አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 9
9
ከምርኮ የተመለሰው የእስራኤል ሕዝብ
1የእስራኤል ሕዝብ በየቤተሰቡ ተመዝግቦ ነበር፤ ይህም ታሪክ በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ሰፍሮ ይገኛል።
የይሁዳ ሕዝብ በሠራው ኃጢአት ምክንያት በመቀጣት ተማርኮ ወደ ባቢሎን ተወስዶ ነበር፤ 2በየከተማው ወዳለው ይዞታቸው የተመለሱት የመጀመሪያዎቹ ካህናት፥ ሌዋውያን፥ የቤተ መቅደስ አገልጋዮችና ሌሎችም እስራኤላውያን ነበሩ። 3ከይሁዳ፥ ከብንያም፥ ከኤፍሬምና ከምናሴ ነገድ የሆኑ ሰዎች በኢየሩሳሌም ለመኖር ወደዚያ ሄዱ። #ነህ. 7፥73።
4-6ከይሁዳ ነገድ በኢየሩሳሌም ለመኖር የሄዱት ስድስት መቶ ዘጠና ቤተሰቦች ነበሩ።
የይሁዳ ልጅ የፋሬስ ዘሮች የዖምሪን የልጅ ልጅ የዓሚሁድን ልጅ ዑታይን መሪ አድርገው መረጡ፤ ሌሎቹ የፋሬስ ዘሮች ኢምሪና ባኒ ናቸው።
የይሁዳ ልጅ የሼላ ዘሮች በኲሩ ዐሳያን እርሱም ከልጆቹ ጋር የቤተሰቡ አለቃ ነበር።
የይሁዳ ልጅ የዛራሕ ዘሮች ይዑኤልን መሪያቸው እንዲሆን አደረጉ።
7-8ከብንያም ነገድ በኢየሩሳሌም ለመኖር የሄዱት የሚከተሉት ናቸው፦
የሃሰኑአ ልጅ ሆዳውያ፥ የሆዳውያ ልጅ መሹላም፥
የመሹላም ልጅ ሳሉ፥ የይሮሐም ልጅ ዩብነያ፥
የሚክሪ የልጅ ልጅ የዑዚ ልጅ ኤላ፥
የዩብኒያ ልጅ ረዑኤል፥ የረዑኤል ልጅ ሸፋጥያ፥ የሸፋጥያ ልጅ መሹላም።
9ከብንያም ነገድ በኢየሩሳሌም ለመኖር የሄዱት በአጠቃላይ ዘጠኝ መቶ ኀምሳ ስድስት ቤተሰቦች ነበሩ፤ ከዚህ በላይ የተጠቀሱትም ወንዶች ሁሉ የቤተሰብ አለቆች ነበሩ።
በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ካህናት
10-12በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩት ካህናት የሚከተሉት ናቸው፦
ይዳዕያ፥ ይሆያሪብና ያኪን፤
በቤተ መቅደስ ዋና ባለሥልጣን የሆነው የሒልቂያ ልጅ ዐዛርያስ፤ የእርሱም የቀድሞ አባቶች መሹላም፥ ጻዶቅ፥ መራዮትና አሒጡብ ናቸው።
የይሮሐም ልጅ ዐዳያ፤ የእርሱም የቀድሞ አባቶች ፓሽሑር ማልኪያ ናቸው።
የዐዲኤል ልጅ ማዕሳይ፤ የእርሱም የቀድሞ አባቶች ያሕዜራ፥ መሹላም፥ መሺሌሚትና ኢሜር ናቸው።
13የቤተሰብ አለቆች የነበሩት ካህናት በድምሩ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሥልሳ ነበሩ፤ እነዚህ ሁሉ በቤተ መቅደስ ውስጥ ለሚከናወነው ሥራ በቂ ችሎታ ያላቸው ነበሩ።
በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ሌዋውያን
14-16በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩት ሌዋውያን የሚከተሉት ናቸው፦
የሐሹብ ልጅ ሸማዕያ፤ የእርሱም የቀድሞ አባቶች ከመራሪ ጐሣዎች የነበሩት ዓዝሪቃምና ሐሻብያ ናቸው።
ባቅባቃር፥ ሔሬሽና ጋላል፤
የሚካ ልጅ ማታንያ፤ የእርሱም የቀድሞ አባቶች ዚክሪና አሳፍ ናቸው።
የሸማዕያ ልጅ አብድዩ የእርሱም የቀድሞ አባቶች ጋላልና ይዱታን ናቸው።
የነጦፋ ከተማ ይዞታ በነበረው ግዛት ይኖር በነበረው የኤልቃና የልጅ ልጅ የአሳ ልጅ ቤሬክያ።
በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ የቤተ መቅደስ ዘበኞች
17በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ የቤተ መቅደስ ዘበኞች የሚከተሉት ናቸው፦
ሻሉም፥ ዓቁብ፥ ጣልሞን፥ አሒማንና ወንድሞቻቸው፤ የእነርሱም አለቃ ሻሉም ነበር፤ 18እስከዚያን ጊዜ ድረስ በምሥራቅ በኩል በንጉሥ ቅጽር በር መግቢያ ተመድበው ነበር፤ እነርሱም ቀደም ሲል ወደ ሌዋውያን ሰፈር በሚያስገቡት ቅጽር በሮች ዘብ ይጠብቁ ነበር።
19የኤቢያሳፍ የልጅ ልጅ የቆሬ ልጅ ሻሉም የቆሬ ጐሣ አባሎች ከሆኑት ከሌሎች ዘመዶቹ ጋር በመሆን የቀድሞ አባቶቻቸው የእግዚአብሔርን ሰፈር ይጠብቁ በነበረው ዐይነት እግዚአብሔር ወደሚመለክበት ድንኳን የሚያስገባውን በር ይጠብቁ ነበር። 20ቀደም ሲል የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ እነርሱን ይቈጣጠር ነበር፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበር።
21የመሼሌምያ ልጅ ዘካርያስ እግዚአብሔር ወደሚመለክበት ድንኳን በሚያስገባው በር ዘብ ጠባቂ ነበር።
22መግቢያ በሮችንና ቅጽር በሮችን ለመጠበቅ የተመረጡ በአጠቃላይ ሁለት መቶ ዐሥራ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም በሚኖሩባቸው መንደሮች መሠረት ተቈጥረው ተመዘገቡ፤ የእነርሱን የቀድሞ አባቶች በዚህ ኀላፊነት የመደቡአቸው ንጉሥ ዳዊትና ነቢዩ ሳሙኤል ነበሩ። 23እነርሱና ልጆቻቸው የእግዚአብሔር ቅጽር በሮችን መጠበቃቸውን ቀጠሉ። 24በእያንዳንዱ አቅጣጫ ማለትም በሰሜን፥ በደቡብ፥ በምሥራቅና በምዕራብ በእያንዳንዱም ቅጽር በር ዘበኞች ነበሩ፤ 25እነዚህን ዘበኞች በመንደሮቻቸው የሚኖሩ ዘመዶቻቸው በየሰባቱ ቀን ተራ እየገቡ መርዳት ነበረባቸው፤ 26አራቱም ሌዋውያን የዘበኞች አለቆች ሲሆኑ እነርሱም ሙሉ ሥልጣን ያላቸው ነበሩ፤ እንዲሁም በቤተ መቅደሱ ላሉት ክፍሎችና በውስጣቸውም ለሚቀመጡ ዕቃዎች ኀላፊዎች ነበሩ። 27ቤተ መቅደሱን የመጠበቅና በየማለዳው የቅጽር በሮችን የመክፈት ተግባር የእነርሱ በመሆኑ እነርሱ የሚያድሩት በቤተ መቅደሱ አካባቢ ነበር።
ሌሎች ሌዋውያን
28ሌሎቹ ሌዋውያን በአምልኮ ጊዜ መገልገያ ለሆኑ ንዋያተ ቅድሳት ኀላፊዎች ነበሩ፤ በአገልግሎት ላይ በሚውሉበት ጊዜ እየቈጠሩ አውጥተው፥ አገልግሎታቸው ሲያበቃም እየቈጠሩ መልሰው ያስቀምጡአቸው ነበር። 29ከእነርሱም አንዳዶች ደግሞ ለሌሎቹ ንዋያተ ቅድሳት፥ ለዱቄቱ፥ ለወይን ጠጁ፥ ለወይራ ዘይቱ፥ ለዕጣንና ለልዩ ልዩ ቅመማቅመም ሁሉ ኀላፊዎች ነበሩ፤ 30ከካህናቱም ወገኖች አንዳንዶቹ ቅመማቅመሙን የማዋሐዱን ኀላፊነት ወሰዱ።
31ከቆሬ ጐሣ የሻሉም የበኲር ልጅ የሆነው ማቲትያ የመባውን ኅብስት የማዘጋጀት ኀላፊነት ነበረው፤ 32የቀዓት ጐሣ አባሎች አንዳንዶቹ ለቤተ መቅደስ የሚሆን ኅብስት በየሰንበቱ የማዘጋጀት ኀላፊነት ነበረባቸው።
33ሌሎች የሌዋውያን ቤተሰቦች አለቆች መዘምራን ነበሩ፤ እነርሱ ሌት ተቀን የማገልገል ኀላፊነት ስለ ነበረባቸው ከሌሎች አገልግሎቶች ነጻ በመሆን በቤተ መቅደሱ ቅጽር ግቢ በተዘጋጁላቸው ክፍሎች ውስጥ ይኖሩ ነበር።
34እነዚህ ሁሉ የሌዋውያን ቤተሰቦች አለቆች ነበሩ፤ በየነገዳቸው ዝርዝር መሠረት መሪዎች ሆነው በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር።
የንጉሥ ሳኦል የቀድሞ አባቶችና ዘሮች
(1ዜ.መ. 8፥29-38)
35ይዒኤል የገባዖንን ከተማ ቈርቊሮ በዚያው ኖረ፤ ሚስቱ ማዕካ ተብላ የምትጠራ ስትሆን፥ 36የበኲር ልጁም ዓብዶን ይባል ነበር፤ ሌሎቹ የእርሱ ወንዶች ልጆች ጹር፥ ቂሽ፥ ባዓል፥ ኔር፥ ናዳብ፥ 37ገዶር፥ አሕዮ፥ ዘካርያስና የሺምዓ አባት ሚቅሎት ተብለው የሚጠሩት ናቸው፤ 38ሚቅሎት የሺምዓም አባት ነው እነርሱም በሌሎቹ በወንድሞቻቸው አቅራቢያ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር።
39ኔር ቂስን ወለደ፤ ቂስ ንጉሥ ሳኦልን ወለደ፤ ሳኦልም ዮናታን፥ ማልኪሹዓ፥ አቢናዳብና ኤሽባዓል ተብለው የሚጠሩትን ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ 40ዮናታንም መሪባዓልን ወለደ፤ መሪባዓልም ሚካን ወለደ፤ 41ሚካም ፒቶን፥ ሜሌክ፥ ታሬዓና አሐዝ ተብለው የሚጠሩትን ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ 42አሐዝም ያዕራን ወለደ፤ ያዕራም ዓሌሜት፥ ዓዝማዌትና ዚምሪ ተብለው የሚጠሩትን ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ ዚምሪም ሞጻን ወለደ፤ 43ሞጻም ቢንዓን ወለደ፤ ቢንዓም ረፋያን ወለደ፤ ረፋያም ኤልዓሳን ወለደ፤ ኤልዓሳም አጼልን ወለደ።
44አጼልም ዓዝሪቃም፥ ቦከሩ፥ እስማኤል፥ ሸዓርያ፥ አብድዩና ሐናን ተብለው የሚጠሩትን ስድስት ወንዶች ልጆችን ወለደ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 9: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997