በዚህ ጊዜ የአጊት ልጅ አዶንያስ ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ ሄደ። ቤርሳቤህም፣ “የመጣኸው በሰላም ነውን?” ስትል ጠየቀችው። እርሱም፣ “አዎን በሰላም ነው” ብሎ መለሰ። ከዚያም፣ “የምነግርሽ ጕዳይ አለኝ” አላት። እርሷም፣ “ዕሺ ተናገር” ብላ መለሰች። እርሱም፣ “መንግሥቱ የእኔ እንደ ነበረና እስራኤልም ሁሉ እኔ እንድነግሥ ዐይናቸውን ጥለውብኝ እንደ ነበር አንቺ ራስሽ ታውቂአለሽ፤ ሆኖም ነገሩ ከእግዚአብሔር የተቈረጠለት ሆነና ሁኔታዎች ተለዋውጠው፣ መንግሥቱ ለወንድሜ ተላለፈ። አሁንም አንዲት ነገር እለምንሻለሁ፤ አታሳፍሪኝ” አላት። እርሷም፣ “በል ዕሺ ተናገር” አለችው። እርሱም፣ “ንጉሥ ሰሎሞን መቼም እንቢ አይልሽምና ሱነማዪቱን አቢሳን እንዲድርልኝ ለምኚልኝ” አላት። ቤርሳቤህም፣ “መልካም ነው፤ ይህንኑ ለንጉሡ እነግርልሃለሁ” ብላ መለሰች። ስለዚህም ቤርሳቤህ የአዶንያስን ጕዳይ ልትነግረው ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ሄደች፤ ንጉሡም ሊቀበላት ተነሣ፤ እጅ ከነሣትም በኋላ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ንጉሡም ለእናቱ ሌላ ዙፋን አስመጥቶ በቀኙ አስቀመጣት። እርሷም፣ “የምለምንህ አንዲት ነገር አለችኝና እባክህ ዕሺ በለኝ” አለችው። ንጉሡም፣ “እናቴ ሆይ፤ አላሳፍርሽምና ንገሪኝ” ሲል መለሰላት። ስለዚህም፣ “ሱነማዪቱን አቢሳን ወንድምህ አዶንያስ ቢያገባትስ?” አለችው። ንጉሥ ሰሎሞንም እናቱን፣ “ስለ ምን ሱነማዪቱን አቢሳን ብቻ ለአዶንያስ ትጠይቂለታለሽ? ታላቅ ወንድሜ ስለ ሆነ መንግሥቱንም ጠይቂለት እንጂ፤ ለርሱ ብቻ ሳይሆን እንዲሁም ለካህኑ ለአብያታርና ለጽሩያ ልጅ ለኢዮአብ ጠይቂላቸው” አላት። ከዚያም ንጉሥ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ስም እንዲህ ሲል ማለ፤ “አዶንያስ ይህን ስለ ጠየቀ በሞት ሳይቀጣ ቢቀር፣ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጣብኝ፤ አሁንም በሚገባ ያጸናኝ፤ በአባቴ በዳዊት ዙፋን ያስቀመጠኝና በሰጠውም ተስፋ መሠረት ሥርወ መንግሥትን የመሠረተልኝ ሕያው እግዚአብሔርን አዶንያስ ዛሬ ይሞታል!” ስለዚህም አዶንያስን እንዲገድለው ንጉሥ ሰሎሞን፣ የዮዳሄን ልጅ በናያስን አዘዘው፤ በናያስም አዶንያስን መትቶ ገደለው። ንጉሡም ካህኑን አብያታርን፣ “ሞት የሚገባህ ሰው ነበርህ፤ ነገር ግን የጌታ እግዚአብሔርን ታቦት በአባቴ በዳዊት ፊት ስለ ተሸከምህ፣ አባቴ የተቀበለውንም መከራ ሁሉ ዐብረኸው ስለ ተቀበልህ፣ እኔ አሁን አልገድልህም፤ ዓናቶት ወዳለው ዕርሻህ ሂድ” አለው። ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ዔሊ ቤት በሴሎ የተናገረውን ቃል ለመፈጸም፣ ሰሎሞን አብያታርን ከእግዚአብሔር ክህነት አስወገደው። ከአቤሴሎም ጋራ ሳይሆን ከአዶንያስ ጋራ አሢሮ የነበረው ኢዮአብም ይህን በሰማ ጊዜ፣ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ የመሠዊያውን ቀንድ ያዘ። ኢዮአብ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ መሄዱንና በመሠዊያው አጠገብ መሆኑን ንጉሥ ሰሎሞን በሰማ ጊዜ፣ የዮዳሄን ልጅ በናያስን፣ “ሂድና ግደለው!” ብሎ አዘዘው። ስለዚህም በናያስ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ገብቶ ኢዮአብን፣ “ንጉሡ፣ ‘ከዚህ ውጣ’ ይልሃል” አለው። እርሱ ግን “አልወጣም፣ እዚሁ እሞታለሁ” አለው። በናያስም፣ “ኢዮአብ የሰጠኝ መልስ ይህ ነው” በማለት ለንጉሡ ተናገረ። ንጉሡም በናያስን እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “በል እንዳለው አድርግ፤ ግደልና ቅበረው፤ ኢዮአብ በከንቱ ካፈሰሰው ንጹሕ ደምም እኔንና የአባቴን ቤት አንጻን። አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ኢዮአብ በሁለቱ ሰዎች ላይ አደጋ ጥሎ በሰይፍ ገድሏቸዋልና ስላፈሰሰው ደም እግዚአብሔር ይበቀለዋል። የእስራኤል ሰራዊት አዛዥ የኔር ልጅ አበኔርና የይሁዳ ሰራዊት አዛዥ የዬቴር ልጅ አሜሳይ ሁለቱም ከርሱ የተሻሉና ይበልጥ ትክክለኛ ሰዎች ነበሩ። የደማቸውም ዕዳ ለዘላለም በኢዮአብና በዘሩ ራስ ላይ ይሁን። ነገር ግን በዳዊትና በዘሩ፣ በቤቱና በዙፋኑ ላይ የእግዚአብሔር ሰላም ለዘላለም ጸንቶ ይኑር።” ስለዚህም የዮዳሄ ልጅ በናያስ ወጣ፤ ኢዮአብንም መትቶ ገደለው፤ እርሱም በምድረ በዳ ባለው በገዛ ምድሩ ተቀበረ። ንጉሡም በኢዮአብ ቦታ የዮዳሄን ልጅ በናያስን በሰራዊቱ ላይ ሾመ፤ በአብያታርም ቦታ ካህኑን ሳዶቅን ተካ። ከዚያም ንጉሡ ሳሚን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “በኢየሩሳሌም ቤት ሠርተህ እዚያው ተቀመጥ፤ ከዚያ ግን የትም እንዳትሄድ፤ ነገር ግን ከዚያ ወጥተህ የቄድሮንን ሸለቆ ከተሻገርህ እንደምትሞት ዕወቅ፤ ደምህም በራስህ ላይ ይሆናል።” ሳሚም መልሶ ንጉሡን፣ “መልካም፤ ባሪያህ ጌታዬ ንጉሡ ያለውን ይፈጽማል” አለው፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ብዙ ጊዜ ተቀመጠ። ከሦስት ዓመት በኋላ ግን፣ ከሳሚ አገልጋዮች ሁለቱ ወደ ጋት ንጉሥ፣ ወደ መዓካ ልጅ ወደ አንኩስ ኰበለሉ፤ ለሳሚም፣ “እነሆ፣ አገልጋዮችህ በጋት ናቸው” ተብሎ ተነገረው። ሳሚ ይህን ሲሰማም አህዮቹን ጭኖ አገልጋዮቹን ለመፈለግ ጌት ወዳለው ወደ አንኩስ ሄደ፤ አገልጋዮቹንም ከጋት መልሶ አመጣቸው። ሳሚ ከኢየሩሳሌም ወደ ጋት ሄዶ መመለሱን ሰሎሞን በሰማ ጊዜ፣ ንጉሡ ሳሚን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ ‘ወደ ሌላ ቦታ የሄድህ ዕለት እንደምትሞት ዕወቅ’ ብዬ በእግዚአብሔር ስም አስምዬ አስጠንቅቄህ አልነበረምን? በዚያ ጊዜ አንተም፣ ‘መልካም ነው፤ እኔም እታዘዛለሁ’ ብለኸኝ ነበር፤ ታዲያ ለእግዚአብሔር የማልኸውን መሐላ ያልጠበቅኸውና እኔም የሰጠሁህን ትእዛዝ ያልፈጸምኸው ለምንድን ነው?” ንጉሡም መልሶ ሳሚን እንዲህ አለው፤ “በአባቴ በዳዊት ላይ ያደረግህበትን ክፉ ነገር ሁሉ ልብህ ያውቀዋል፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ክፉ ሥራህ ብድሩን ይከፍልሃል። ንጉሥ ሰሎሞን ግን ይባረካል፤ የዳዊትም ዙፋን በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” ከዚያም ንጉሡ የዮዳሄን ልጅ በናያስን አዘዘው፤ በናያስም ወጣ፤ ሳሚንም መትቶ ገደለው። በዚህ ጊዜም መንግሥቱ በሰሎሞን እጅ ጸና።
1 ነገሥት 2 ያንብቡ
ያዳምጡ 1 ነገሥት 2
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ነገሥት 2:13-46
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች