኮ ታላቅ ወንድሜ ነው፤ ለምን ለካህኑ አብያታርና ለኢዮአብም ልዩ አስተያየት እንዳደርግላቸው አትጠይቂላቸውም!” አላት። ከዚህ በኋላ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ስም እንዲህ ሲል ማለ፦ “አዶንያስ ይህን በማቀዱ በሕይወቱ እንዲከፈል ባላደርግ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ በበለጠም ይቅጣኝ! እግዚአብሔር በአባቴ በዳዊት ዙፋን ላይ አስቀምጦ መንግሥቴን የጸና አድርጎልኛል፤ ይህን መንግሥት ለእኔና ለዘሮቼ በመስጠት ቃሉን ጠብቆአል፤ እንግዲህ አዶንያስ በዚህ በዛሬው ቀን በሞት እንደሚቀጣ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ!” ስለዚህም አዶንያስን እንዲገድለው ንጉሥ ሰሎሞን ለዮዳሄ ልጅ ለበናያ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ በናያም ሄዶ አዶንያስን ገደለው። ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን ካህኑን አብያታርን እንዲህ አለው፤ “ወደ ትውልድ አገርህ ወደ ዐናቶት ሂድ፤ አንተ በሞት ልትቀጣ ይገባህ ነበር፤ ነገር ግን የልዑል እግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት በአባቴ በዳዊት ፊት ትሸከም ስለ ነበርክ ከእርሱም ጋር የመከራው ሁሉ ተካፋይ ስለ ነበርክ እኔ አሁን አልገድልህም ከዚህም በኋላ ሰሎሞን አብያታርን የእግዚአብሔር ካህን ሆኖ ከሚያገለግልበት የክህነት ሥልጣን ሽሮ አባረረው፤ በዚህም ዐይነት እግዚአብሔር በሴሎ ስለ ካህኑ ዔሊና ስለ ትውልዱ የተናገረው ቃል ተፈጸመ።” በአንድ በኩል የአዶንያስ ደጋፊ፥ በሌላ በኩል ደግሞ የአቤሴሎም ተቃዋሚ የሆነው ኢዮአብ ይህን የተፈጸመውን ነገር ሁሉ ሰማ፤ ስለዚህም ሸሽቶ ወደ ተቀደሰው ድንኳን ሄደ፤ በዚያም የመሠዊያውን ቀንዶች ይዞ ተማጠነ፤ ኢዮአብ ወደ ተቀደሰ ድንኳን ሸሽቶ መሄዱንና በመሠዊያው አጠገብ መገኘቱን ሰሎሞን በሰማ ጊዜ፥ ኢዮአብን እንዲገድለው ለበናያ ትእዛዝ አስተላለፈ። እርሱም ወደ ተቀደሰው ድንኳን ሄዶ ኢዮአብን “ከዚህ ድንኳን እንድትወጣ ንጉሡ አዞሃል” አለው። ኢዮአብ ግን “አልወጣም! እዚሁ እሞታለሁ!” አለ። በናያም ተመልሶ ኢዮአብ ያለውን ለንጉሡ ነገረው። ሰሎሞንም በናያን እንዲህ አለው፦ “ኢዮአብ እንዳለህ ግደለውና ቅበረው፤ በዚህ አኳኋን ኢዮአብ ካፈሰሰው ንጹሕ ደም በደል የእኔንና የአባቴን ቤት የነጻን አድርገን። አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ኢዮአብ ስለ ገደላቸው ስለ እነዚያ ሰዎች ደም እግዚአብሔር ኢዮአብን ይቀጣዋል፤ ኢዮአብ ከእርሱ የተሻሉትን ሁለት ንጹሓን ሰዎች ገድሎአል፤ እነርሱም የእስራኤል ጦር አዛዥ አበኔርና የይሁዳ ጦር አዛዥ ዐማሣ ነበሩ። ኢዮአብ እነዚህን ሰዎች በመግደሉ በእርሱ ላይ የተፈጸመበት ቅጣት በእርሱና በዘሮቹ ላይ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኑር፤ በዙፋኑ ላይ ለሚቀመጡት ለዳዊት ዘሮች ግን የእግዚአብሔር ሰላም ለዘለዓለም አይለያቸው።” ስለዚህ በናያ በታዘዘው መሠረት ኢዮአብን ገደለው፤ በቤቱም አጠገብ በሚገኘው በረሓ ተቀበረ። ንጉሥ ሰሎሞን በኢዮአብ ፈንታ በናያን የሠራዊቱ አዛዥ፥ በአብያታርም ፈንታ ሳዶቅን ካህን አድርጎ ሾመ። ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን ሽምዒን አስጠርቶ እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “በዚህ በኢየሩሳሌም የራስህን መኖሪያ ቤት ሠርተህ ተቀመጥ፤ ከዚያ ወደየትም አትሂድ፤ ከከተማይቱ ወጥተህ የቄድሮንን ወንዝ ተሻግረህ ብትገኝ በእርግጥ ትሞታለህ፤ ለደምህም ተጠያቂ ራስህ ነህ።” ሺምዒም “ንጉሥ ሆይ! ውሳኔህ ትክክል ነው፤ እኔ አገልጋይህ አንተ ጌታዬ እንዳልከው አደርጋለሁ” ሲል መለሰ፤ ስለዚህ በኢየሩሳሌም ብዙ ጊዜ ተቀመጠ። ከሦስት ዓመት በኋላ ግን ሁለቱ የሺምዒ አገልጋዮች የማዕካ ልጅ ወደ ሆነው አኪሽ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ጋት ንጉሥ ኰብልለው ሄዱ፤ ሺምዒም ባሪያዎቹ በጋት መኖራቸው ተነገረው፤ አህያውን ጭኖ እነርሱን ለማግኘት በጋት ወደሚኖረው ወደ ንጉሥ አኪሽ ሄደ፤ እነርሱንም በዚያ ስላገኛቸው ወደ ቤቱ መልሶ አመጣቸው። ሰሎሞን ሺምዒ ከኢየሩሳሌም ወደ ጋት ሄዶ መመለሱን ሰማ። ንጉሡም ሽምዒን አስጠርቶ “ከኢየሩሳሌም እንዳትወጣ በእግዚአብሔር ስም አስምዬህ አልነበረምን? ወጥተህ ብትገኝ ግን በእርግጥ እንደምትሞት አስጠንቅቄህ አልነበረምን? በዚህስ ተስማምተህ ትእዛዜን እንደምትፈጽም ቃል ገብተህልኝ አልነበረምን?” አለው። “ታዲያ፥ በእግዚአብሔር ስም ከማልክ በኋላ የእግዚአብሔርን መሐላ ለምን አልጠበቅህም? ትእዛዜንስ ስለምን አላከበርክም? በአባቴ በንጉሥ ዳዊት ላይ የፈጸምከውን በደል ሁሉ በደንብ ታውቃለህ፤ አንተ ስላደረግኸው ክፉ ነገር እግዚአብሔር ራሱ ይቀጣሃል፤ እኔን ግን እግዚአብሔር ይባርከኛል፤ የዳዊት መንግሥትም ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል።” ከዚህም በኋላ ለዮዳሄ ልጅ ለበናያ ሺምዒን እንዲገድል ትእዛዝ አስተላለፈ፤ በናያም ሄዶ ሺምዒን ገደለው፤ በዚህም ዐይነት መንግሥቱ በሰሎሞን እጅ የጸና ሆነ።

1 ነገሥት 2:13-46 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

የሐጊት ልጅ አዶንያስ ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ ሄደ፤ ቤርሳቤህም “ወደ እኔ የመጣኸው በሰላም ነውን?” ስትል ጠየቀችው። እርሱም “አዎን በሰላም ነው የመጣሁት” ሲል መለሰ። ቀጠል አድርጎም “እኔ የምጠይቅሽ ጉዳይ አለኝ” አላት። እርሷም “ጉዳይህ ምንድነው?” አለችው። አዶንያስም እንዲህ አላት፦ “ንጉሥ መሆን የሚገባኝ እኔ እንደ ነበርኩና ይህንንም በእስራኤል ምድር የሚኖር ሁሉ በተስፋ ይጠባበቅ እንደ ነበር አንቺ ራስሽ ታውቂያለሽ፤ ነገር ግን ጉዳዩ ከጌታ ስለ ተወሰነ ለእኔ መሰጠት የሚገባው መንግሥት ተላልፎ ለወንድሜ ሆኖአል። አሁንም የምጠይቅሽ አንድ ጉዳይ ስላለኝ እምቢ በማለት አታሳፍሪኝ።” ቤርሳቤህም “ጉዳይህ ምንድነው?” ስትል ጠየቀችው። እርሱም “ንጉሥ ሰሎሞን አንቺን እምቢ እንደማይልሽ ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ አቢሻግ ተብላ የምትጠራውን ሹኔማይት ልጃገረድ በሚስትነት እንዲድርልኝ እባክሽ አማልጅኝ” አላት። እርሷም “መልካም ነው! ይህን ለንጉሡ እነግርልሃለሁ” አለችው። ስለዚህም ቤርሳቤህ የአዶንያስን ጉዳይ ልትነግር ወደ ንጉሡ ገባች፤ ንጉሡም ከተቀመጠበት ተነሥቶ እናቱን እጅ በመንሣት ተቀበላት፤ እርሱም በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠ በኋላ ሌላ ዙፋን አስመጥቶ በቀኙ አስቀመጣት፤ እርሷም “እንድትፈጽምልኝ የምጠይቅህ አንድ ትንሽ ጉዳይ አለኝ፤ እባክህ እምቢ በማለት አታሳፍረኝ” አለችው። ንጉሡም “እናቴ ሆይ! አላሳፍርሽም፤ ጉዳዩ ምንድነው” አላት። እርሷም “ወንድምህ አዶንያስ አቢሻግን ሚስት አድርጎ ያገባ ዘንድ ፍቀድለት” አለችው። ንጉሡም “አቢሻግን በሚስትነት እንድድርለት ብቻ ለምን ትጠይቂኛለሽ? መንግሥቴንም ጭምር እንድለቅለት ለምን አልጠየቅሽኝም? እርሱ እኮ ታላቅ ወንድሜ ነው፤ ለምን ለካህኑ አብያታርና ለኢዮአብም ልዩ አስተያየት እንዳደርግላቸው አትጠይቂላቸውም!” አላት። ከዚህ በኋላ ሰሎሞን በጌታ ስም እንዲህ ሲል ማለ፦ “አዶንያስ ይህን በማቀዱ በሕይወቱ እንዲከፈል ባላደርግ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ በበለጠም ይቅጣኝ! እግዚአብሔር በአባቴ በዳዊት ዙፋን ላይ አስቀምጦ መንግሥቴን የጸና አድርጎልኛል፤ ይህን መንግሥት ለእኔና ለዘሮቼ በመስጠት ቃሉን ጠብቆአል፤ እንግዲህ አዶንያስ በዚህ በዛሬው ቀን በሞት እንደሚቀጣ በሕያው ጌታ ስም እምላለሁ!” ስለዚህም አዶንያስን እንዲገድለው ንጉሥ ሰሎሞን ለዮዳሄ ልጅ ለበናያ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ በናያም ሄዶ አዶንያስን ገደለው። ንጉሥ ሰሎሞን ካህኑን አብያታርን፤ “ወደ ትውልድ አገርህ ወደ ዐናቶት ሂድ፤ አንተ በሞት ልትቀጣ ይገባህ ነበር፤ ነገር ግን የልዑል እግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት በአባቴ በዳዊት ፊት ትሸከም ስለ ነበርክ ከእርሱም ጋር የመከራው ሁሉ ተካፋይ ስለ ነበርክ እኔ አሁን አልገድልህም” አለው። ስለዚህ ሰሎሞን አብያታርን የጌታ ካህን ሆኖ ከሚያገለግልበት የክህነት ሥልጣን ሽሮ አባረረው፤ በዚህም ዓይነት ጌታ በሴሎ ስለ ካህኑ ዔሊና ስለ ትውልዱ የተናገረው ቃል ተፈጸመ። በአንድ በኩል የአዶንያስ ደጋፊ፥ በሌላ በኩል ደግሞ የአቤሴሎም ተቃዋሚ የሆነው ኢዮአብ የተፈጸመውን ነገር ሁሉ ሰማ፤ ስለዚህም ሸሽቶ ወደ ጌታ ድንኳን ሄደ፤ በዚያም የመሠዊያውን ቀንዶች ይዞ ተማጠነ። ኢዮአብ ወደ ጌታ ድንኳን ሸሽቶ መሄዱንና በመሠዊያው አጠገብ መገኘቱን ሰሎሞን በሰማ ጊዜ፥ ኢዮአብን እንዲገድለው ለበናያ ትእዛዝ አስተላለፈ። እርሱም ወደ ጌታ ድንኳን ሄዶ ኢዮአብን “ከዚህ ድንኳን እንድትወጣ ንጉሡ አዞሃል” አለው። ኢዮአብ ግን “አልወጣም! እዚሁ እሞታለሁ!” አለ። በናያም ተመልሶ ኢዮአብ ያለውን ለንጉሡ ነገረው። ሰሎሞንም በናያን እንዲህ አለው፤ “ኢዮአብ እንዳለህ ግደለውና ቅበረው፤ በዚህ አኳኋን ኢዮአብ ካፈሰሰው ንጹሕ ደም በደል የእኔንና የአባቴን ቤት የነጻን አድርገን። አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ኢዮአብ ስለ ገደላቸው ስለ እነዚያ ሰዎች ደም ጌታ ኢዮአብን ይቀጣዋል፤ ኢዮአብ ከእርሱ የተሻሉትን ሁለት ንጹሓን ሰዎች ገድሎአል፤ እነርሱም የእስራኤል ጦር አዛዥ አበኔርና የይሁዳ ጦር አዛዥ ዐማሣ ነበሩ። ኢዮአብ እነዚህን ሰዎች በመግደሉ በእርሱ ላይ የተፈጸመበት ቅጣት በእርሱና በዘሮቹ ላይ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኑር፤ በዙፋኑ ላይ ለሚቀመጡት ለዳዊት ዘሮች ግን የጌታ ሰላም ለዘለዓለም አይለያቸው።” ስለዚህ በናያ በታዘዘው መሠረት ኢዮአብን ገደለው፤ በቤቱም አጠገብ በሚገኘው በረሓ ተቀበረ። ንጉሥ ሰሎሞን በኢዮአብ ፈንታ በናያን የሠራዊቱ አዛዥ፥ በአብያታርም ፈንታ ሳዶቅን ካህን አድርጎ ሾመ። ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን ሽምዒን አስጠርቶ እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “በዚህ በኢየሩሳሌም የራስህን መኖሪያ ቤት ሠርተህ ተቀመጥ፤ ከዚያ ወደየትም አትሂድ፤ ከከተማይቱ ወጥተህ የቄድሮንን ወንዝ ተሻግረህ ብትገኝ በእርግጥ ትሞታለህ፤ ለደምህም ተጠያቂ ራስህ ነህ።” ሺምዒም “ንጉሥ ሆይ! ውሳኔህ ትክክል ነው፤ እኔ አገልጋይህ አንተ ጌታዬ እንዳልከው አደርጋለሁ” ሲል መለሰ፤ ስለዚህ በኢየሩሳሌም ብዙ ጊዜ ተቀመጠ። ከሦስት ዓመት በኋላ ግን ሁለቱ የሺምዒ አገልጋዮች የማዕካ ልጅ ወደ ሆነው አኪሽ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ጋት ንጉሥ ኰብልለው ሄዱ፤ ሺምዒም ባርያዎቹ በጋት መኖራቸው ተነገረው፤ አህያውን ጭኖ እነርሱን ለማግኘት በጋት ወደሚኖረው ወደ ንጉሥ አኪሽ ሄደ፤ እነርሱንም በዚያ ስላገኛቸው ወደ ቤቱ መልሶ አመጣቸው። ሰሎሞን ሺምዒ ከኢየሩሳሌም ወደ ጋት ሄዶ መመለሱን ሰማ። ንጉሡም ሽምዒን አስጠርቶ “ከኢየሩሳሌም እንዳትወጣ በጌታ ስም አስምዬህ አልነበረምን? ወጥተህ ብትገኝ ግን በእርግጥ እንደምትሞት አስጠንቅቄህ አልነበረምን? በዚህስ ተስማምተህ ትእዛዜን እንደምትፈጽም ቃል ገብተህልኝ አልነበረምን?” አለው። “ታዲያ፥ በጌታ ስም ከማልክ በኋላ ለምን መሐላውን አልጠበቅህም? ያዘዝኩህን ትእዛዝስ ለምን አላከበርክም? በአባቴ በንጉሥ ዳዊት ላይ የፈጸምከውን በደል ሁሉ በደንብ ታውቃለህ፤ አንተ ስላደረግኸው ክፉ ነገር ጌታ ራሱ ይቀጣሃል፤ እኔን ንጉሥ ሰለሞንን ግን ጌታ ይባርከኛል፤ የዳዊት መንግሥትም ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል።” ከዚህም በኋላ ለዮዳሄ ልጅ ለበናያ ሺምዒን እንዲገድል ትእዛዝ አስተላለፈ፤ በናያም ሄዶ ሺምዒን ገደለው፤ በዚህም ዓይነት መንግሥቱ በሰሎሞን እጅ የጸና ሆነ።